ስዊዲናዊቷ የአካባቢ ጥበቃ ተከራካሪ ግሬታ ተንበርግ ጀርመን ውስጥ ታሰረች

ግሬታ በፖሊሶች ተይዛ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ግሬታ በፖሊሶች ተይዛ

ታዋቂዋ ወጣት የአካባቢ ጥበቃ ተከራካሪ ግሬታ ተንበርግ በምዕራባዊ ጀርመን ውስጥ በሚገኝ አንድ መንደር አቅራቢያ ከተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋሏን ፖሊስ አስታወቀ።

ስዊዲናዊቷ ግሬታ ከሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ጋር በመሆን ባዶውን የተተወው ሉትዘርራዝ የተባለው መንደር፣ በአቅራቢያ ላለ የድንጋይ ከሰል ማውጫ ማስፋፊያነት እንዲውል እየተካሄደ ያለውን ማፍረስ እንዲቆም በተደረገው ተቃውሞ ላይ ነው በፖሊስ የተያዘችው።

ፖሊስ ለቢቢሲ እንደተናገረው ግሬታ የተያዘችው ለእስር ሳይሆን ማንነቷን የሚገልጸው መታወቂያዋ ከተጣራ በኋላ ትለቀቃለች።

ፖሊስ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገረው ግሬታ ተንበርግ ወደ አንደኛው የማዕድን ማውጫ ተቃርበው ከነበሩት የተቃዋሚዎች ቡድን ውስጥ ነበረች።

ግሬታን ጨምሮ በተቃውሞው ወቅት በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ማንነት ከተጣራ በኋላ ከእስር ይለቀቃሉ ተብሏል።

ግሬታ እና አብረዋት የነበሩት ተቃዋሚዎች የተያዙበት የድንጋይ ከሰል የማዕድን ማውጫ ስፍራ እየፈረሰ ካለው መንደር ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

ግሬታ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ በሦስት የፖሊስ መኮንኖች ሸክም ላይ ሆና ፈገግ ብላ ስትወሰድ የሚያሳይ በተቃውሞው ስፍራ የተቀረጸ ቪዲዮ ታይቷል።

ፖሊስ ለሮይተርስ እንደተናገረው ከግሬታ በተጨማሪ አንድ ተቃዋሚ ግለሰብ ወደ ማዕድን ማውጫው ስፍራ ዘሎ ገብቷል።

የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ኃይል ለማግኘት የድንጋይ ከሰልን መጠቀም ጀርመን በካይ ጋዝን ለመቀነስ እያደረገች ያለውን ጥረት ያደናቅፋል ብለው ይከራከራሉ።

ጀርመን በአውሮፓውያኑ 2030 የድንጋይ ከሰልን ጥቅም ላይ መዋልን ለማቆም ቃል ገብታ ነበር።

ተቃውሞ በገጠመው የማዕድን ማውጫ የሚመረተው ሊግናይት የተባለው የድንጋይ ከሰል ከሌሎቹ በበለጠ አካባቢን የሚበክል ሲሆን፣ ከስፍራው በዓመት 25 ሚሊዮን ቶን የኸው ማዕድን ይመረትበታል።

የጀርመኗ ሉትዘርራዝ መንደር ለድንጋይ ከሰል ምርት ማስፋፊያነት እንዲፈርሱ ከተደረጉት መንደሮች መካከል የመጨረሻዋ ይሆናለች ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ እርምጃ የተፈጥሮ አካባቢን ይጎዳል በሚል የተካሄደውን ተቃውሞ አስተባባሪዎች፣ በተቃውሞው ላይ 35,000 የሚደርሱ ሰዎች መሳተፋቸውን ሲገልጹ፣ ፖሊስ ግን ቁጥሩን ወደ 15,000 የሚጠጋ ነው ብሏል።