ቀይ ባሕር ላይ በሁቲ ታጣቂዎች የተመታችው የግሪክ መርከብ በውሃ መጥለቅለቋ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, EPA-EEE/REX/Shutterstock
ባለቤትነቷ የግሪክ የሆነች መርከብ የቀይ ባሕርን ስታቋርጥ በየመን ሁቲ አማጽያን በሰው አልባ የጦር ጀልባ በተፈጸመባት ጥቃት በውሃ ክፉኛ እንደተጥለቀለቀች እና የሞተር ክፍሏ እንደተጎዳ አሜሪካ ገልጻለች።
የዩናየትድ ኪንግደም ንጉሣዊ ባሕር ኃይል የማሪታየም ንግድ ጽህፈት ቤት የሁቲ አማጽያን ከተቆጣጠሩት የሆዴይዳ ወደብ ደቡባዊ ምዕራብ አቅጣጫ አንዲት መርከብ ከበስተጀርባዋ ጥቃት እንደደረሰባት ጥቆማ ደርሶኛል ብሏል።
መርከቧ ውስጥ ውሃ ዘልቆ እንደገባ እና ክስተቱም ከቁጥጥር ውጪ እንደሆነ ጽህፈት ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።
በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያን ለጥቃቱ ኃላፊነት ወስደዋል። የላይበሪያ ሰንደቅ ዓላማን ስታውለበልብ የነበረችው ቱቶር የተሰኘችውን መርከብ የባሕር ድሮን በመጠቀም ጥቃት እንደፈጸሙባት አስታውቋል።
የሁቲ አማጽያን በጋዛ ለሚገኙ ፍልስጤማውያ ድጋፋቸውን በመግለጽ በቀይ ባሕር የሚጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ይገኛሉ። ይህ ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ እያስተጎጎለ ነው።
የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ መርከቧ ላይ ጥቃት ለማድረስ አማጺ ኃይሉ ሰው አልባ የጦር ጀት፣ በርካታ ድሮኖች እና ባለስቲክ ሚሳኤል እንደተጠቀመ ገልጸዋል።
የአማጺ ቡድኑ ቃል አቀባይ ጨምሮም በጥቃቱ መርከቧ ክፉኛ እንተጎዳች እና የመስመጥ አደጋ እንደተጋረጠባት አመልክተዋል።
መግለጫው መርከቡ የጥቃት ኢላማ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዳ “የመርከቡ ባለቤት የሆነው ኩባንያ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ወዳለው የፍልስጤም ወደቦች መሸጋገር የሚከለክለውን ትዕዛዝ በመጣሱ ነው” ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በኢራን የሚደገፉት አማጽያን ጥቃቱን ለማድረስ የተጠቀሙበት ሰው አልባ ጀልባ በቅርቡ ሩሲያ ውስጥ የተገጣጠመ ነው ሲል ገልጿል።
ዕዙ በኤክስ ገጹ ባወጣው መገለጫ ጥቃቱ በመርከቧ ላይ “ከፍተኛ የውሃ መጥለቅለቅ” እንዳስከተለ እና የሞተር ክፍሏንም እንደጎዳው አመልክቷል።
ጨምሮም ባለፉት 24 ሰዓታት ሁቲዎች ከሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች የተተኮሱ ሚሳኤሎች እና አንድ ድሮን “በተሰካ ሁኔታ” ማውደሙን አስታውቋል።
ይህ የአማጺ ቡድኑ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ እየፈጸመ ያለው “ኃላፊነት የጎደለው”ተግባር ቀጠናው እንዳይረጋጋ እና የባሕረኞች ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል ሲልም አክሏል።
አማጺው ሁቲ ራሱን በኢራን የሚመራው የእስራኤል፣ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ተቃዋሚ ንቅናቄ አካል አድርጎ የሚቆጥር ሲሆን፣ በጋዛ ሰርጥ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን ያለውን ድጋፍ አውጇል።
ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ የሁቲ አማጺያን ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ያሏቸው መርከቦች ላይ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ። ይህንንም የሚያደርጉት ለፍልስጤም ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
በምላሹ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሁቲ ኃይሎችን ኢላማ በማድረግ የመን ውስጥ ተከታታይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል። በአጸፋው የሁቲ አማጽያን ከእነዚህ አገራት ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሌሎች አገራት መርከቦችን ኢላማ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህ የአማጺያኑ ጥቃት በርካታ የመርከብ ድርጅቶች በዓለም የባሕር ንግድ ውስጥ 12 በመቶ ድርሻ ያለውን የየቀይ ባሕር መስመርን እንዳይጠቀሙ እያስገደዳቸው ነው።
በሌላ ዜና የመንግሥታቱ ድርጅት ሁቲ ሁለት ተጨማሪ ሠራተኞቹን በየመን እንዳሰረበት ገልጿል። ቡድኑ ባለፈው ሳምንት 11 የተመድ ሠራተኞችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ተገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከታሳሪዎቹ መካከል አንድ ሠራተኛው እንደሚገኝ ገልጿል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክትር ቴድሮስ አድሃኖም በኤክስ ገጻቸው ሁኔታው እጅግ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።








