እስራኤል ውስጥ በኤርትራውያን መካከል በተከሰተ ግጭት አንድ ሰው በስለት ተወግቶ ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Israel Police Spokesperson
በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ በኤርትራውያን መካከል በተከሰተ ግጭት አንድ ሰው በስለት ተወግቶ ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ ገለጸ።
ከትናንት በሰቲያ ሰኞ ግንቦት 19/2016 ዓ.ም. ጎራ በለየ እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኤርትራውያን በተሳተፉበት ግጭት ከሞተው አንድ ሰው በተጨማሪ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የእስራኤል ፖሊስ አስታውቋል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱን የአምቡላንስ አገልግሎትን በመጥቀስ በግጭቱ ቢያንስ ስምንት ሰዎች ተጎድተው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ብለዋል።
ፖሊስ በግድያ ወንጀሉ የጠረጠረን አንድ ኤርትራዊ ግለሰብን ጨምሮ 20 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ይፋ አድርጓል።
ኤርትራውያንን በሁለት ጎራ የከፈለ ግጭት ሲከሰት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደም በእስራኤል፣ በተለያዩ የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ከተሞች በኤርትራውያን መካከል ግጭት ሲያጋጥም ቆይቷል።
ከጥቂት ቀናት በፊትም በዩናይትድ ኪንግደም ሼፊልድ ከተማ በሁለት ጎራ በተከፈሉ ኤርትራውያን መካከል ግጭት ተከስቶ የአገሪቱ ፖሊስ 25 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
ቅዳሜ ግንቦት 17/2016 ዓ.ም. በነበረው ግጭት 20 ሰዎች የተጎዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታውቋል።
ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በሼፊልድ በነበረውን ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንዶች በዱላ ሲደባደቡ እና ድንጋይ ሲወራወሩ አሳይተዋል።

ከዚህ ቀደም ከነበሩ ግጭቶች መካከል ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ በእስራኤል ቴል አቪቭ የተከሰተው ሁከት ከፍተኛ ጉዳት እና የንብረት ውድመት ያስከተለ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. ኤርትራውያኑ ከባድ ሁከት ፈጥረው በፖሊስ እና በንብረት ላይ ጉዳት ካደረሱ በኋላ አፍሪካውያን ስደተኞችን በሙሉ ‘በአስቸኳይ’ ከእስራኤል ለማባረር ዕቅድ እንዲወጣ ትዕዛዝ እስከመስጠት ደርሰው ነበር።
ኤርትራውያንን ጨምሮ በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች በግብፅ በኩል ድንበር በማቋረጥ እስራኤል ገብተው ይኖራሉ። እነዚህ ስደተኞች እስራኤል በበረሃማው ድንበር ላይ አጥር ከመገንባቷ በፊት ወደ አገር የገቡ ናቸው።
በ2015 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ ከኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅት ጋር በተያያዘ በቴል አቪቭ፣ ስቱትጋርት፣ ስቶክሆልም፣ ለንደን፣ ዘ ሄግ እና ቶሮንቶ ግጭት ካስተናገዱ ከተሞች መካከል ይገኙበታል።
ባለፉት ወራት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በኤርትራውያን ማኅብረሰብ አባላት የተዘጋጁ ፌስቲቫሎች በተደራጁ ቡድኖች ሲታወኩ ይስተዋላሉ።
የባሕል ፌስቲቫሉን የሚቃወሙ ኤርትራውያን ሥነ ሥርዓቱ “ለአምባገነኑ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት” ገንዘብ ማሰባሰቢያ ነው ይላሉ።















