ህወሓት ሊያካሂድ ያቀደው ጠቅላላ ጉባኤ ከአባላቱ ተቃውሞ እየገጠመው ነው

ከደም አፈሳሹ የትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ሕጋዊ ህልውናውን ያጣው ህወሓት 14ኛ ጉባኤውን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን ይነገራል።
በአሁኑ ወቅት የጉባኤውን ተሳታፊዎች ለመምረጥ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ስብሰባዎች እየተደረጉ ሲሆን፣ አንዳንዶች ግን ጉባኤው እንዳይካሄድ የሚል ውሳኔ አሳልፈዋል።
ለምሳሌ በደቡብ ትግራይ ዞን ከሚገኙት 14 ወረዳዎች 12ቱ የፓርቲው ጉባኤ በዚህ ጊዜ እንዳይካሄድ ወስነዋል።
በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እነዲሁም የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታቸው ረዳ በሚመራው አሰተዳደር መካከል ክፍፍል እንዳለ አንዳንድ ዘገባዎች እና የመሪዎቹ መግለጫዎች ይጠቁማሉ።
በደቡብ ምሥራቅ ዞን እንደርታ ወረዳ የፓርቲው አባላት “ጉባኤው በዚህ ጊዜ እንዳይካሄድ” የሚል ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ በስብሰባው የ24 ቀበሌዎች ተወካዮች መገኘታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የእንደርታ ወረዳ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ስላስ ሃፍቱ ሕዝቡ የተወሳሰበ ችግር ውስጥ ባለበት እና በፓርቲው ውስጥ አንድነት በሌለበት ሁኔታ ጉባኤ መካሄድ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንዳልሆን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የፓርቲው ሊቀመንበር እና ምክትላቸው አንድ ባልሆኑበት፣ የቁጥጥር ኮሚሽኑ ሊቀመንበሩን ጨምሮ አባላቱ በሌሉበት ጉባኤ ማካሄድ ተገቢ አይደለም” ብለዋል።
ወይዘሮ ስላስ ተሰብሳቢዎቹ ፓርቲው በአባላቱ የቀረበውን ሀሳብ እንዲያዳምጥ መማጸናቸውንም አስታውሰዋል።
“ከዚህ በፊት የአባላቱን ድምጽ የሚሰማ ድርጅት ነበር፤ ፓርቲው ወደ ቀድሞው ባህሪው ሊመለስ ይገባል። ከዚህ ውጪ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ አይደለም።”
በህወሓት ውስጥ የጎራ መፈጠር
በኢትዮጵያን እና በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ ለአስርታት የቆየ ጉልህ ሚና የነበረው ህወሓት፣ በ50 ዓመት ታሪኩ አጋጥሞት የማያውቀው ፈተና እንደገጠመው ከጥቂት ሳምንታት በፊት መግለጹ ይታወሳል።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የወጀራት ወረዳ የፓርቲው ኃላፊ እንዳሉት፣ አባላቱ ተቃውሞ እያነሱ ያሉት በክልሉ በተፈጠረው ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ነው።
“የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ ከጉባኤው ይቅደም የሚል ፍላጎት ነው ያለው። በመሠረታዊ ድርጅቱ ስብሰባ ላይ መሳተፍ የነበረባቸው አባላት እና ካድሬዎች አልተገኙም። [በመካሄድ ላይ ያሉ] ስብሰባዎች እራሳቸው አፋኝነት የሚታይባቸውን እና የተለየ ሃሳብ ተቀባይነት የማይሰጥበት ናቸው” ብለዋል።
የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ዞን የሕዝብ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ደስታ ግርማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ መድረኩ የተካሄደው በጉዳዩ ላይ አንድ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ታስቦ ነው።
በክልሉ ውስጥ “ከፌዴራል መንግሥት እና ከምርጫ ቦርድ እውቅና ሳይሰጠው የህወሓት ጉባኤ መካሄድ ለሕዝብ አጥፊ እና የማይጠቅም ነው” የሚል አቋም የያዙ ሰዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።
“የቁጥጥር ኮሚሽኑ አባላት በሌሉበት፣ ሁለት ሰዎች ከአዘጋጅ ኮሚቴው በቀሩበት፣ በአጠቃላይ በፌዴራል መንግሥት ላይ እምነት በሌለበት ሁኔታ እና ብዙ ሰዎች ከአዘጋጅ ኮሚቴው ራሳቸውን ባገለሉበት ሁኔታ ውስጥ ጉባኤ ማካሄድ አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል መረጃዎች አሉ፤ እኔም ይህንን ተገንዝቤ ነው ራሴን ያገለልኩት” ይላሉ።
የህወሓት ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላቱን ከህወሓት 14ኛ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ አባልነት ማንሳቱን አስታውቋል። የቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀ መንበር አቶ ተኽለብርሃን አርኣያ በፓርቲው ውስጥ በተሳሳተ መንገድ መሄድ የሚፈልግ ኃይል አለ በማለት ተችተዋል።
“አመራር ከዓላማው ሲያፈነግጥ ድርጅቱን ያበላሻል። አመራር የራሱን ጥቅምን እና ኃይሉን ማዕከል አድርጎ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው። በፓርቲው ውስጥ ሁለት ጐራ የለዩ ቡድኖች አሉ። ሁሉንም ነገር ያበላሸው ይሄው መቧደን ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የምሥራቅ ትግራይ ዞን የሕዝብ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ደስታ በበኩላቸው “አንድ ፓርቲ በየጊዜው ጉባኤውን ማካሄድ ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ በዝግጅቱ ላይ ትኩረት የሚሹ ነገሮች አሉ። ተመሳሳይ አመለካከት መያዙ ወደ አንድነት ያመራል እንጂ የተከፋፈሉ ቡድኖች ተይዞ ወደ ጉባኤ መሄድ የጤና አይደለም” ብለዋል።
“ሁለት ቡድኖች አሉ፤ አንደኛው ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን የሚቆጣጠር ሲሆን፣ ሌላው በፓርቲው የሚመራ ነው። ስለዚህ ይህንን ጉባኤ እንዳይካሄድ የምንቃወመው አንዱን ሌላውን ቆርጦ መጣል ይፈልጋል ብለን ስለምናምን ነው” ብለዋል።
“ሌላ የጦርነት አዙሪት”
በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከህወሓት አመራር በኩል የተቀናጀ ስም ማጥፋት እና ጥቃት ሲሰነዝርበት እንደቆየ መግለፁ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ህወሓትን ምርጫ ቦርድ እስካልመዘገበው ድረስ በአገር አቀፍ ምርጫ እና የፖለቲካ መድረኮች ላይ መሳተፍ እንደማይችል፣ እውቅና ከማግኘቱ በፊት ወደ ጠቅላላ ጉባኤ መሄድም ወደ ግጭት ሊመራ የሚችል አካሄድ መሆኑ ተናግረዋል።
አቶ ደስታም በህወሓት አመራር መካከል ባለው አለመግባባት እና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ሊፈጠር የሚችለውን ቅራኔ ከግምት ውስጥ በማስገባት የፓርቲው ጉባኤ ባይካሄድ የሚል አቋም የያዙት የከፋ አደጋ እንዳይደርስ በሚል መሆኑን ይናገራሉ።
“እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ጉባኤ ማካሄድ የባሰ ለሁለት ስለሚከፋፍለን፤ ምናልባትም ወደ ሌላ የጦርነት አዙሪት ስለሚመራን ስብሰባው ውድቅ እንዲሆን ተደርጓል። የእንደርታ ወረዳ አባላትም በዚህ ጉባኤ ላይ አንሳተፍም በማለት ወስነዋል” ብለዋል።
ምርጫ ቦርድ ህወሓት ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር በነበረው የፖለቲካ አለመግባባት ወደ ጦርነት ከገባ በኋላ ሕጋዊ እውቅናውን መሰረዙ የሚታወስ ነው።
ህወሓት በፖለቲካ ውሳኔ ያጣው ሕጋዊ አካላነት እውቅናው እንዲመለሰለት እንጂ እንደገና እንዲመዘገብ አይፈልግም ሲሉ የፓርቲው ቃል አቀባይ አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የማይጨው ከተማ ከንቲባ የማነ ንጉሤ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሁሉ በፊት ፓርቲው ጉባኤውን አካሂዶ የሕዝቡን መልካም አስተዳደር ጥያቄ ቢመልስ የሚል እምነት እንደነበራቸው፣ ነገር ግን ህወሓት ያደረጋቸውን ረዥም ጊዜ የወሰዱ ስብሰባዎችን ከተመለከቱ በኋላ “ድርጅቱ አመራር በኔትወርክ እና በአካባቢያዊነት እየታመሰ እንደሆነ” መገንዘባ መቻላቸው ይናገራሉ።
“አንድ ቡድን ሌላውን ማሸነፍ የሚፈልግበት ሁኔታ አለ፤ በሁለተኛ ደረጃ ይህ ኔትወርክ ለረጅም ጊዜ የቆየእና ስር የሰደደ ነው” ሲሉም የቁጥጥር ኮሚሽኑ ሦስት አባላት ከወጡ ጉባኤውን የሚመራው ማን ነው? የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
ተወካዮቹ የህወሓትን ሕጋዊ እውቅና ወደነበረበት ለመመለስ በመግባባት ሊፈታ ይገባል የሚል አቋም እንዳላቸውም አቶ የማነ ተናግረዋል።
“ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መግለጫ ህወሓት በሕጉ መሠረት ካልተመዘገበ ወደ ሌላ ሁኔታ እንሸጋገራለን ብሏል። ስለዚህ መግባባት ላይ አልተደረሰም ማለት ነው የሚል ትርጉም ሰጥቶናል” ብለዋል።
ስለዚህ ይህን ሳይጠራ ወደ ጉባኤ መሄድ የሚያስከትለው መዘዝ አደገኛ ከመሆኑም በላይ የበለጠ ይከፋፍለናል የሚል አቋም አላቸው።
አቶ ደስታ በበኩላቸው አሁን ያለው ልዩነት በ1993 ዓ.ም. የተከሰተውን ዓይነት አንዱ ቡድን ሌላውን ቆርጦ የመጣል ኣካሄድ መሆኑን ያምናሉ።
ህወሓት ከዚህ በፊት ‘ሕንፍሽፍሽ’ በሚል የሚታወቁ ውስጣዊ የመከፋፈል አደጋዎች አጋጥመውት የሚያውቅ ድርጅት ሲሆን፣ በተለይ በአገር መሪነት ሥልጣን ላይ ሳለ በ1993 ዓ.ም. ለሁለት ጐራ በተሰነጠቀበት ወቅት በርካታ አንጋፋ አመራሮቹ ከፓርቲው መወገዳቸው ይታወሳል።












