ኢዜማ በሥልጣን ላይ ካሉ ሚኒስትሮች ትይዩ 22 የራሱን ሚኒስትሮች መሰየሙን አስታወቀ

የትይዩ ካቢኔ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Ezema

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ፣ ኢዜማ የመንግሥት ሥራዎችን የሚከታተሉ 22 ትይዩ የካቢኔ ሚኒስትሮችን አዋቅሮ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ።

ኢዜማ የራሱን ትይዩ ካቢኔ ማቋቋሙን ባሳወቀበት መግለጫው እንዳመለከተው፣ ይህ ትይዩ ካቢኔ የዕለት ከዕለት የመንግሥት ተግባራትን መከታተል፣ የሚወጡ ረቂቅ ሕጎችን መተቸት፣ የፖሊሲ ንድፈ ሐሳቦችን ማውጣትና መሰል ሥራዎችን ያከናውናል።

የፓርቲው ትይዩ ካቢኔ ፀሐፊ አቶ ይመስገን መሳፍንት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ካቢኔውን ማቋቋም ያስፈለገበትን ምክንያት ለዲሞክራሲ፣ ለአገራዊ ለውጥ እንዲሁም አገሪቱ እንድትሄድበት በሚፈልገው የልማት መስክ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል በሚል መሆኑን ይናገራሉ።

አክለውም አገራዊ ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግ ወይንም ደግሞ በትክክል እየተመራ ስለመሆኑ የሚከታተል እና ድጋፍ የሚያደርግ የሰላ ትችቶችንም ለማቅረብ ይረዳል በሚል መቋቋሙን አመልክተዋል።

ጨምረውም በኢዜማ የተዋቀረው ትይዩ ካቢኔ መንግሥት በአዋጅ ያቋቋማቸው 22 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የሚመሩ ሚኒስትሮችን እንደሾመው ሁሉ፣ ፓርቲው 22 ትይዩ ሚኒስትሮችን መሰየሙን ጠቅሰዋል።

ኢዜማ የሰየማቸው ትይዩ ሚኒስትሮች ማንነትና ኃላፊነትን በሚመለከት ከቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ይመስገን ይህንን ለጊዜው ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል።

የፓርቲው ሕገ ደንብ በሚለው መሠረት የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ይህንን ትይዩ ካቢኔ አዋቅረው ሥራ መጀመራቸውን ያሳወቀው ኢዜማ፣ ይህ መንግሥታዊውን አስተዳደር ከሚያከናውነው መዋቅር በትይዩ የተቋቋመው ካቢኔ "በምንም መልኩ የተጠባባቂ መንግሥትነትና የባለአደራነት ስብስብ እንዳልሆነ" አመልክቷል።

በካቢኔው በየተለያዩ ዘርፎችን የሚከታተሉ ትይዩ የካቢኔ ሚኒስትሮች የተሰየሙ ሲሆን እሱም ቡድኖችን በማዋቀር ኃላፊነትን በማከፋፈል ፓርቲውን ተፎካካሪ ማድረግ ዋነኛ የሥራ ድርሻቸው እንደሚሆን ገልጿል።

አቶ ይመስገን አክለውም ፓርቲያቸው ትይዩ ካቢኔውን አዲስ መንግሥት እንደተመሰረተ ይፋ ማድረግ ያልቻለው አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር መሆኑን ጠቅሰው፣ ፓርቲያቸው የትይዩ ካቢኔውን ምሥረታ ያካሄደው ጥቅምት 08/2021 ዓ.ም እንደነበር አስታወሰዋል።

ነገር ግን በዚያ ወቅት በአገሪቱ የሰሜናዊ ክፍል ጦርነት እየተካሄደ ይህንን ይፋ ማድረግ ከፓርቲያቸው እንደማይጠበቅ መሆኑ ስለታመነበት መዘግየቱን ጠቅሰዋል።

ኢዜማ ይህንን ትይዩ ካቢኔ ሲያቋቁም በሥልጣን ላይ ያሉ ሕግ አውጪዎች ተፎካካሪዎቻቸው ምን እንደሚሉ እንዲያውቁ የሚያደርግና ለመራጩ ሕዝብ ደግሞ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ሌላም አማራጭ መፍትሔ እንዳለ ያሳያል ብሏል።

ይህ ትይዩ ካቢኔ "ተጠባባቂ መንግሥት ወይም የባለአደራ ስብስብ" አለመሆኑን በአጽንኦት አመልክቶ፣ በሕግ አውጪ ወይም በሕግ አስፈጻሚ ውስጥ ቀጥተኛ ሚና ተጫዋች በማድረግ የዴሞክራሲ መሣሪያ፣ የሰላምና የልማት መገልገያ አድርጎ ለውጥ አምጪ ማድረግ ይጠበቃል ብሏል ኢዜማ።

አዲሱ መንግሥት ሲዋቀር የኢዜማ አመራሮች እና አባላት ሥልጣን ማግኘታቸውን በማንሳት አይጋጭም ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ ይመስገን፣ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የፀደቀው የፓርቲው ሕገ ደንብ ላይ የትይዩ ካቢኔ ምሥረታ መስፈሩን አንስተው ሕጋዊ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም የፓርቲያቸው አባላትም ከመንግሥት የቀረበላቸውን የአብረን እንስራ ጥያቄ ተቀብለው በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ መገኘታቸው እንደማይጋጭ በመጥቀስ፣ እንዲያውም የመንግሥት ሥራን ለመከታተል እና እግር በእግር ለመተቸት ጥሩ መደላደል ይፈጥራል ሲሉ አብራርተዋል።

በኢዜማ ሕገ ደንብ የመሪው መዋቅር የትይዩ ካቢኔ እንደሚያዋቅር ይደነግጋል። የሕገ ደንቡ አንቀጽ 7.1.9 ፓርቲው ስልጣን ላይ ካልወጣ መሪው፣ ዋና ወይም ዋና ያልሆነ የፓርላማ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እንደሚሆን ይደነግጋል።

ትይዩ ካቢኔ ምንድን ነው?

በምርጫ መንግሥት የመመስረት ድምጽ ያላገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትይዩ ካቢኔ/ሚኒስትር የመሰየም ልምድ በተለይ በእንግሊዝ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሲተገበር የቆየ ነው።

በምርጫ የበላይነትን ያገኘው ፓርቲ መደበኛውን የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ ተቋማትን ይዞ ሚኒስትሮችን በመሾም በተግባር የዕለት ከዕለት ኃላፊነቱን ለመወጣት ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎች ይህ ሥልጣን ስለማይኖራቸው በፓርቲያቸው መሪ አማካኝነት መንግሥትን ከሚመራው ካቢኔ ትይዩ ተመሳሳይ የሆነ ካቢኔን ሊያዋቅሩ ይችላሉ።

በዚህም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ የመንግሥት አስተዳደር ዘርፎች ሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት በተለየ ያላቸውን አማራጭ እንዲሁም ብቁ ባለሙያዎችን ለሕዝቡ ለማቅረብና ለማስተዋወቅ ይጠቀሙበታል።

ትይዩ ካቢኔ/ሚኒስትር ሲዋቀር በኃላፊነት ላይ ካለው መዋቅር ጋር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ግልባጭ ሲሆን በመንግሥት የሥልጣን መዋቅር ውስጥ ላሉ የሚኒስትርነት ቦታዎች በተመሳሳይ ተቃዋሚዎች የራሳቸውን ሰው ይሰይማሉ።

እነዚህም ግለሰቦች የተመደቡባቸውን ቦታዎችን የሚመለከቱ ሕጎች፣ ክስተቶችና ሌሎችም ነገሮች በመያጋጥሙ ጊዜ የፓርቲያቸውን አቋምና አማራጭ ያንጸባርቃሉ።

የትይዩ ካቢኔ አባላት በሥልጣን ላይ ካሉት ሚኒስትሮች በተመሳሳይ በፓርቲያቸው የሚሰየሙ በመሆናቸው ትይዩ ሚኒስትር ተብለው በበርካታ አገራት የሚጠሩ ቢሆንም በመንግሥት ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን የአስፈጻሚነት ሥልጣን ግን የላቸውም። '

እንዲህ አይነቱ የተቃዋሚ ትይዩ የካቢኔ ሚኒስትሮች ካሏቸው መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ጃፓን የሚጠቀሱ ሲሆን በርካታ አገራት ውስጥም ይገኛሉ። ከአፍሪካም በደቡብ አፍሪካና ሱዳን ውስጥ የተቃዋሚዎች ትይዩ ካቢኔ አላቸው።