በአሜሪካ በተፈጸመ ጥቃት 10 ሰዎች ሲገደሉ ተጠርጣሪው በፖሊስ እየተፈለገ ነው

የፖሊስ ተሽከርካሪዎች በጥቃቱ ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የፖሊስ ተሽከርካሪዎች በጥቃቱ ስፍራ

በአሜሪካዋ የካሊፎርኒያ ግዛት ከተማ በሆነችው ሞንቴሬይ ፓርክ ውስጥ በሚገኝ የንግድ ስፍራ በተፈጸመ የተኩስ ጥቃት አስር ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

በተጨማሪም ሌሎች አስር ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን ጥቃት ፈጻሚው በፖሊስ እየተፈለገ ነው።

በአሜሪካ ቅዳሜ ምሽት ላይ በቀሪው ዓለም ደግሞ እሁድ ንጋት ላይ ነው የሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ጥቃት የተፈጸመው።

በቻይና እና በአንዳንድ አገራት ውስጥ ዛሬ የሚከበረውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከተማዋ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀደም ብለው ተሰባስበው እንደነበር ተነግሯል።

የሎስ አልጀለስ አካባቢ የፖሊስ መሥሪያ ቤት እንዳለው ተኩሱን ከፍቷል በሚል የተጠረጠረው ግለሰብ ወንድ እንደሆነ ያመለከተ ቢሆንም፣ ስለግለሰቡ ተጨማሪ ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥቧል።

የፖሊስ ሻምበል አንድሩ ሜየር እንዳሉት የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ሠራተኞች አስር ሰዎች ወደ ተገደሉበት ስፍራ ጥቃቱን ተከትሎ በአስቸኳይ ደርሰዋል።

ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 10 ሰዎች ቆስለው ወደ አካባቢው ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን፣ የጉዳታቸው ሁኔታም ከቀላል አስከ አስጊ እንደሆነ ተነግሯል።

መርማሪዎች የጥቃቱን ምክንያት በተመለከተ የጥላቻ ወንጀል ነው ብሎ ለመደምደም ጊዜው ገና መሆኑን ገልጸዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንዳሳዩት ከሎስ አንጀለስ ከተማ በስተምሥራቅ 13 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሞንቴሬይ ፓርክ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች ተሰማርተዋል።

አንድ የዐይን እማኝ ለሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ እንደተናገረው፣ ሦስት ሰዎች ተሯሩጠው ወደ ምግብ ቤቱ በመግባት አንድ ከባድ ጠብመንጃ የታጠቀ ግለሰብ በአካባቢው ተኩስ መክፈቱን እና ቤቱን እንዲዘጋ እንደነገሩት ገልጿል።

ዓመታዊው የአዲስ ዓመት በዓል በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የሚከበር ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በነበረው ክብረ በዓል ላይ ከ100,000 ሕዝብ በላይ ሲታደምበት ቆይቷል።

ቅዳሜ ምሽት በርካታ ሕዝብ የታደመበት የበዓል ሥነ ሥርዓት ሲካሄድባት የነበረችው ሞንቴሬይ ፓርክ ከተማ 60,000 ያህል ነዋሪ ያላት ሲሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእስያ አገራት ማኅበረሰቦች ይገኙባታል።

የጨረቃ ዑደትን መሠረት በማድረግ የጊዜ ቀመራቸውን በሚያሰሉት በቻይና እና በተለያዩ የእስያ አገራት ውስጥ ያሉ ሕዝቦች አዲስ ዓመታቸውን የሚጀምሩት ዛሬ እሁድ ጥር 13/2015 ዓ.ም. ነው።