በእስራኤል ሙዚየም ጉብኝት ላይ የነበረው ታዳጊ የ3500 ዕድሜ ያለውን ቅርስ ሰበረ

የአራት ዓመት ዕድሜ ባለው ታዳጊ የተሰበረው ቅርስ

የፎቶው ባለመብት, Hecht Museum staff

በእስራኤል ሙዚየሙ ውስጥ የሚገኝና የ3ሺህ 500 ዓመት ዕድሜ እንዳለው የተነገረ ማድጋ በአራት ዓመት ሕጻን ጎብኚ ድንገት መሰባበሩ ተዘገበ።

በሰሜን እስራኤል ሀይፋ የሚገኘው ሔቼት ሙዚየም ለቢቢሲ፣ ይህ የውሃ መያዣ እንስራ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2200 እና በ1500 ዓመተ ዓለም በመዳብ ዘመን ጥቅም ላይ ይውል የነበረ እና ምንም ጉዳት ሳይደርስበት የተገኘ ብርቅዬ ቅርስ ነበር ብሏል።

ሙዚየሙ የቅርስ ግኝቶችን “ያለ ክልከላ እና ገደብ” ለዕይታ ማቅረብ “የተለየ መስህብ” ይኖረዋል በሚል ከመስታወት ውጪ የሙዚየሙ መግብያ በር አካባቢ ተቀምጦ ነበር ብሏል።

የሕጻኑ አባት አሌክስ እንዳለው ከሆነ፣ ልጁ “ማድጋውን ቀስ አድርጎ ጎትቷል”። ምክንያቱ ደግሞ “ውስጡ ምን አለ ከሚል ጉጉት” ሲሆን ይህም አንዲወድቅ አድርጎታል።

አሌክስ አክሎም ልጁን ከተሰበረው ማድጋ ጎን መመልከቱ “ድንጋጤ” ፈጥሮበት እንደነበር ገልጾ፣ በመጀመርያ “የኔ ልጅ አይደለም የሰበረው” ብሎ ማሰቡን አልሸሸገም።

ይኹን አንጂ ልጁን ካረጋጋ በኋላ በአካባቢው ለሚገኝ ጥበቃ የተፈጠረውን ማስረዳቱን አሌክስ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የሙዚየሙ ባልደረባ የሆኑት ሊሂ ላስዝሎ “ለዕይታ የሚቀርቡ ቅርሶች ሆን ተብለው እንዲወድሙ የሚደረግበት አጋጣሚ አለ። እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ፖሊስ ጉዳዩን አንዲይዘው ተደርጎ በተለየ ሁኔታ ነው የሚስተናገዱት” ብለዋል።

“ይኹን እንጅ ይህ አጋጣሚ ሆን ተብሎ የተደረገ አይደለም። ሙዚየሙን እየጎበኘ በነበረ ሕጻን ልጅ በድንገት የደረሰ አደጋ ነው። እኛም የምንሰጠው ምላሽ በዚያው ልክ ይሆናል።” ሲሉ አብራርተዋል።

ሔቸት ሙዚየም እንዳለው ይህ አደጋ ከተፈጠረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሕጻኑን እና ቤተሰቡን ዳግም ወደ ሙዚየሙ በመጋበዝ በድጋሚ ቅርሳ ቅርሶቹን እንዲጎበኙ አድርገዋቸዋል።

እንስራውን ወደ ነበረበት ለመመለስም በቅርስ ጥበቃ የተካኑ ባለሙያዎች እንደሚጥሩ እና “በአጭር ጊዜ ውስጥ” ወደ ነበረበት ቦታ ተመልሶ ለዕይታ እንደሚበቃ ተነግሯል።

የሕጻኑ አባት አሌክስ ማድጋው ተጠግኖ ቢመለከቱ “ከጭንቀት አንደሚላቀቅ” ገልጾ “ተመልሶ እንደ ቀደመው ባለመሆኑ ግን አዝናለሁ” ብሏል።

ማድጋው የሙዚየሙ መግብያ ላይ ያለ ምንም መከላከያ ለዕይታ ተቀምጦ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Hecht Museum staff

ሙዚየሙ ለቢቢሲ እንዳስረዳው “ አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት ቅርሳ ቅርሶች ያለ መስታወት ግድግዳ ወይንም መከላከያ ለዕይታ የሚቀርቡበት አጋጣሚ አለ።”

እናም “ከእንዲህ ዓይነቱ አልፎ አልፎ ከሚገጥም አደጋ ውጪ” ይህንን የሙዚየሙን አሰራር እንደሚቀጥሉበት አስታውቀዋል።

ማድጋው በጥንት ዘመን ወይን ወይም የወይራ ዘይት ለመያዝ ያገለግል ነበር ተብሎ ይገመታል።

ይህ ማድጋ በመጽሐፍ ቅዱሱ ንጉሥ ዳዊት እና ንጉሥ ሠለሞን አገዛዝ ዘመን መካከል ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ነው ተብሎ የሚገመት ሲሆን የምሥራቅያዊ ሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ ከተማ የከንዓን አካባቢ ቁሳቁስ ነው ተብሎ ይታመናል።

የመካነ ቅርስ ባለሙያዎች በቁፋሮ ያገኟቸው ተመሳሳይ ከሸክላ የተሰሩ ቁሳቁሶች በቁፋሮ ወቅት ተሰብረው አልያም ሙሉ ሳይሆኑ እንደሚገኙ እና ይህ ቅርስ ግን ምንም ሳይሆን መገኘቱ “አስደናቂ ግኝት” አድርጎት ነበር ብሏል ሙዚየሙ።

ሔቸት ሙዚየም በሰሜን እስራኤል በሀይፋ ዩኒቨርስቲ የሚገኝ ሲሆን በቁፋሮ የተገኙ ቅርሳ ቅርሶችን እና የስነ ጥበብ ውጡቶችን ይሰበስባል።