አቶ ጌታቸው ረዳ ተፈናቃዮች ላሉበት ችግር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተጠያቂ ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Tigray TV
በትግራይ ክልል በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው በችግር ላይ ባሉ ሰዎች ሁኔታ ውስጥ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አንዱ ተጠያቂ መሆኑን ገለጸ።
የአስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በሺዎች የሚቆጠሩ በትግራይ ክልል የሚገኙ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በመቀለ ከተማ ያደረጉትን ሰልፍ ተከትሎ ነው ይህንን የተናገሩት።
በክልሉ መዲና ሰልፍ የወጡት ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያች እንዲመለሱ እና ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
በክልሉ መሰል ሰልፍ ሲደርግ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ለሰልፈኞች ባሰሙት ንግግር ተፈናቃዮቹ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ላለመለሳቸው “አንዱ ተጠያቂ አስተዳደራቸው እንደሆነ” አምነዋል።
“እዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የወደቃችሁት ሥራችንን መሥራት ስላልቻልን ነው” በማለት አቶ ጌታቸው አስተዳደራቸው የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወስድ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለው ተፈናቃዮቹ በቅርቡ ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንደሚመለሱ ቃል ገብተዋል።
ኅዳር 2014 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በተለይ ከምዕራብ ትግራይ እንደተፈናቀሉ ይነገራል።
በምዕራብ ትግራይ እና በተወሰኑ የክልሉ ምዕራባዊ ክፍሎች የሚገኙ ነዋሪዎች በአማራ ክልል በሚገኙ ታጣቂዎች ከሥፍራው እንደተፈናቀሉ ይናገራል።
አማራ ክልል በትግራይ ክልል የሚገኘው ምዕራባዊ ክፍል ይገባኛል የሚል ጥያቄ ያነሳል።
ሰልፈኞቹ ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለስ እንዲችሉ እና ፈጣን የሆነ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Tigray TV
“በረሃብ ልናልቅ ነው”
ከሰልፉ አዘጋጆች አንዱ የሆነው ተፈናቃዩ ብርሃነ ኃይላይ “የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ሆነን መኖር” በቃን ይላል።
“እያልን ያለነው የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ሆነን መኖር አንችልም ነው። ወደቤታችን መልሱን። የፕሪቶሪያው ስምምነት ሊፈፀም ይገባል ነው።”
ለተፈናቃዮቹ እየቀረበ ያለው ሰብዓዊ እርዳታ እየተቆራረጠ እንደሆነም የሚናገረው ብርሃነ “በረሃብ ልናልቅ ነው” ይላል።
ክልላዊው የትግራይ ቴሌቪዥን በቃሬዛ ሆነው በሰልፉ የተሳተፉ ሰዎችን ፎቶ ግራፍ በፌስቡክ ገጹ አስመልክቷል።
አዘጋጆቹ እንደሚሉት እኒህ ሰዎች በምግብ እጦት እና በሕክምና እርዳታ አለማግኘት ምክንያት ቆመው መሄዳ ያቃታቸው ሰዎች ናቸው።
ሌላኛው የሰልፉ ተሳታፊ የሆነው አሸብር ሀገዞም ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅሎ ከመጣ በኋላ በመቀለ ከተማ አነስተኛ ዳስ ጥሎ ነው የሚኖረው።
እሱ እንደሚለው ለጨመረሻ ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ የደረሳቸው ከ10 ወራት በፊት ነው።
“በጣም ርቦናል። ሕመም ላይ ነን። እርዳታ ያስፈልገናል። ለመጨረሻ ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ የደረሰን ባለፈው ሚያዝያ ነው። በተስፋ ነው እየኖርን ያለነው።”
“ቀስ በቀስ ወደ ሬሳነት እየተቀየርን ነው። በየቀኑ ሰዎች እየሞቱ ነው” ብሏል።
ብርሃነ እንደሚለው ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ በመጠለያ የነበሩ 39 ሰዎች በረሃብ እና በሕክምና እጦት ምክንያት ሞተዋል።
ሁለት ዓመት የፈጀው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቆም ምክንያት የሆነው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆንም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ከመቅጠፉ እና ንብረት ከማውደሙ በተጨማሪ በጦርነቱ የሰብዓዊ መብት ተፈጽሟል፤ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
በተለይ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳበት ምዕራብ ትግራይ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ከአካባቢው በኃይል እንዲወጡ መደረጋቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቡድኖቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት አድርገው ነበር።
ማዕከላዊው መንግሥት የይገባኛል ጥያቄ በሚነሱባቸው አካባቢዎች ሕዝበ-ውሳኔ ከመካሄዱ በፊት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ ቢልም እስካሁን ይህ አልሆነም።
የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ ያለው ህወሓት፤ የክልሉ ነዋሪዎች በረሃብ እና በድርቅ ምክንያት አደጋ ላይ እያሉ እያካሄደ ያለው ስብሰባ የፓርቲውን ውስጣዊ ችግር ለመፍታት ነው በሚል ወቀሳ እየደረሰበት ይገኛል።












