የኢዜማ ሊቀመንበር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፓርቲያቸው አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Citizens for Social Justice
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀ መንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፓርቲያቸው አስታወቀ።
ዶክተር ጫኔ የእስር ማዘጃ በሌለበት ሁኔታ ትናንት እሁድ መስከረም 13/ 2016 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች መወሰዳቸውንም ኢዜማ ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሊቀ መንበሩ በቁጥጥር ስር ውለው የተወሰዱት የሰሌዳ ቁጥር በሌለው መኪና እንደሆነ ያሰፈረው መግለጫ፣ በምን ምክንያት እንደተያዙም ማወቅ አልተቻለም ብሏል።
ሆኖም ሊቀ መንበሩ በቁጥጥር ስር የዋሉበት መንገድ ሕግ እና ሥርዓትን ያልተከተለ ነው ሲልም ወቅሷል።
“ይህን መሰል ሕግ እና ሥርዓት ያልተከተለ እርምጃን በፅኑ እናወግዛለን” ሲል ፓርቲው ተቃውሞውን ገልጿል።
ኢዜማ ጉዳዩን በጥንቃቄ እና በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝም አስታውቆ፣ ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሟል ብሏል።
በጉዳዩ ላይ የፓርቲው መሪ እና የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ያሉት የለም።
ኢዜማ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሰባስበው የመሠረቱት ፓርቲ ሲሆን፣ የፓርቲው መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ተሹመው በማገለግል ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ከዚህ ቀደም የኢዜማ ምክትል ሊቀ መንበር እና አሁን የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶክተር ጫኔ፣ በመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) እና በኢኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ውስጥ በተለያዩ የአመራርነት ቦታዎች አገልግለዋል።
በተጨማሪም ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም. በነበረው ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥም አባል ነበሩ።
በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ ተወልደው ያደጉት ፖለቲከኛው ዶክተር ጫኔ፣ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአሥመራ ዩንቨርስቲ እና ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸውን ከፓርቲያቸው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ሦስተኛ ዲግሪያቸውን አሜሪካ ከሚገኘው አትላንቲክ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርስቲ ተቀብለዋል።
የፖለቲካውን ዓለም ከመቀላቀላቸው በፊት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት እና በአመራርነት አገልግለዋል፣ እንዲሁም በግል እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥም በከፍተኛ ኃላፊነት መሥራታቸው ተጠቅሷል።












