ቻይና በደህንነት ስጋት ምክንያት ስውር የኤሌክትሪክ መኪና በር እጀታዎችን አገደች

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ቻይና በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ስውር የበር እጀታዎች እንዳይኖሩ አገደች። ይህ እርምጃ የቢሊየነሩ ኤሎን መስክ ኩባንያ በሆነው ቴስላ ለገበያ ቀርበው ተወዳጅነት ያተረፉት አወዛጋቢ ዲዛይኖችን መጠቀምን ያቆመች የመጀመሪያዋ አገር አድርጓታል።

ይህ ውሳኔ የተሰማው በዓለም ዙሪያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከደህንነት ተቆጣጣሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው ባለበት ወቅት ነው።

ቻይና ውስጥ ሁለት የዢያኦሚ (Xiaomi) የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የደረሱት ከባድ አደጋዎችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ መቋረጥ በሮች እንዳይከፈቱ ሳያደርግ አይቀርም ተብሏል።

በአዲሱ ደንብ መሠረት፣ መኪኖች በሮቻቸው በውስጥም ሆነ በውጭ በኩል በእጅ በቀላሉ መከፈት (mechanical release) የሚችሉ ሲሆን ብቻ መሸጥ እንደሚፈቀድላቸው የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል።

አዲሶቹ መመሪያዎች እአአ ከጥር 1 2027 ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የቻይና የኢንዱስትሪ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ደንቦች ከእቃ መጫኛው በስተቀር የእያንዳንዱ ተሳፋሪ በር ውጫዊ ክፍል፣ እጀታውን ጋር ለመድረስ ከ6 ሴ.ሜ፣ በ2 ሴ.ሜ፣ በ2.5 ሴ.ሜ የማይበልጥ ክፍተት እንዲኖረው ይደነግጋል።

በመኪናው ውስጥ ደግሞ በሩን እንዴት መክፈት እንደሚቻል ለማሳየት ቢያንስ 1 ሴ.ሜ በ 0.7 ሴ.ሜ የሚለኩ ምልክቶች መኖር አለባቸው።

በባለሥልጣናት ፈቃድ የተሰጣቸው እና ወደ ቻይና ገበያ ለመግባት የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኙ መኪኖች ዲዛይናቸውን ለማዘመን ተጨማሪ ሁለት ዓመታት ይጠብቃቸዋል።

የተደበቁ እጀታዎች በቻይና አዲስ የኢነርጂ ተሽከርካሪ (NEV) ገበያ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ፤ ይህም የኤሌትሪክ መኪኖች እንዲሁም ቅይጥ መኪናዎችን እና በነዳጅ ባትሪ የሚሰሩትን ያካትታል።

በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ቻይና ዴይሊ ጋዜጣ ላይ በተጠቀሰው መረጃ መሠረት፣ እነዚህ መኪኖች ከ100 ምርጥ ሽያጭ ካላቸው የኤሌትሪክ መኪናዎች ውስጥ 60 በመቶ ያህሉን ይይዛሉ።

ምንም እንኳን እርምጃዎቹ የሚተገበሩት በቻይና ገበያ ላይ በሚሸጡ ሞዴሎች ላይ ብቻ ቢሆንም፣ አገሪቱ በዓለም አቀፍ የመኪና ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እያገኘች በመምጣቷ እርምጃው በዓለም ዙሪያ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይገመታል።

የቴስላ የበር እጀታዎች በአሜሪካ የደህንነት ተቆጣጣሪዎች ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን በአውሮፓ ያሉ ባለሥልጣናት የራሳቸውን እርምጃ ለመውሰድ እያጤኑ ነው።

በኅዳር ወር የአሜሪካ ብሔራዊ የፍጥነት መንገድ ትራፊክ ደህንነት አስተዳደር (NHTSA) በቴስላ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የበር እጀታዎች ላይ ያተኮረ ምርመራ አድርጓል።

አስተዳደሩ ምርምራውን ለማድረግ የወሰነው በድንገት ሥራቸውን አቁመው ሕጻናት በመኪኖቹ ውስጥ ተዘግቶባቸው እንዲቆዩ መሆናቸውን ተከትሎ የደረሰውን ሪፖርት ተከትሎ ነው።

አስተዳደሩ የኩባንያው ዋና ሞዴል በሆነው የቴስላ 2021 ሞዴል Y መኪኖች ላይ ዘጠኝ ቅሬታዎች እንደደረሱት ገልጿል።

በአራቱ ቅሬታዎች የመኪና ባለቤቶቹ ችግሩን ለመፍታት መስኮቱን መስበረቸውን ተናግረዋል።