“ማስፈራራቱ ሊቆም ይገባል” ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸው የታወጀው ዊሊያም ሩቶ ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ ውጤቱን ውድቅ ካደረጉ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገሩ ሲሆን የመናገር ነጻነትን እና የዲሞክራሲ እሴቶችን እንደሚያከብሩም ገልጸዋል።
ሆኖም “ማስፈራራት፣ ዛቻዎች ሊቆሙ ይገባል” ካሉ በኋላ
“አስተዳደራችን እያየነው ካለነው ማስፈራሪያና ዛቻ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ለኬንያ ህዝብ ቃል እገባለሁ” ብለዋል።
“ዲሞክራሲያዊት የሆነች አገራችንን እየመለስን ነው” ያሉት ዊሊያም ሩቶ ይህንን ንግግራቸውን ያሰሙት ለጥምረቱ አባላት ሲሆን ራይላ ኦዲንጋ ማክሰኞ እለት ስለሰጡት አስተያየት በቀጥታ አልጠቀሱም።
በዚህ ንግግራቸው ስለ ህዝባዊ አገልግሎት ያነሱ ሲሆን ይህም በባለሙያዎች የሚመራ ይሆናል ብለዋል።
"ህዝባዊ አገልግሎቶች በባለሙያዎች የሚመሩ ሆነው ማንኛውንም ኬንያዊ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ውጪ በእኩልነት አገልግሎት ያገኛል" ብለዋል።
ፖለቲካዊ አቋም እንዲዙ ተገደዋል ያሏቸውን የመንግሥት ሰራተኞች ወደ ስራቸው ተመልሰው በሙያቸው እንዲያገለግሉም ጠይቀዋል በዛሬው ንግግራቸው።
“"የፖለቲካ ንግድ የሚካሄደው በፖለቲካ ተዋናዮች ነው።" ያሉት ተመራጩ ፕሬዚዳንት “በዚህም መንገድ ነው ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ መንግሥት የሚኖረው” ብለዋል።
በኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ሊቀ መንበአር አሸናፊነታቸው የተገለጸው ዊሊያም ሩቶ በ39 ግዛቶች 25 በመቶ ድምጽ በማግኘት ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ሁለት ምርጫዎች በበለጠ በሰፊ ማሸነፋቸውን ተናግረዋል።
ህዝቡ ፖለቲከኞች ወደ ስራቸው እንዲገቡ እና አገልግሎታቸውን መስጠት እንዲጀምሩም እንደሚፈልግ የተናገሩት ዊሊያም ሩቶ በዚህም ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ ውጤቱን ውድቅ በማድረግ መገዳዳራቸውን እንደማይፈልጉ ማሳያ ነው።
“ጉዳዩን ተቀብለው እልባት ካገኙለት ከኬንያ ህዝብ ተማሩ” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአገሪቱ እየተደረጉ ያሉ የደስታ መግለጫዎችን በመጥቀስ የኬንያ ህዝብ የምርጫውን ውጤት መቀበሉ አመላካች እንደሆነም ጠቁመዋል።












