የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ሁለተኛ ዙር ግምገማ በአዲስ አበባ ተካሄደ

የፎቶው ባለመብት, Africa Union
ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨው የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት አፈጻጸም ሁለተኛ ዙር ግምገማ ማክሰኞ ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መካሄዱን የአፍሪካ ኅብረት አስታወቀ።
በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የተካሄደው ግምገማ በህወሓት እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምነት ያሳካቸው ተግባራትን ለመገምገም እና የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም በዘላቂነት የትግበራውን ስኬታማነት ለማረጋገጥ ስትራቴጂዎችን የሚነድፍ መሆኑን ኅብረቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በዚህ ግምገማ ላይ ተፈራራሚዎቹ የህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥት ተወካዮች እንዲሁም ታዛቢዎቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ተሳትፈዋል።
ከእነዚህ አካላት በተጨማሪ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲደረስ ሚና ያላቸው ሦስቱ የአፍሪካ አገራት ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ በተወካዮቻቸው በኩል የዚህ ግምገማ አካል እንደነበሩ ተገልጿል።
በማክሰኞ ዕለት የተካሄደው ይህ ግምገማ የፌራል መንግሥቱ እና ህወሓት መካከል ባለው የፖለቲካ ውይይት ላይ እና ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የጋራ መግባባትን መመርመሩም የኅብረቱ መግለጫ ጠቅሷል።
ሁለቱ አካላት የትግራይ ጦርነት መነሳት ተከትሎ ከምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው መመለስ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ መበተን እና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ የማዋሃድ ርዕሰ ጉዳዮችን በመምረጥም ተወያይተዋል።
ትጥቅ የማስፈታቱትንም ሆነ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ኑሯቸውን ለማቋቋም የሚያስችል የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም በጦርነት የወደመችውን ትግራይ መልሶ የመገንባት አስፈላጊነትም ተጠቅሷል።
የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ተፈናቃዮቹን ወደቀያቸው መመለስም ሆነ በትጥቅ ማስፈታታት እና ከማኅበረሰቡ ጋር መልሶ የማዋሃድ ጉዳይ ላይ መሻሻል እንደታየ ዕውቅና ሰጥተው ደረጃ በደረጃ ለመፈጸምም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል።
ግምገማውን አስመልክቶ የፖለቲካ ውይይት፣ ትጥቅ መፍታት እና ተፈናቃዮችን መመለስ በስፋት ውይይት የተካሄደበት እንደነበር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ፣ ሐምሌ 3 በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሂደት መሻሻል እንዳለ ሁለቱም አካላት ቢቀበሉትም በዋናነት በዚህ የተጎዱትን የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮችን ጨምሮ የተፈናቃዮችን ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ በመፍታት ሂደቱን ማፋጠን አስፈላጊነት ማመላከታቸውንም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ በሚያዝያ ወር መጨረሻ በሰጡት መግለጫ እስከ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም. ድረስ ጦርነቱን ተከትሎ በአማራ ክልል ስር ተጠቅለው የተቋቋሙ አስተዳደሮች እንደሚፈርሱ እና ተፈናቃዮች እንደሚመለሱ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ስምምነት መደረሱን መግለጻቸው ይታወሳል።
የፕሪቶሪያን ስምምነት ተከትሎ ተግባራዊ ካልሆኑ ጉዳዮች አንዱ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለስ ጉዳይ እንደሆነ የተናገሩት ጄኔራሉ በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት በተደረገው ውይይትም መግባባት ላይ እንደተደረሰም ገልጸው ነበር።
ባለፈው ወርም በጦርነቱ ወቅት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎችን የመመለስ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።
በተጨማሪም የህወሓት ምዝገባ እና በሱዳን ባለው ጦርነት ምክንያት ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉ የትግራይ ተወላጆችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ጉዳይ መነሳቱንም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።
የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች ተገናኝተው ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ገለጻ ማድረጋቸውንም አቶ ጌታቸው አመላክተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ላስመዘገቡት የተሻሻለ ሂደት እንዲሁም ስምምነቱን እየተከታታሉ ያሉ አባላት ላሳዩት የማያወላዳ አመራር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ኅብረቱ እየመራው ላለው ለዚህ ስምምነት ሂደት የኬንያ፣ የናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ መንግሥታት እያደረጉት ላለው ቀጣይነት ላለው ድጋፍ አድናቆቱን ችሯል።
ኅብረቱ እነዚህን ውይይቶች ከማመቻቸት በተጨማሪ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ሂደት በተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ዘላቂ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።
የፌደራል መንግሥቱ በግምገማው ላይ ምንም አስተያየት ባይሰጥም የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የአፍሪካ ኅብረት በሚያደርገው ግምገማ ምክንያት ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ ማቋረጡን በፌስቡክ ገጹ ገልጿል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ለዚህ ግምገማ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ሰነዶችን በማዘጋጀት እና ውስጣዊ ግምገማ ሲያካሂዱ መቆየታቸውንም ይኸው መረጃ አመልክቷል።
የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር በሁለተኛው የስትራቴጂ ግምገማ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያቀኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ሰኔ 28/ 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አመልክቶ ነበር።
አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን በመደገፍ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም ይኸው መግለጫ አትቷል።
ትጥቅ በማስፈታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና ከማኅበረሰቡ መልሶ የማዋሃድ ፕሮግራም፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን በመመለስ እንዲሁም በሽግግር ፍትህ እና ተጠያቂነትን በማስፈን አሜሪካ ድጋፏን ትቀጥላለች ብሏል።
በአፍሪካ ጥላ ስር የተካሄደው የፕሪቶሪያው ስምምነት የመጀመሪያ ግምገማ መጋቢት 2/ 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።
የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት በመጀመሪያው ስብሰባቸው ላይ ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት አፈጻጸም ተግባራዊነት ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸው በሚቀጥሉት ወራትም ለመወያየት ቀጠሮ ይዘው መለያየታቸው ይታወሳል።












