በኬንያ የዩኬ ወታደሮች ፈጽመዋቸል የተባሉ ‘አሰቃቂ ድርጊቶች’ ምስክርነት መሰማት ጀመረ

ከአምስት ዓመት በፊት በጦሩ መኪና ተገጭታ የአካል ጉዳተኛ የሆነችው የ22 ዓመቷ ቻውላ ሜሙሲ
የምስሉ መግለጫ, ከአምስት ዓመት በፊት በጦሩ መኪና ተገጭታ የአካል ጉዳተኛ የሆነችው የ22 ዓመቷ ቻውላ ሜሙሲ

በኬንያ በሥልጠና ላይ ባሉ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ወታደሮች ጥሰቶች ተፈጽሞብናል የሚሉ ኬንያውያን ምስክርነታቸውን ከሰሞኑ እየሰጡ ነው።

ኬንያውያኑ በዩኬ ወታደሮች ደርሶብናል ያሏቸውን ልብ የሚሰብሩ ጥሰቶችን በተመለከተ ምስክርነታቸውን እየሰጡ ያሉት በአገሪቱ ፓርላማ ለተቋቋመ አጣሪ ቡድን ነው።

በኬንያ በመሰልጠን ላይ የነበሩት እና ባቱክ የተሰኙት የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች አድርሰዋቸዋል የተባሉ ግፎችን እና በደሎችን ለማጣራት ነው ይህ ሕዝባዊ አጣሪ ቡድን የተቋቋመው።

ለዚህ አጣሪ ኮሚቴ መነሻ የሆነው ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ተገድላ ተጥላ የተገኘችው ኬንያት የአግነስ ዋንጂሩ አስደንጋጭ ሁኔታ ነው።

በ21 ዓመቷ የተገደለችው አግነስ ዋንጂሩ አስከሬኗ በማዕከላዊ ኬንያ በሚገኝ ሆቴል በሽንት ቤት ፍሳሽ ማጠራቀሚያ ውስጥ የተገኘ ሲሆን፣ ይህ የሆነው ከዩኬ ወታደሮች ጋር አንድ ምሽት ላይ ስትዝናና ከታየች ከሦስት ወራት በኋላ ነው።

የአምስት ወር ጨቅላ እናት የነበረችው ሟቿ ዋንጂሩ ለመጨረሻ ጊዜ የታየችው ከሁለት የብሪታኒያ ወታደሮች ጋር ከመጠጥ ቤት ስትወጣ ነበር።

ታዲያ ከጊዜ በኋላ ወታደሮቹ ከቆዩበት ክፍል በስተጀርባ የአካል ክፍሎቿ ጎድለው እና በስለት ቆስለው አስከሬኗ ተገኝቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 የኬንያ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ተመልክቶ ዋንጂሩ በአንድ ወይም በሁለት የብሪታኒያ ወታደሮች ተገድላለች የሚል ብያኔ ሰጥቷል።

ባቱክ እና የኬንያ ባለሥልጣናት ግድያውን ለመሸፋፈን ሞክረዋል የሚሉ ክሶችን አጣሪው ቡድን ሰምቷል።

የዋንጂሩ የእህት ልጅ ኢስተር ኢንጆኪ ለዚህን ያህል ዓመታት ተጠያቂ ባለመኖሩ ቤተሰቡ ላይ የፈጠረውን ብስጭት ለቡድኑ አስረድታለች።

“እርማችንን ማውጣት እንፈልጋለን። ፍትህ እየጠየቅን ነው” ስትል ተናግራለች።

የኬንያ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት በግድያዋ ላይ ምርመራ ቢከፍትም የተከሰሰ ሰው የለም፤ እንዲሁም ኬንያ ተጠርጣሪዎች ተላልፈው እንዲሰጧት አልጠየቀችም።

ዩኬ ተጠርጣሪዎች ተላልፈው እንድትሰጥ የሚቀርብ ማንኛውንም ጥያቄ እንደማትቃወም ጠቁማለች።

ሌሎች ከተሰሙ አሳዛዥ ምስክርነቶችም መካከል ጦሩ በመኪና ገጭቶ ለአካል ጉዳተኛ የደረጋት ወጣት ነፍሰ ጡር፣ በሠራዊቱ የማሠልጠኛ ስፍራ ወታደሮቹ አስነስተውታል በተባለ እሳት ቤታቸውን አጥተው በአንበሳ ጉዳት የደረሳባቸው ሰዎች ይገኙበታል።

ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ተገድላ ተጥላ የተገኘችው ኬንያዊቷ አግነስ ዋንጂሩ

የፎቶው ባለመብት, ROSE WANYUA

የምስሉ መግለጫ, ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ተገድላ ተጥላ የተገኘችው ኬንያዊቷ አግነስ ዋንጂሩ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የባቱክ የጦር ሰፈር የተቋቋመው አገሪቱ ከቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ነጻነትዋን ከተጎናጸፈች በኋላ በአውሮፓውያኑ 1964 ሲሆን፣ ስፍራውም ከናይሮቢ 200 ኪሎሜትት ርቀት ላይ በምትገኘው ኛኙኪ ነው።

ላለፉት አስርት ዓመታት በአገሪቱ የተሰማሩት የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች በዚህ ወቅት ሕጉን ጥሰው ከሆነ በማንኛውም ወታደር ላይ ኬንያ ክስ እንደምትመሠርት የኬንያ መከላከያ ሚኒስትር አደን ዱዋሌ ገልጸዋል።

በኬንያ የሚገኘው የዩኬ ከፍተኛ ኮሚሽን ሂደቱን እንደሚያውቅ እና ኮሚሽኑም ሆነ ባቱክ ከአጣሪው ጋር እንደሚተባበሩ ለቢቢሲ ገልጿል።

በባቱክ የጦር ሰፈር አቅራቢያ በዚህ ሳምንት በተደረጉ አራት ሕዝባዊ ችሎቶች በብሪታንያ ወታደሮች ተፈጽመዋል የተባሉ ጥሰቶችን ለመስማት በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ ስፍራው ጎርፈዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በጦሩ መኪና ተገጭታ የአካል ጉዳተኛ የሆነችው የ22 ዓመቷ ቻውላ ሜሙሲ እናት ሜሙሱ ሎቼዴ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ልጃቸው በዊልቸር ላይ አንደሆነች እና የዩኬ ባለሥልጣናት እንደሚንካከቧት ቃል ገብተው እንደነበር ተናግረዋል።

“የፍርድ ቤት ክስ እንደማይፈልጉ እና ልጄን እንደሚንከባከቧት ለመወያየት ተወካይ ልከው ነበር” ሲሉ የዩኬ ጦር ልምምዶችን በሚያካሂድበት ስፍራ ለተቋቋመው ችሎት እና ለአጣሪው ቡድን ተናግረዋል።

ከኬንያ መንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት በየዓመቱ እስከ ስድስት የሻለቃ ጦር ለስምንት ሳምንታት ወታደራዊ ልምምዶችን ያደርጋሉ።

እናቲቱ እንደሚናገሩት ጦሩ የልጃቸውን መታከሚያ ለሁለት ዓመት ያህል ቢከፍልም፣ ነገር ግን ቃል በገባው መሠረት ካሳውን አልሰጠም ይላሉ።

አደጋውን መመልከቱን የሚናገረው ሌኖ ሌማራምባ የጦሩ መኪና ግለሰቧን ከገጫት በኋላ በዚያው ጥሏት መሄዱን መመልከቱ እንዳስደነገጠው ለቢቢሲ ገልጿል። የዐይን እማኙ ወጣቷንም በወቅቱ እንደረዳት ተናግሯል።

“የባቱክ መኪና ነበር። ላስቆመው ብሞክርም ዝም ብለው ነዱት” የሚለው የዐይን እማኙ “አሳዛኝ ትዕይንት ነበር። ሰውነቷ በደም ተጥለቅልቋል፣ አጥንቷ ተሰብሯል። ሰዎች ሊነኳት ፈሩ” በማለትም በእሱ መኪና አሳፍረው ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ምን ያህል ከባድ እንደነበረ ገልጿል።

ሌላኛዋ ምስክርነቷን የሰጠችው የ28 ዓመቷ ጄኔሪካ ናሞሩ በችሎቱ ላይ የተገኘችው ከአምስት ዓመት ሴት ልጇ ጋር ነበር።

በፓርላማው የተቋቋመው አጣሪ ቡድን አባላት
የምስሉ መግለጫ, በፓርላማው የተቋቋመው አጣሪ ቡድን አባላት

በኬንያ የፓርላማ መከላከያ ኮሚቴ ለተቋቋመው የአጣሪ ቡድን አባላትም ከአንደኛው የዩኬ ወታደር ጋር ግንኙነት እንደነበራት እና በወቅቱም ማርገዟን ገልጻለች።

ለወታደሩ ነፍሰጡር መሆኗን ስትነግረው ግንኙነቱን እንዳቋረጠ እና ኬንያንም ጥሎ በመሄድ ልጇን ብቻዋን እንድታሳድግ መገደዷን ተናግራለች።

ለተወሰነ ጊዜም በኢንተርኔት ግንኙነታቸው ቢቀጥልም ልጃቸው መወለዷን ስትነግረው ሁሉንም ዓይነቶች ግንኙነቶች አቁሟል ብላለች።

“አሁን የምፈልገው ልጄ ትምህርት ቤት እንድትሄድ እና የተሻለ የወደፊት ሕይወት እንዲኖራት ድጋፍ እንዲያደርግ ነው” ብላለች።

ሌላኛው አጣሪው የሰማው ከሦስት ዓመት በፊት የዱር እንስሳት መኖሪያ በነበረ የወታደራዊ የሥልጠና ስፍራ ላይ ወታደሮቹ አስነስተውታል ስለተባለው እሳት ነው። በዚህ የእሳት ቃጠሎ ለከፋ የጤና ችግር የተዳረጉ ነዋሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ለአራት ቀናት እንደቆየ የተነገረለት የእሳት ቃጠሎ ከ12,000 ሄክታር በላይ መሬት ሲያወድም፣ ቢያንስ የአንድ ሰው ሕይወት ቀጥፏል።

በችሎቱ ላይ የተገኘው ሊፓሶ ሌጌይ እሳቱ የዱር እንሳሳቱን መኖሪያ ካወደመ በኋላ አንድ አንበሳ ሰዎች ወደሚኖሩበት ሰፈር ገብቶ ጥቃት እንዳደረሰበት ገልጿል። የደረሰበት ጥቃት የከፋ እንደሆነ ተናግሮ በሕይወት በመትረፉ ዕድለኛ እንደሆነ መስክሯል።

ሊሞት ተቃርቦ እንደነበር የገለጸው ሊፓሶ ጀርባው ላይ ጉዳት ደርሶብኛል ብሏል።

በተጨማሪም ቃጠሎው መሬታቸው ላይ ባደረሰው ውድመት ምክንያት ማረስ እንደማይችሉም በዚህ ወቅት የተናገረው ሊፓሶ ጅብ እና ነብርን ጨምሮ የዱር እንስሳት ኑሯቸውን ስጋት ላይ ጥለውታል ብሏል።

በርካቶችም ከእሳት ቃጠሎው በኋላ የከፋ የአተነፋፈስ እና የዐይን እክሎች እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል። ሲሞን ካቡሩ የተባለው ግለሰብ በጭስ ምክንያት በገጠው የአተነፋፈስ ችግር ምክንያት ለመድኃኒት ጥገኛ እንደሆነ የህክምና ማስረጃዎቹን የፓርላማ አባላትን ለያዘው አጣሪ ቡድን አሳይቷል።

ቃጠሎውን ተከትሎ ከ7 ሺህ የሚበልጡ የአካባቢው ነዋሪዎች በጦሩ ላይ በብሪታኒያ ጦር ላይ ሕጋዊ እርምጃዎችን መጀመራቸው ተነግሯል።