በቀን ስንት ስኒ ቡና መጠጣት ይመከራል? ለምን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም እንደ ቡና ተወዳጅና ተዘውታሪ መጠጥ አለ?
ቡና ካፊን አለው። ስለዚህ ያነቃቃል። ቀናችንን ያበራዋል። ፍክትክት ያደርገናል።
አንዳንዶች አንድ ስኒ ቡና ፉት ካላልኩ ዐይኔ አይገለጥልኝም ይላሉ። አደጋ ላይ ናቸው ማለት ነው?
ሌሎች ደግሞ ቡና ሱስ ያመጣል። ሱስ ደግሞ የጤና ጠንቅ ነው ብለው ይደመድማሉ። ልክ ናቸው?
ሳይንስ ምርምሩን እንደቀጠለ ነው። ቡና ለጤና ጥሩ ነው ከሚሉ ውጤቶች ባሻገር አደጋም አለው የሚሉ ጥናቶች ባለፉት ዐመታት በብዙ ታትመዋል።
ለመሆኑ ካፊን ያላቸው ቡናና ሌሎች አነቃቂ መጠጦችን በምን መጠን ነው መውሰድ የሚመከረው የሚለው የጤና ሳይንስን ዘወትር እንዳነጋገረ ነው።
በቅርቡ አንድ እውቅ የአሜሪካ 'ለመኔድ' አቅራቢ ሥራ አቁሟል። ምክንያቱ ደግሞ ለመኔዱ ውስጥ የሚጨመረው የካፊን መጠን አሳሳቢ ሆኖ በመገኘቱ ነው።
የካፊን መጠጦች አሳሳቢ ሊሆኑብን ይገባል?
ብዙ ካፊን ሰውነታችንን ምን ያደርገዋል?
ሰውነታችን ፋብሪካ ነው። ሁልጊዜ በሥራ የተጠመደ ነው። የልብ ምት፣ የደም ዝውውር፣ የእንቅልፍ መተኛትና መነሳት ወዘተረፈ።
ይህ የሰውነት እንቅስቃሴ አዲኖሲን በሚባል ኬሚካል ይወሰናል።
ምንድነው ደግሞ አዲኖሲን?
በተፈጥሮ ሰውነታችን የሚያመርተው ኬሚካል ነው። ይህ ኬሚካል ሰውነታችን ባተሌ ሆኖ ከዋለ በኋላ ድካም እንዲሰማው የሚያደርግ እጅግ አስፈላጊ ኬሚካል ነው። እሱ ባይኖር ሰውነታችን ዝሎ ከጥቅም ውጭ ይሆን ነበር።
ኬኔት ጃኮፕሰን ሳይንቲስት ናቸው። ''ብዙ ሥራ የበዛበት የሰውነታችን ክፍል ድካም እንዲሰማውና እረፍት እንዲያደርግ ይህ ኬሚካል ወሳኝ ሚና አለው'' ይላሉ።
አዶኒሴን ኬሚካል በሴሎቻችን በላይኛው ክፍል ተነጥፎ የሚገኝ ነው። ልክ በዚያ አካባቢ ያለ ሴል ብዙ ሠርቶ ጉልበቱ ብርክ ሲይዘው ''ስማኝ አንተ ሴል ሆይ! ደክሞሃል በቃህ'' የሚል መልእክት ይልክለታል። ወይም ደግሞ ተፍ-ተፍ ማለትህን ቀንስ ብሎ ያስጠነቅቀዋል።
ይህ ደግሞ እንደ ልብ ምት፣ ኩላሊት፣ የበሽታ ተከላካይ የሴል ሠራዊት ሥራ ሳይቀር እንዲረጋጋ ያደርጋል። ካልተረጋጋ ይዳከማል፣ ይዝላል። ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ሰውነታችን ልክ እንደመኪና ነው። የሚነዳበት ልክ አለው።
አሁን ወደ ካፊን እንምጣ።
ቡናን ጨምሮ ማንኛውንም ካፊን ስንወስድ የካፊን ጭማቂው በፍጥነት ወደ ደም ትቦ ይዘልቃል።
ከዚያ ከአዴኖሲን ጋር ግብግብ ይገጥማል። ካፊን ያሸንፋል።
ካፊኑ ምን ያደርጋል? አድኖሲን ኬሚካል ከሴል ጫፎች ጋር ግንኙነት እንዳያደርግ ይከለክለዋል።
ከዚያ ሰውነታችን መድከሙን ይረሳል። የሚነግረው የለማ። ደክመሃል ብሎ የሚነግረው ኬሚካል ዝም እንዲል ተደረገ።
በዚህ የተነሳ ነው ካፊን ድካምን ''ወዲያ ዞር በል'' የሚለው። ይህ ማለት ግን ሰውነታችን አልደከመም ማለት ነው እንዴ?
ካፊን ስንወስድ የዶፓሚን እና የአድሬናሊን መጠናችንን ሰማይ ይሰቅለዋል። ዶፓሚን እና አድሬናሊን ደግሞ ኒውሮትራንስሚተሮች ናቸው። የነርቭ ኬብሎች እንበላቸው። ካፊን ስናገኝ ከየት እንደመጣ የማናውቀው መነቃቃት ሰውነታችንን ይወረዋል።
“አንጎላችን ትልቅ ጡንቻ ማለት ነው። ሥራው በአግባቡ እንዲሠራ መነቃቃትን ይፈልጋል። ዶፓሚን፣ አደርናሊንና ካፊን ደግሞ በአያሌው ያነቃቁታል” ይላሉ ፕሮፌሰር ዳሚየን ቤይሌይ። ፕሬፌሰር ዳሚየን በሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርስቲ የፊዚዮሎጂ መምህር ናቸው።
የካፊን የጤና ትሩፋቶች
ካፊን ለጤና በጎ ሚናን ይጫወታል። በተለይ ቡና ለሰውነታችን ጤና መልካም እንደሆነ ብዙ ጥናት አመላክቷል።
ወደ 200 ጥናቶች ተነባብረው የመሰከሩት አንድ ሐቅ ቢኖር በቀን እስከ ሦስት ቡና ስኒ መጠጣት የጤና በረከት ነው እንጂ መርገም አይደለም።
አንድ በ19ሺህ ሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት ግን ከ2 ስኒ ቡና በላይ በቀን መጠጣት በልብ ሕመም ለመሞት ዕድል እንደሚጨምር አመላክቷል። ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው ሰዎቹ መጀመርያውኑ የደም ግፊት ያለባቸው ከሆኑ ነው።
ቡና ጤናማ ሰዎች ላይ የልብ ሕመም እንደማያመጣ ጥናቱ አመላክቷል። በዚሁ ጥናት ከሻይ ይልቅ ቡና የድብታ ስሜትን እንደሚያጠፋም ተደርሶበታል።
ሌሎች ጥናቶች ደግሞ የካንሰር የልብና የስኳር ሕመሞችን በተመለከተ መጠነኛ ቡና መጠጣት መጠነኛ የመከላከል ሥራ እንደመሥራት ነው ብለዋል።
በሌላ ቋንቋ ቡና ለነዚህ በሽታዎች ተጋላጭነትን ይቀንሳል ማለት ነው።
መጠነኛ ቡና ፉት ማለት ለአልዛሚር እና ዲሜንሺያ (የዝንጋታ ደዌዎች) መጋለጥን በስሱ ይቀንሳል።
አንድ ጥናት እንዲያውም ቡና በአልዛሚር ከመጠቃት በ60 % ተጋላጭነት ይቀንሳል ብሏል።
አንጎላችን የጠቅላላ የሰውነታችን 2% ክብደት ቢኖረውም የሚያቃጥለው ኃይል ግን ከባድ ነው። ቡና ስንጠጣ ታዲያ አንጎላችንን ሥራ እናቀልለታለን። መጠነኛ ካፊን ወደ አንጎል የሚፈሰውን የደም ዝውውር ያሳልጣል።
“ምንም እንኳ ብና ለአንጎል የደም ዝውውር መሳለጥ አስተዋጽኦ ቢኖረውም ከፍተኛ ራስ ምታትና ማይግሪን ላለባቸው ሰዎች ካፊኑ ሲበዛ የበለጠ ይቀሰቅስባቸዋል።
ሌላው መረዳት ያለብን የቡና የጤና ትሩፋቶች ሁሉ በቡና ውስጥ ከሚገኝ ካፊን የመጡ አለመሆናቸው ነው።
ለምሳሌ በቡና ውስጥ ያለው ክሎሮጄኒክ አሲድ ለጤና በረከቶች ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ይላሉ ተመራማሪዎች። በተለይ የስኳር ተጋላጭነትን ለመቀነስ።
"በርካታ ጥናቶች ቡና ለስኳር በሽታ በጎ ሚና እንዳለው አሳይተዋል። ነገር ግን ይህ ሚናው ካፊኑ በወጣለት ቡና (ዲካፍ) ውስጥም አለ። ይህ የሚያሳየው በረከቱ በካፊኑ ውስጥ ብቻ አለመሆኑን ነው የሚነግረን” ይላሉ እኒህ ተመራማሪ።
የተቆላ ቡና፣ ወይም ደግሞ የተፈጨ አልያም በተለያየ መልኩ የሚሰናዳ ቡና ውጤቱም በዚያው መጠን ይለያያል።
ለምሳሌ ካፊን የተጨመረባቸው መጠጦች በሰውነታችን የሚያመነጩት አንድ አይነት ነገር ነው ማለት አይደለም።
የተቆላ ቡና አንቲኦክሲደንት እና አንቲ ኢንፈላማቶሪ (ጸረ-ብግነት) ሆነው ተገኝተዋል።
ከማሽን ተሰናድቶ ያለቀለት ቡና ፊልተር ደግሞ ሌላ መልክና ውጤት አለው። ነጥቡ ሁሉም ካፊን በሰውነታችን ውስጥ የሚኖረው ሚና አንድ አይደለም ለማለት ነው።
ሁሉም ካፊን አንድ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Image
ቡና ዋናው የካፊን አባት ቢሆንም ሻይም ቀላል አይደለም። ለምሳሌ በደንብ የፈላ ጥቁርና አረንጓዴ ሻይ ከቡና የበለጠ ካፊን ሊኖረው ይችላል።
“አንዳንዴ ከቡና ይልቅ ሻይ መጠጣት የተሻለ የጤና ትሩፋት ሊኖረው ይችላል” የሚባለውም ለዚሁ ነው ይላሉ ተመራማሪዎች።
በግማሽ ሚሊዯን ቡና ጠጪዎች፣ ለ20 ዓመታት የተሠራ አንድ ጥናት ያመላከተው ነገር አለ። ተቀሽሮ፣ ተፈጭቶ፣ ተቆልቶ የሚሠራ የተጣራ ቡና የሚጠጡ ሰዎች፣ ሌላ ዓይነት ካፊን ከሚጠጡት ጋር ሲነጻጸሩ ከልብ ቧንቧ ጋር የተያያዙ በሽታዎች ተጋላጭነታቸው ቀንሶ ተገኝቷል።
ካፊን የያዙ ጉልበት ሰጪ መጠጦች (Energy drinks) በአንጻሩ በርካታ የሰውነት አካላትን እንደሚያስቆጡ ተደርሶበታል።
የጉልበት ሰጪ መጠጦች በስፖርተኞች የሚዘወተሩ ናቸው።
ቡና መቼ መጠጣት ነው ጥሩ?
ቡናን ጠዋት ጠጣነው ወይ ደግሞ አታካች ስብሰባ ላይ በኩባያ ይዘነው ገብተን ጨለጥነው ቦታና ጊዜው ለውጥ ያመጣል?
ጥሩ የሚባል የቡና መጠጫ የቀኑ ክፍለ ጊዜ የቱ ነው?
ተመራማሪዎች ቡና ሰውነት ውስጥ የደም ስሮች ውስጥ ለመግባት 20 ደቂቃ ይፈልጋል ይላሉ። መነቃቃቱ ሰማይ የሚነካው ደግሞ ከ60 ደቂቃ በኋላ ነው ብለዋል።
በዚህ ምክንያት ስፖርት ለሚሠሩ ሰዎች ማዘውተሪያ ከመግባታቸው ከአንድ ሰዓት በፊት ቢወስዱ ይመከራል። ጡንቻ በደንብ እንዲነቃቃ፣ ለድካም እጅ እንዳንሰጥ የሚያደርገው ከ60 ደቂቃ በኋላ ስለሆነ ነው።
ጠዋት ከእንቅልፍ እንደነቁ ቡና ፉት ማለት በፍጹም አይመከርም። ተመራማሪዎች ከእንቅልፍ ከነቃን ከ90 ደቂቃ እስከ 2 ሰዓት መጠበቅ መልካም ነው ይላሉ። ለምን?
ከእንቅልፍ በነቃን በአንድ ሰዓት ውስጥ አዲኖሲን ኬሚካል ከሴሎቻችን ላይ ገለል ይላል። ምክንያቱም የድካም መልእክት አስተላላፊ ኬሚካል አይደል? ሰውነታችን እረፍት ስላደረገ ነው ገለል የሚለው።
ይህ ደግሞ ሴሎቻችን ካፊንን ለመቀበል ዝግጁ ያደርጋቸዋል። አዲኖሲን የድካም ኬሚካል መሆኑን ልብ ይሏል።
ሌሎች ተመራማሪዎች ግን ይህን አይቀበሉም። ሁለቱ ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም ይላሉ።
ይሁንና ካፊን ከአንጀታችን ሙሉ በሙሉ ገለል ለማለት ሰዓታት እንደሚፈልግ ተደርሶበታል።
ታዲያ አንድ ሰው የቀኑን የመጨረሻውን ቡና ፉት ቢል የሚመረጠው ወደ እንቅልፍ ከመሄዱ 8 ሰዓት ገደማ በፊት ነው።
ጠዋት ደግሞ ከነቃን በኋላ ረፈድፈድ አድርገን ቢሆን ይመከራል።
ቡና የማይመከረው ለማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካና የዩኬ ብሔራዊ የጤና ማእከላት ካፊን በተለይ ለእርጉዝ ሴት በቀን 200 ግራም በላይ መሆን የለበትም ይላሉ።
በቅርብ ጊዜ ከተደረጉ 37 ጥናቶች 32 የሚሆኑት ቡና በእርግዝና ወቅት ባይጠጣ ይመክራሉ። ለምን ሲባሉ ለጽንሱ ጤናማ እድገት ጥሩ ስላልሆነ የሚል መልስ አላቸው።
ካፊን በቀላሉ ፕላሴንታ/ placenta/ (ከእናት ወደ ልጅ ምግብ የሚያመላልስ ድልድይ ወይም መጋቢ ሽል) በቀላሉ ያልፋል።
እናት የምትጠጣው ቡና ወደ ጽንስ ለመጓዝ ደቂቃ የማይወስድበትን ለዚያ ነው። የፕላሴንታ ድልድይ ከፊኑን ለማስቆም የትራፊክ መብራት የለውም።
አንዳንድ ጥናቶች እንዲያውም የበዛ ካፊን የምትጠጣ ነፍሰ ጡር ለውርጃ አልያም ለጽንስ ሞት የመጋለጥ እድሏ ከፍ ይላል ብለው ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
የምታጠባ ሴትም ካፊን መውሰዷ በእናት ጡት በኩል ወደ ልጁ ሊሄድ ይችላል ይላሉ ፕሮፌሰር ጃክ ጀምስ። ፕሮፌሰር ጃክ በአይስላንድ ሬይክጃቪክ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው።
ስለዚህ እርጉዝ ሴት ቡና ባታበዛ የሚል ጠንከር ያለ ምክር አለ።
ሌላው ደግሞ ካፊን ለእንቅልፍ ጠንቅ መሆኑ ነው።
ካፊን ያበዙ ሰዎች ሱሰኛ ይሆኑና ለማቆም በሚሞክሩበት ጊዜ ለከፍተኛ የጤና ቀውስ ይጋለጣሉ።
አንድ ሱሰኛ ቡና ባቆመ በ6 ሰዓታት ውስጥ ቀውስ ውስጥ ይገባል። ይህ ማለት ራስ ምታት፣ መነጫነጭ፣ ድብታን ይጨምራል።
ይህ ማለት በምታጠባ እናት የቡና ሱሰኛ መሆን በሚጠባው ልጅም ተመሳሳይ ስሜት ሊያደርበት ይችላል።
“ካፊን የእንቅልፍ ምስቅልቅል ወይም የእንቅልፍ መጣት ብቻ አይደለም የሚያሰከትለው። የምንተኛውን እንቅልፍ ጥራትም ይቀንሳል” ይላሉ አንድ ተመራማሪ።
በቀን 3 ስኒ ቡና ብዙ ነው?
በዩኬ ይህ ነው የሚባል የተቀመጠ ቁጥር የለም።
የአውሮፓ የምግብና ጤና ባለሥልጣን ግን አንድ አዋቂ ሰው 400 ሚሊ ግራም ካፊን በላይ በቀን ውስጥ መጠጣት የለበትም ይላል።
በአንድ ጊዜ ከሆነ ደግሞ ከ200 ሚሊ ግራም በላይ መጠጣት አይመክርም።
ትልቁ ችግር ታዲያ በምንጠጣቸው መልከ ብዙ የካፊን መጠጦች ስንት ሚሊ ግራም ካፊን እንዳለባቸው ማወቅ አለማላችን ነው።
በአንድ ስኒ ቡና 100 ሚሊ ግራም ካፊን አለ ተብሎ ይገመታል። 400 ሚሊ ግራም ማለት ደግሞ 4 ስኒ ማለት ነው።
ለምሳሌ ኢስፕሬሶ፥ ወይም ማኪያቶ ወይም ሌላ መጠጥ ካፊን አላቸው። መጠናቸው ግን ይለያያል። ያንን የካፌ ባሬስታዎች አይነግሩንም። ስለዚህ በቀን ምን ያህል ካፊን ወደ ሰውነታችን እንደገባ አናውቅም።
ለምሳሌ ጢኒጧ ኢስፕሬሶ ከ250 ሚሊ ግራም እስከ 700 ሚሊ ግራም ካፊን ትይዛለች። አንዳንድ የጉልበት ሰጪ ትልልቅ መጠጦች ደግሞ እስከ 600 ሚሊ ግራም ብቻ ይይዛሉ።
በዚህ የተነሳ ብዙ ሰው በቀን የወሰደውን የካፊን መጠን አያውቅም።
አንዳንዴ መጠናችንን ማለፋችንን የምናውቀው በምናሳየው ባህሪ ሊሆን ይችላል። ልባችን በፍጥነት ሲመታ፣ ወይ ደግሞ በቂ ሳንጠጣ ቀርተን መነጫነጭ ስንጀምር ወይ ደግሞ ራስ ምታት ሲወቅረን።
በደምሳሳው ግን ተመራማሪዎች በቀን ከ2 እስከ 3 ስኒ ቡና በቂ ነው ይላሉ።
የመጨረሻው ምክር ማቆም ለሚፈልጉ ነው።
ጨርሶውኑ ካፊን መውሰድ ለማቆም ስንወስን በአንድ ጊዜ ማቆም ጉዳት አለው። ባለሙያዎች የሚመክሩት ቀስ በቀስ እንድናቆም ነው።
ለምሳሌ ላለፉት 6 ዓመታት በቀን 6 ስኒ ቡና የሚጠጣ ሰው፣ ማቆም ከፈለገ በመጀመርያው ሳምንት መጠኑን ወደ 4 ቡና ዝቅ ያድርግ፤ ቀጥሎ በቀን ወደ 2 ስኒ ቡና ያውርደው፤ እንዲያ እያለ ጨርሶውኑ ማቆም ይችላል።
ይህ ሱስን በአንድ ጊዜ ማቆም ከሚያመጣው መዘዝ (withdrawal symptoms) ይከላከላል ነው የሚሉን፤ አዋቂዎች፣ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች።
ይህ ረዥም ዘገባ ራሱ በቡና አጋዥነት የተጻፈ ሳይሆን አይቅርም።












