አቶ ታዬ ደንደአ የሰባት ዓመት ከሁለት ወር እስር ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, ministry of peace
የቀድሞው የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ እና የኦሮሚያ ምክር ቤት አባል አቶ ታዬ ደንደአ ጥፋተኛ በተባሉበት ክስ የሰባት ዓመት ከሁለት ወር እስር ተፈረደባቸው።
አቶ ታዬ ዛሬ አርብ ኅዳር 26/2018 ዓ.ም. የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና በሕገ መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ጥፋተኛ በተባሉበት ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት ነው።
የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን እና የክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ታዬ ሕገ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት እንዲሁም ፍቃድ ሳይኖራቸው በቤታቸው ውስጥ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ60 ጥይቶች ጋር ተገኝቷል በሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
የአቶ ታዬ ጠበቃ "መስማት የነበረባቸው ሦስት የመከላከያ ምስክሮች ነበሩ፤ እነርሱ ሳይሰሙ ቀርተዋል። የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እናከብራለን ነገር ግን ቅሬታዎች አሉን" ሲሉ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረዋል።
ዐቃቤ ሕግ እና ተከሳሹ አቶ ታዬ ደንደአ ከቤታቸው በተገኘ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ክስ ላይ ሲከራከሩ የቆዩ ሲሆን፣ በክርክሩ ወቅት ዐቃቤ ሕግ ሁለት ምስክሮች አቅርቦ አስመስክሯል።
አቶ ታዬ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታን ጠባቂዎቻቸው መልቀቃቸውን በመጥቀስ 'የደኅንነት ስጋቶች' ስላለባቸው መሣሪያ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸው ኮሚሽነሩ መሣሪያ ይሰጠኝ የሚለውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ደብዳቤ እንዲጽፉ እንደነገሯቸው ገልጸዋል።
ከዚያም በወቅቱ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት እና አሁን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑትን አቶ ቢናልፍ አንዷለምን ደብዳቤ እንዲጽፉላቸው መጠየቃቸውን ለችሎቱ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ደብዳቤ ከመጻፍ ይልቅ በቃል ይሻላል ተብሎ የሚፈልጉትን ጦር መሣሪያ እንዲታጠቁ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በ2015 ዓ.ም. አንድ ክላሽ ጥይቶች ከያዘ ሁለት ካዝና ጋር ከግለሰብ ተቀብለው መውሰዳቸውን፣ ይህም ፈቃድ ሳይወጣለት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
ይህንን እንዲያስረዱላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም፣ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒን የመከላከያ ምስክሮችን በማድረግ አቅርበዋል።
ሆኖም ፍርድ ቤት ቀርበው ምስክርነታቸውን ለመስጠት የቻሉት አምባሳደር ቢናልፍ አንዱዓለም እና ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ብቻ ናቸው።
የተከሳሹ ጠበቃ አቶ አበራ ንጉሥ ቀሪዎቹ ሦስት የመከላከያ ምስክሮች አለመመስከራቸው ለቅጣት ውሳኔው መክበድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ።
"ፍርድ ቤቱ በሬጅስትራር በኩል ለማቅረብ ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፣ የፌዴራል ፖሊስም የመጥሪያ ወረቀት እንዲያደርሳቸው ሙከራ ተደርጎ ለመቅረብ አልቻሉም። ይህም የደንበኛዬን ራሱን የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ መብት ጎድቶታል" ብለዋል።
"የተላለፈው ውሳኔ የደንበኛዬን መሠረታዊ ራንስ የመከላከል መብትን የጣሰ በመሆኑ ጥፋተኛ መባሉን እንቃወማለን" ያሉት ጠበቃው "ቅጣቱ አስተማሪ ነው ብለን አናምንም፤ የተጣለው ቅጣት በጣም ከፍተኛ ነው ብለን እናምናለን" ሲሉም አክለዋል።
ችሎቱ በአቶ ታዬ ላይ ካሳለፈው የእስር ውሳኔ በተጨማሪ የአምስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት የወሰነባቸው ሲሆን ጠበቃቸው በአጠቃላይ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዐቃቤ ሕግ ሦስት ተጨማሪ ክሶችን በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ ያቀረበ ሲሆን፣ ይህንን ለማየት ችሎቱ ለታኅሣሥ 8/2018 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
ከሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ጋር በተያያዘ በቀረቡባቸው ክሶች ከእስር ቤት በዋስ ወጥተው እንዲከላከሉ ተወስኖላቸው የነበረው አቶ ታዬ ደንደአ፤ ዐቃቤ ሕግ ነጻ የተባሉባቸውን ክሶች በመቃወም ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ የዋስትና መብታቸው ተነስቶ ለእስር ተዳርገዋል።
ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው ምክንያት በእስር ላይ የቆዩት አቶ ታዬ ደንደአ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የመንግሥት ተሿሚ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።
አቶ ታዬ በአገሪቱ ስላለው የሰላም ሁኔታ እና በመንግሥት ውስጥ ስላሉ ጉዳዮች ለመገናኛ ብዙኃን በመናገር እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሐሳባቸውን በመግለጽ ይታወቃሉ።
የጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደርን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተቹ በኋላ ከሰላም ሚኒስትር ዴኤታነታቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጻፈ ደብዳቤ ተሰናብተዋል።
ከዚያም በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ ጠንከር ያለ ትችት እና ክስ በሰነዘሩበት ምሽት በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተወስደው አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ ቆይተው በፍርድ ቤት ውሳኔ በዋስ ቢለቀቁም ከግንቦት 2017 ዓ. ም. ጀምሮ በድጋሚ ታስረዋል።
አቶ ታዬ "ከጠላት ጋር ማበር" አና የአገር መከላከያ ሠራዊትን ለመምታት "ዝግጅት አድርገዋል" በሚል ከቀረቡባቸው ሁለት ከባድ ክሶች ነጻ ተብለዋል።
ተከሳሹ በፍርድ ቤት ነጻ የተባሉባቸው ክሶች ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ታይተው ውድቅ ተደርገው የነበሩ ቢሆንም፣ ነገር ግን በድጋሚ እንዲታዩ ተወስኖ ነበር።
አቶ ታዬ አሁን የሰባት ዓመት እስር የተፈረደባቸው ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል በአንደኛው ሲሆን፣ ከሳምንት በፊት ሦስት ተጨማሪ ክሶች እንደቀረበባቸው መገለጹ ይታወሳል።
ጠበቃቸው አቶ አበራ ንጉሥ እንደተናገሩት ሦስቱ ክሶች ሁከት እና ብጥብጥ ማስነሳት እንዲሁም በሕግ የተመረጠ መንግሥትን በኃይል ለመናድ መሞከር፣ በመከላከያ ሠራዊት ላይ ሐሰተኛ እና የሚያደናግር መረጃ መንዛት እና አገርን የመድፈር ወንጀል ናቸው።















