አቶ ታዬ ለምስክርነት የጠሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከንቲባዋ ባይቀርቡም ሁለት ምስክሮችን አሰሙ

የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ለምስክርነት የቆጠሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ ባይቀርቡም ሌሎች ሁለት የመከላከያ ምስክሮቻቸው መሰማታቸውን ጠበቃቸው ተናገሩ።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል እና የገዢው ፓርቲ ባለሥልጣን የነበሩት አቶ ታዬ ባለፈው ዓመት በቁጥጥር ስር ውለው ለወራት ከታሰሩ በኋላ ከእስር ወጥተው የተወሰኑ ክሶቻቸውን ከውጪ ሲከታተሉ መቆየታቸው ይታወሳል።
ውድቅ የተደረጉት ክሶቻቸውን እንዲከላከሉ ካለፈው ግንቦት ወር ማብቂያ ወዲህ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ታዬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎችንም በምስክርነት ቆጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ዛሬ ሰኞ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም. ጉዳያቸው የታየው አቶ ታዬ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውጪ ሁለት የመከላከያ ምስክሮችን ማሰማታቸውን ጠበቃቸው አቶ አበራ ንጉሥ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን የፌደራል ፖሊስ በምስክርነት እንዲያርባቸው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የከንቲባ አዳነች አቤቤ ጉዳይ ከምን እንደደረሰ በፍርድ ቤቱ የተሰጠ ምላሽም ሆነ ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄ ለማቅረብ እንዳልቻሉ ጠበቃው ገልጸዋል።
ቢሆንም ቀደም ሲል ፍርድ ቤት እንዲከላከሉ በወሰነባቸው ክሶች ላይ መከላከያ ይሆኑኛል ያሏቸው የሁለት ሰዎች ምስክርነት በዛሬው ዕለት ተሰምቶ ለሐምሌ 11/2017 ዓ.ም. ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
ጠበቃው አቶ አበራ በቀጣይ ቀጠሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ለምን በምስክርነት እንዳልቀረቡ እንደሚጠይቁ እና ሌሎች የመከላከያ ምስክሮች እንዲሁም ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ እንደሚያርቡ አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው ከተባረሩ በኋላ ለእስር የተዳረጉት አቶ ታዬ ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እንዲሁም የጦር መሳሪያ ሕግን በመተላለፍ ወንጀሎች ተከሰው ነበር።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሽብር እና የሕገ መንግሥት ችሎት ከሦስቱ ክሶች መካከል በሁለቱ፣ ማለትም ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት እና ለፀረ-ሰላም ኃይሎችን ድጋፍ ማድረግን በተመለከቱ ክሶች በነጻ አሰናብቷቸው ነበር።
የጦር መሳሪያ ወንጀሎችን በተመለከተ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ በዚያው ችሎት ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ ለወራት የቀረቡባቸውን ቀሪ ክሶችን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ ዐቃቤ ሕግ አቋርጧቸው የነበሩ ሁለት ክሶችን ዳግም አንቀሳቅሷል።
አቶ ታዬ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነው የአገርን፣ የመንግሥትን እና የሕዝብን ደኅንነት ማረጋገጥ ሲገባቸው በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 257 ንዑስ አንቀጽ (ሠ) ተላልፈዋል በሚል ተከሰው ነበር።
በተጨማሪም ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት እንዲሁም ፍቃድ ሳይኖራቸው በቤታቸው ውስጥ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ60 ጥይቶች ጋር ተገኝቷል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ነገር ግን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት ሐምሌ መጨረሻ አቶ ታዬ ደንደአ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ሁለቱን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ አሰናብቷቸው እንደነበር ይታወሳል።
ከሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ የቀረቡባቸውን ክሶች ደግሞ ከእስር ቤት በዋስ ወጥተው እንዲከላከሉ ተወስኖላቸው የነበረ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ ግን አቶ ታዬ ነጻ የተባሉባቸውን ክሶች በመቃወም ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ የዋስትና መብታቸው ተነስቶ ለእስር ተዳርገዋል።















