ወርቅ ለማምጣት ያለመችው በእግር ቀስት የምትወረውረው ሕንዳዊቷ አትሌት

የፎቶው ባለመብት, Abhilasha Chaudhary
የቀስት ስፖርት ተወዳዳሪዋ ዴቪ ፒክስ 50 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ዒላማውን ለመምታት ስታነጣጥር ፊቷ ላይ የሚነበበው ትኩረት ለየት ያለ ነው።
ሕንድ በሚገኘው አካዳሚ ልምምዷን የምታደርገው አብራት ከምትወዳደረው ተቀናቃኟ ጋር ነው። ተቀናቃኟም ልክ እንደሷ በምስጠት ታነጣጥራለች።
ነገር ግን ድቪ ወንበር ላይ ተቀምጣ ነው ይህን የምታደርገው። ቀስቷን በቀኝ እግሯ አንስታ በቀኝ ትከሻዋ ደግሞ ገመዱን አክርራ በመያዝ በአፏ ነው የምትተኩሰው።
ዴቪ ይህን ስታደርግ በታላቅ ምስጠት ነው። ከዒላማዋ ምንም ቢሆን አትዛነፍም።
ጃሙ ግዛት የተወለደችው የ17 ዓመቷ ታዳጊ ፎኮሜሊያ በተባለ በሽታ ምክንያት ነው እጆቿን ያጣችው። በቀስት ዒላማ ውድድር ያለ እጅ በመወዳደር የመጀመሪያዋ ሴት ሆናለች።
በእስያ ፓራ ጨዋታ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችው ዴቪ በአውሮፓውያኑ ነሃሴ 28 በፓሪስ በሚጀመረው ፓራሊምፒክስ ለመወዳደር ዝግጅቷን አጠናቃለች።
“ሕልሜ የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣት ነው” ትላለች ዴቪ። “እስከዛሬ ያገኘኋቸውን ሜዳሊያዎች ስመለከት ተጨማሪ እንዳሸንፍ መነቃቂያ ይሆነኛል።”
ዘንድሮ በሚካሄደው ፓራሊምፒክስ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ 4400 አትሌቶች በ22 የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ።
ፓራሊምፒክስ በአውሮፓውያኑ 1960 ከተጀመረ ወዲህ የቀስት ዒላማ ውድድር አብሮት ተጉዞ እዚህ ደርሷል። ብሪታኒያ፣ ዩኤስኤ እና ደቡብ ኮሪያ በፓራሊምፒክስ ውድድር በርካታ ሜዳሊያ ያላቸው ሲሆን ሕንድ በ17 ውድድሮች ተሳትፋ አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች።
በቀስት ዒላማ የሚወዳደሩ የፓራሊምፒክ አትሌቶች እንዳለባቸው የአካል ጉዳት መጠን በተለያዩ መስኮች ይመደባሉ። የዒላማው ርቀትም በየመስኩ የተለያየ ሲሆን አትሌቶች የሚጠቀሟቸው እንደ ተሽከርካሪ ወንበር [ዊልቼይር] እና ሌሎች መሣሪያዎችም ግምት ውስጥ ይገባሉ።
ደብሊው1 በሚባለው ዘርፍ የሚወዳደሩ የቀስት ተወዳዳሪዎች ዊልቸር የሚጠቀሙ ሲሆኑ ከሁለት እጅ እና ሁለት እግር ቢያንስ ቦስቱ ጉዳት ያለባቸው የጡንቻ ጥንካሬ አሊያም የእንቅስቃሴ ውስንነት ያለባቸው ናቸው።
ኦፕን በሚባለው ዘርፍ የሚወዳደሩ ደግሞ በላይኛው አሊያም በታችኛቸው የአካል ክፍል ወይም በአንደኛው ጎናቸው ውሱንነት ያለባቸው ሆነው ዊልቸር የሚጠቀሙ ናቸው። አትሌቶቹ እንደ አስፈላጊነቱ የተለያዩ ቀስቶችን ይጠቀማሉ።
ዴቪ በአሁኑ ወቅት በሴቶች ኦፕን ዘርፍ ከዓለማችን ቁጥር አንድ የቀስት ተወዳዳሪ ተብላ ተመድባለች።
በ2023 በዓለም የፓራ-አርቸሪ የዓለም ሻምፒዮና ሁለተኛ በመወጣት የብር ሜዳሊያ አግኝታ ነው ለፓሪስ ፓራሊምፒክ ውድድር የበቃችው።
ዴቪ በፓሪስ ከዓለም ቁጥር ሶስቷ ጄን ካርላ ጎግል እና ካለፈው ፓራሊምፒክስ የወርድ ሜዳሊያ ባለቤቷ ኦዝኑር ኩሬ ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነገር ግን ዴቪን የሚያውቋት እሷ ለስፖርቱ የተፈጠረች ናት ማሸነፏም አይቀርም ይላሉ።
“ዴቪ አይደለችም የቀስት ውድድርን የመረጠችው፤ የቀስት ውድድር ነው ዴቪን የመረጣት” ይላል ከሁለቱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞቿ አንዱ አብሂላሻ ቻውዳሪ።
አነስ ባለች መንደር ከገበሬ ወላጆቿ የተወለደችው ዴቪ ቀስት ምን እንደሚመስል እስከ 15 ዓመቷ ድረስ አታውቅም ነበር።
ነገር ግን በ2022 ተወልዳ ካደገችበት መንደር 200 ኪሎ ሜትር ርቃ ጃሙ የሚገኝ አንድ የስፖርት ኮምፕሌክስ ውስጥ ከገባች በኋላ ነው ነገሮች መቀየር የጀመሩት።
አሰልጣኞቿ በዴቪ ብቃት እጅግ መደነቃቸውን ይናገራሉ። በዚህ የስፖርት አካዳሚ ሳለች ነው ቻውዳሪ እና ከቀስት ጋር ያስተዋወቃት ሌላኛው አሰልጣኟ ኩልዲፕ ቬድዋንን ያገኘቻቸው። ትንሽ ቆይታ ወደ ካትራ ከተማ ወደ ሚገኝ ሌላ መለማጃ ተዛወረች።
እርግጥ ነው አሰልጣኞቿ ሥራቸው ቀላል አልነበረም። የዴቪን እግር ጠንካራ ማድረግና የላይኛው የሰውነት ክፍሏን ማለማመድ ቀላል ባይሆንም በስተመጨረሻ ተሳካላቸው።
ዴቪ እንደምትለው የእግሯ ጥንካሬ የመጣው ለበርካታ ዓመታት በእጇ ፈንታ እግሯን ለተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመጠቀሟ ሳቢያ ነው። የምትፅፈው፤ ከጓደኞቿ ጋር ዛፍ የምትወጣው በእግሯ አማካይነት ነው።
እንዲያም ሆኖ በቀስት ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገሯን መወከል እንደምትፈልግ ስትናገር ጥርጣሬ የገባቸው ትንሽ አልነበሩም።
“የማይቻል መስሎኝ ነበር። መጀመርያ ላይ እግሬን በጣም ያሳክከኝ ነበር። ነገር ግን ከቆይታ በኋላ ተለማመድኩት” ትላለች።
ዴቪ አንዳንድ ጊዜ ሞራሏ ሲዳከም መነቃቂያዋ የተለየ መሣሪያ በመጠቀም በእግሮቹ ቀስት በመወርወር ታዋቂ የሆነው አሜሪካዊ አትሌት ማት ስቱትዝማን ነው።
የዴቪ ወላጆች ይህንን ማሽን የሚገዙበት አቅም የላቸውም። ይሄኔ ነው አሰልጣኟ ቬድዋን ለሷ የሚሆን ቀስት ለመስራት ቆርጦ የተነሳው። ከአካባቢው በተገኙ ቁሳቁሶች ለሷ የሚሆን መሣሪያ ሰርቶ ሰጣት።

የፎቶው ባለመብት, Abhilasha Chaudhary
ዴቪ በአዲሱ ማሽን ታግዛ ልምምድ በጀመረች በአራተኛው ወር ለውድድር የሚሆን ቀስት መሸከም እና 50 ሜትር ርቀት ላይ ዒላማን አነጣጥራ መጣል ቻለች። 50 ሜትር ኦፕን በሚባለው ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩበት ርቀት ነው።
በሁለት ዓመታት ውስጥ ዴቪ ቀስት መወርወር ከመለማመድ አልፋ በእስያ ፓራ ጨዋታ በሴቶች ውድድር ወርቅ ማግኘት ቻለች። ይህን ያደረገችው 10 ነጥብ የሚያሰጠውን ዒላማ በተከታታይ ስድስት ጊዜ በመምታት ነው።
“9 ነጥብ ሳመጣ እንኳ በሚቀጥለው ዒላማዬ እንዴት አድርጌ ነው 10 ነጥብ ማምጣት የምችለው የሚለው ነው የማስበው” ትላለች።
ዴቪ ይህን ለማሳካት ጠንክራ መሥራት ብቻ ሳይሆን መስዋዕትነትም መክፈል ነበረባት። ዴቪ እንደምትለው ወደ ካትራ ከመጣች ወዲህ ላለፉት 2 ዓመታት አንድም ቀን ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ሄዳ አታውቅም።
አሁን ግን የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ለመሄድ ያቀደችው ዴቪ “ከተሳካልኝ ከወርቅ ሜዳሊያ ጋር” ትላለች።












