የኢትዮጵያን ገበያ ያንኳኳው 'የቻይና በርበሬ' የት ገባ?

የፎቶው ባለመብት, Tim Graham
ያሳለፍነው የኅዳር ወር ክረምቱን ተሰቅሎ የሚቆየው የበርበሬ ዋጋ የሚረጋጋበት፤ አዲስ ምርት የሚገባበት እና በርካታ ኢትዮጵያዊያን ረዘም ላለ ጊዜ የሚያቆያቸውን የበርበሬ ምርት የሚሸምቱበት ነው።
ወቅቱ ገበሬው፣ ሸማቹ፣ ነጋዴው እና ደላላው በጋራ የሚረባረቡበት ነው።
ታዲያ አዲስ አበባ በርበሬ አብቅላ ኢትዮጵያን ባትመግብም በመላው አገሪቱ የሚመረተው ሁሉ ተሰብስቦ ወደ የክልሉ ይከፋፈልባታል። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚዘዋወርበት ተክለሐይማኖት ደግሞ ዋነኛው የበርበሬ ግብይት ማዕከል ይባላል።
ታዲያ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ በእነዚህ አከፋፋዮች ዘንድ ያልተለመደ ምርት "የቻይና በርበሬ" በሚል ስያሜ ብቅ ብሎ መስከረም አጋማሽ ላይ መጥፋቱን ነጋዴዎች ይናገራሉ።
"በርበሬውን ከተክለ-ሐይማኖት ስናመጣው የታሸገበት ማዳበሪያ 'ሜድ ኢን ቻይና' [ቻይና የተሰራ] ይላል" ሲል ብርሌው አየሁ የተባለ ነጋዴ ይናገራል።
መሪ አካባቢ በሚገኘው የበርበሬ ገበያ 30 ገደማ የበርበሬ ነጋዴዎች ቢገኙበትም በጥቅምት ወር አጋማሽ ለዚህ ዘገባ ሲባል "የቻይና በርበሬ ያለህ" ተብሎ ቢፈለግም አለኝ ያለ አልተገኘም።
ብርሌው እንደሚለው ከሆነ ነጋዴዎቹ በርበሬውን ይሸጡ እንደነበር እንኳን እንዲታወቅባቸው አይፈልጉም፤ ደንበኛ ላለማጣት።
በርግጥ ተክለሐይማኖት አካባቢ የሚገኙት ዋነኛ የበርበሬ አከፋፋዮች ለዚህ ምስክር ናቸው። ቢቢሲ ተዘዋውሮ ያነጋጋራቸው ሦስት አከፋፋዮች "ይዘነውም አይተነውም አናውቅም" ይላሉ።
ነገር ግን በተቃራኒው አብዲ የተሰኘ አንድ አከፋፋይ አብዛኛው አከፋፋይ ይይዘው እንደነበር እና በኅዳር ወር አዲስ የበርበሬ ምርት በመድረሱ እና ዋጋውም በመረጋጋቱ 'የቻይና በርበሬ' ከገበያ መውጣቱን ይናገራል።
ቢቢሲ ይህንን 'የቻይና በርበሬ' የተባለውን የበርበሬ ምርት ምንጭ በተመለከተ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም።
በአሁኑ ጊዜ የበርበሬ ዋጋ ቢያንስ እስከ መቶ ብር ድረስ ቅናሽ አሳይቷል። የሐረር በርበሬ 220 ብር በመሸጥ ዝቅተኛ ዋጋውን ይዟል።
ከፍተኛ ጥራት አለው የሚባለው የማረቆ በርበሬ ደግሞ በኪሎ ቢበዛ 300 ብር ቢሸጥ ነው ሲል አብዲ ይናገራል። እስካለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ ዝቅተኛው የበርበሬ ዋጋ 340 ብር ደርሶ እንደነበር ሸማቾች ይናገራሉ።
በርበሬ ወይም 'ሬድ ፔፐር' በዓለም ላይ ከቲማቲም ቀጥሎ በከፍተኛ ደረጃ የሰው ልጆች የሚመገበው የምግብ ምርት ነው። በአውሮፓውያኑ 2018 በተደረገ ጥናት ቬትናማውያን በዓለም ከፍተኛው የበርበሬ ወይም 'ሬድ ፔፐር' ተጠቃሚ ተብለዋል።
ቀጥሎም ሕንድ እና አሜሪካ የሚከተሉ ሲሆን ሦስቱ አገራት በዓለም ላይ በዓመት ጥቅም ላይ ከሚውለው በርበሬ ውስጥ 41 በመቶውን ያህል ይመገባሉ።
ኢትዮጵያዊያን አጥብቀው የሚወዱት በርበሬ ዋጋ ለምን ይዋዥቃል?
ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ከሚያመርቱት በርበሬ ውስጥ 92.4 በመቶ የሚሆነውን ለገበያ እንደሚያቀርቡና ይህም በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ከፍተኛ የገበያ ሰብሎች ውስጥ እንደሚያስመድበው ከሁለት ዓመት በፊት አራት ምሁራን ባሳተሙት ጥናት ላይ ተጠቅሷል።
አምራች ገበሬዎቹ ከ60 በመቶ በላይ ምርታቸውን በአካባቢያቸው ለሚገኙ ጅምላ ነጋዴዎች ይሸጣሉ ሲል በአበበ ቢራ፣ ጥጋቡ ዳኘው፣ አበበ ዳኘው እና አስማማው አለሙ የተጠናው ጥናት ያሳያል።
መነሻው ከደቡብ አሜሪካ እንደሆነ የሚነገርለት በርበሬ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች በከፍተኛ መጠን ይመረታል።
ታዲያ ባለሞያዎቹ ባጠኑት ጥናት መሰረት ከፍተኛው የበርበሬ ምርት ተግዳሮት የግብአት እጥረት ነው። የበርበሬ ምርት ከፍተኛ የሆነ ለበሽታ ተጋላጭነት ደግሞ ሌላኛው ማነቆ ነው።
በተጨማሪም በርበሬ ሲተከል፣ ሲታረም እና ደርሶ ሲሰበሰብ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል ይፈልጋል። ስለዚህም በርበሬን ለማምረት የሚያስፈልገው ከፍተኛ የሰው ኃይል በምርቱ ላይ እና በዋጋው ላይ የእራሱ ተጽእኖ እንዳለው አጥኚዎቹ አመልክተዋል።
ሌላው ዋነኛ የበርበሬ ገበያ ላይ ያለው ማነቆ በግብይት ወቅት ያሉ ችግሮች ሲሆኑ፣ አጥኚዎቹ ያነጋገሯቸው አምራቾች እንደሚሉት ከመንግሥት ድጋፍ ማጣት ዋነኛው የገበያው ችግር አባባሽ ነው።
በመቀጠልም በቂ የመጋዘን ስፍራ አለመኖር፣ የብድር አገልግሎት እጥረት፣ በገዢ እና በሻጭ መካከል ያለ የትክክለኛ መረጃ ክፍተት እንዲሁም ከጥራት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች የበርበሬን ገበያ በመፈተን ይጠቀሳሉ።
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚስቶች ማኅበር ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት እና የመንግሥት የኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው ያገለገሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰዒድ ኑሩ (ዶ/ር) አራት ዋና ዋና ማነቆዎች በርበሬን ጨምሮ ሌሎች ወቅትን ጠብቀው የሚመረቱ ምርቶች ላይ ለሚታዩ የዋጋ መናር ምክንያት ናቸው ይላሉ።
የመጀመሪያው ምርቱን በበቂ ሁኔታ ያለማምረት ነው። አንድ ምርት በበቂ ሁኔታ በአገር ውስጥ ማምረት ካልተቻለ የቱንም አይነት እርምጃ ቢወሰድ ውጤት ማየት አይታሰብም ይላሉ ሰዒድ (ዶ/ር)።
እንደ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ያሉ በቂ የውጪ ምንዛሬ ያላቸው አገራት "ከበለገው ይግጣሉ" በማለት፣ በቂ ገንዘብ ያለው አገር በልግ ከሆነበት አገር የፈለገውን ምርት ገዝቶ ከዓመት ዓመት ሕዝቡን በተረጋጋ ገበያ ሊመግብ እንደሚችል ያብራራሉ።
ሁለተኛው እንደ በርበሬ ያሉ ምርቶችን ተገቢ የሆነ የማቆያ ዘዴዎችን በመጠቀም ከዓመት ዓመት እንዲቆይ ማድረግ ሌላው እርምጃ ነው። እንደ ቲማቲም ያሉ ከበርበሬ ይልቅ በአጭር ጊዜ የሚበላሹ ምርቶችን እንኳን ከገበያ እንዳይጠፉ የሚያደርግ ዘዴ መኖሩን የሚያስታውሱት ሰዒድ (ዶ/ር) ይህንን በበርበሬ ላይ መተግበር ቀላል ነው ይላሉ።
ሌላው መፍትሄ ነጋዴዎች ምርቱ በረከሰ ጊዜ እንዲያከማቹ ማስቻል ነው። "ኢትዮጵያ ውስጥ ነጋዴዎች ምርትን ያከማቻሉ የሚለው በአሉታዊ መልኩ ብቻ መወሰዱ አግባብ አይደለም" ይላሉ የኢኮኖሚ ባለሞያው።
"በውጪው አገር ኢንቨርተሪ የሚባል ኢንቨስትመንት አለ። አንድ ምርት ሲረክስ ነጋዴዎች ሰብስበው የሚያቆዩበት እና ምርቱ ገንዘባቸውን ይዞ ለቆየበት እንደ ሽልማት የተወሰነ ጭማሪ አድርገው፣ ምርቱ ሲጠፋ ለገበያ የሚያቀርቡበት ሥርዓት ማለት ነው። ይህ መጥፎ ጊዜ ጠብቀው ምርት የሚያከማቹትን አያጠቃልልም። በሪል ስቴት ወይም መሰል ምርቶች ላይ እንደሚደረግ ኢንቨስትመንት ማለት ነው" ሲሉ ሰዒድ (ዶ/ር) ያብራራሉ።
ሌላኛው ማነቆ እንደ በርበሬ ያሉ ምርቶች ላይ እሴት የሚጨምር ኢንዱስትሪ ቁጥር ትንሽ ከመሆኑ ጋር ይያያዛል። በርበሬ ተመጥኖ እና ተዘጋጅቶ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ምርት እንደመሆኑ፣ ዋጋው በረከሰ ወቅት በርበሬው ቢዘጋጅ ምርቱ በማይኖርበት ጊዜ የተወሰነ ገንዘብ ጨምሮ መሸጥ ዋነኛ አማራጭ መሆን ይቻላል ሲሉም ሦስተኛውን ችግር እና መፍትሄውን ያመላክታሉ።
የምርት እጥረት ባለበት ወቅት ከውጪ ማስገባቱ መፍትሄ ይሆናል?
የምርቱ እጥረት ባለበት ወቅት ከውጪ ማስገባት በእርግጥም በቂ የውጪ ምንዛሬ ላለው አገር መፍትሄ ነው የሚሉት ሰዒድ (ዶ/ር)፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ግን በርካታ ችግሮችን የሚያስከትል እርምጃ ነው ይላሉ። ነገር ግን አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ማስገባት በጥንቃቄ የሚወሰድ እርምጃ ከሆነ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት አጽንኦት ይሰጡታል።
ባለሙያው ስለ ጥቅሞቹ ከማብራራታቸው በፊት እጥረትን እንደ ችግር መመልከት ማቆም እንደሚያስፈልግ እና ለአንድ አልሚ እጥረት የገበያ እድል ሆኖ መታየት እንደሚገባው ያብራራሉ። ይህም የማምረት ችግር ለሌለበት አገር በተለይም ለእጥረት መፍትሄ መስጠት ለአምራቾች የገበያ እድል ነው ይላሉ።
ለዚህ ምሳሌ ሲጠቅሱ፡
"ከዓመታት በፊት የአገር ባህል ልብስ ከአውሮፓ ከሚመጡ ልብሶች በላይ ውድ መሆኑን ያዩ ቻይናውያን ወስደው በርካሽ ቴክኖሎጂ ሰርተው መልሰው አመጡት። ይህ እንግዲህ በየዕለቱ የማንለብሰው የክት ልብስ ነው። ታዲያ በየዕለቱ የምንጠቀማቸው ምርቶች እጥረት ሲፈጠር ይሄንን ለመሙላት መንቀሳቀስ ነበር የሚገባን" ሲሉ ሰዒድ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ የበርበሬ እጥረትን ለመፍታት ከውጪ አገር ማስገባቷ ዘላቂ እስካልሆነ ድረስ ለጥቅም ማዋል እንደሚያግዝ ያስረዳሉ። አንዱ ቴክኖሎጂውን መቅሰም ነው። የምግብ ምርት እንደመሆኑ አመራረቱን ማየት ቢያስፈልግም አንድን ምርት አንድ ጊዜ ወይም ሁለቴ አስገብቶ ምርቱን መሞከር ችግር እንደሌለውም ይናገራሉ።
ነገር ግን ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች በግብርና ሥራ ለዘመናት የቆዩበት ሙያ ሆኖ ሳለ ልክ እንደ ኢንዱስትሪ ምርቶች የግብርና ምርት ማስገባት ግን አስመጪውን እና ሸማቹን ለስንፍና መንግሥትን ደግሞ ለከባድ የውጪ ምንዛሬ እጥረት ይዳርጋል ይላሉ።
ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን እንደ ማሽኖች ያሉ ግብአቶችን ለማስገባት እንጂ አንድም ኪሎ የግብርና ምርት በቋሚነት ኢትዮጵያ ማስገባቷ አግባብ አይደለም ሲሉም ያክላሉ።
"አስመጪዎች በተሻለ ጥራት በቅናሽ የተመረት የግብርና ምርት ማምጣት ከጭቃው ከአፈሩ ጋር መታገልን ያስቀርላቸዋል። ይህ አንዴ ከተለመደ ከባድ ነው። ስንፍናን ያመጣል። ሱፐር ማርኬት ውስጥ ከግብፅ የሚመጣ አራት ፍሬ ብርቱካን በ280 ብር ይሸጣል። የተገነጠለ ዶሮ፣ እንቁላል እንዲሁም ሽንኩርት ከውጪ ይገባል። የአየር ንብረታችን እጅግ የተመቸ ሆኖ ሳለ ይህ እንዴት ሆነ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል" ይላሉ ሰኢድ ኑሩ (ዶ/ር)።
እንደ መውጫ
ከመስከረም አስከ ኅዳር ድረስ በግዴታ ነጋዴው ይዞ ሲሸጠው የቆየው 'የቻይና በርበሬን' በተመለከተ ነጋዴዎቹ በእርግጥም ቅሬታ ነበራቸው። በርበሬው ገና ከማዳበሪያው ሲፈታ ጀምሮ "የኬሚካል ሽታ" እንዳለው እና በርበሬውን የገዙ ደንበኞችም ደስተኛ እንዳልሆኑ ብርሌው ተናግሯል።
"የቻይናው በርበሬ በ250 ሲመጣ የአገር ውስጥ በርበሬ 350 ነበር የሚሸጠው። ይሄ ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ነበር። የገዙኝ ደንበኞችም ሲፈጭም ዱቄቱ እንደሚያምር ነግረውኝ ነበር። ምግብ ውስጥ ሲገባ ነው ችግሩ" ሲል ብርሌው ለቢቢሲ ተናግሯል። ደንበኞቹ ቅር መሰኘታቸውን እንደነገሩት አልሸሸገም።
የኢኮኖሚ ባለሞያው ሰዒድ (ዶ/ር) ከውጪ አገር እንዲህ ያሉ የግብርና ምርቶች ሲገቡ በሽታ ይዘው እንዳይመጡ ጥንቃቄ ተደርጎ መሞከር ይገባዋል ሲሉም ያስጠነቅቅቃሉ።
ገበሬዎች የቅንጬ አረም የሚሉት ከፍተኛ ጉዳት ያለው አረም ብሎም በአንድ ወቅት ከሕንድ የገባ ማንጎን ተከትሎ የመጣ የሰብል በሽታን በምሳሌነት ያነሳሉ።
"ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነጋዴ ቁጥር ለቁጥጥር የማይመች ነው" የሚሉት ባለሙያው በሌላው አገር አነስተኛ ቁጥር ያለው ትልልቅ ነጋዴ ስላለ ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ቀላል ያደርገዋል። ይህ ለአምራች ገበሬውም እንደሚሰራ ይናገራሉ።
ትርፍ የሚገኘው አንድም ብዙ ምርት በአነስተኛ ዋጋ በመሸጥ ወይም አነስተኛ ምርት በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያው፣ አነስተኛ ነጋዴም ሆነ ገበሬ ያለበት አገር የዋጋ መናሩ የሚገመት ነው ይላሉ።
"ባደጉ አገራት መንግሥት የሚደራደረው አራት አምስት ከሚሆኑ ሱፐርማርኬቶች ጋር ነው። እኛ ጋር 20 ሺህ ሱቆችን ዘጋን የሚል ዜና እንሰማለን። ይህ የበለጠ እጥረት ይፈጥራል። አንድ አዲስ አበባ በቅርቡ የተከፈተ ሱፐር ማርኬት አለ። ከራሱ ማሳ ብርቱካን 30 ብር በኪሎ አምጥቶ ይሸጣል። ከእርሱ ሱፐርማርኬት ምርቱን የገዙ አጠገቡ ያሉ ትንንሽ ሱቆች ራሱን ብርቱካን በእጥፍ 60 ብር ይሸጣሉ" ሲሉ ሰዒድ (ዶ/ር) በትልልቅ አቅራቢዎች እና አነስተኛ ቸርቻሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት ያስረዳሉ።
እንዲሁም የኢትዮጵያ የገበያ መዋቅር ደላላ የተጫነው እና ሰዎች በምርት ሥራ ላይ ከመሳተፍ ይልቅ በመሃል በመደለል እያተረፉ መኖርን መምረጣቸው ሌላው ከፍተኛ ችግር ነው ይላሉ ሰኢድ (ዶ/ር)።
ልክ እንደ አበባ ሁሉ የምግብ የሚያመርቱ ትልልቅ ኩባንያዎችን በማገዝ ወደ አገር ውስጥ በመጋበዝ ከእነሱ መማር እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ።
"በአንድ ጊዜ 100 ሻማ ማብራት አይቻልም" የሚሉት ሰኢድ "ከአንድ ሻማ መጀመር ግን ይቻላል" ይላሉ።
የአበባ አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከ10 ዓመት በፊት ኬንያ ውስጥ ምርጫን ተከትሎ የመጣ ቀውስን ሸሽተው ነበር። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የአበባ ምርት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ እንደሆነ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች የገቡበት ብሎም የቴክኖሎጂ ሽግግሩም በተሳካ ሁኔታ የተሳለጠበት ዘርፍ መሆኑን ያነሳሉ።
ይህ በሌላው ዘርፍ መደገም አለበት እንደ ሰኢድ ኑሩ (ዶ/ር) ትንታኔ።
"የመጀመሪያውም፣ ሁለተኛውም ሦስተኛውም መፍትሄ አንድ ነው። በግብርና ራሳችንን መቻል ነው" ሲሉ ዘመናዊ ግብርናን ማስፋፋት ብቸኛው መፍትሄ መሆኑን ባለሙያው ለቢቢሲ ተናግረዋል።












