አቶ ታዬ ደንደአ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች ከሁለቱ ነጻ ሲወጡ በአንደኛው ጥፋተኛ ተባሉ

የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ታዬ ደንደአ በዐቃቤ ሕግ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች ፍርድ ቤት በሁለቱ በነጻ ሲያሰናብታቸው በአንዱ ግን ጥፋተኛ ተባሉ።
ዛሬ ማክሰኞ ኅዳር 3/2018 ዓ. ም. የአቶ ታዬን ጉዳይ የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና በሕገ መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ከቀረቡለት ሦስት ክሶች የጦር መሣሪያ ሕግን በመተላለፍ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነው እንዳገኛቸው ወስኗል።
የአቶ ታዬ ጠበቃ አቶ አበራ ንጉሥ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ደንበኛቸው ከቀረቡባቸው ክሶች በሁለቱ ነጻ ተብለዋል።
አቶ ታዬ ነጻ የተባሉባቸው ክሶች "ከጠላት ጋር ማበር" አና የአገር መከላከያ ሠራዊትን ለመምታት "ዝግጅት አድርገዋል" የሚሉት ሁለት ከባድ ክሶች ናቸው።
ተከሳሹ አሁን በፍርድ ቤት ነጻ የተባሉባቸው ክሶች ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ታይተው ውድቅ ተደርገው የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን በድጋሚ እንዲታዩ መወሰኑ አይዘነጋም።
በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ፤ ዐቃቤ ሕግ በፍርድ ቤት ካቀረባቸው መከራከሪያዎች መካከል አቶ ታዬ በፌስቡክ ገጻቸው ያጋሩት መረጃ "ታጣቂዎች መንግሥትን መገዳደራቸውን ተቀባይነት ያለው የሚያስመስል ነው" የሚለው ይገኝበታል።
በተጨማሪም ከመታሰራቸው በፊት አቶ ታዬ ከቢቢሲ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስም ዐቃቤ ሕግ ለክሱ ማጠናከሪያነት ጠቅሶ ነበር።
አቶ ታዬ በበኩላቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩት መልዕክት የእሳቸው መሆኑን አረጋግጠው "እኔ ያስተላለፍኩት መልዕክት ወንጀል አይደለም" ሲሉ ተከራክረዋል።
አቶ ታዬ በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩትን መልዕክት እንዲሁም ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንደተመለከተ የገለጸው ፍርድ ቤቱ በሁለቱ ክሶች ነጻ ሲላቸው በሦስተኛው ክስ ግን ጥፋተኛ ተብለዋል።
የመጀመሪያው እና አቶ ታዬ ነጻ የተባሉበት ክስ፤ "የወንጀል ሕግ 251 ንዑስ ሐ በመተላለፍ ከጠላት ጋር (ከሸኔ እና ከፋኖ ጋር) ተባብረዋል" የሚል እንደሆነ የጠቀሱት ጠበቃው ይህም ከ20 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ወይም ሞት የሚያስቀጣ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ሁለተኛው ነጻ የተባሉበት ክስ፤ የወንጀል ሕን 257 ንዑስ ሠ በመተላለፍ "መንግሥትን ለመጣል የፕሮፖጋንዳ እና ሌሎች ድጋፎችን ለጠላቶች በማድረግ ግዙፋዊ መሰናዶ አድርገዋል" የሚለው ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ እንደሆነም አክለዋል።
የቀድሞው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን እና የክልል ምክር ቤት እንደራሴው አቶ ታዬ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች በሁለቱ ነጻ ከተባሉ በኋላ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙበት ሕገ ወጥ መሣሪያ ይዞ በመገኘት ክስ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ለመስማት ለኅዳር 15/2018 ዓ. ም. ቀጠሮ እንደተሰጠ ጠበቃው ገልጸዋል።
"በዛሬው ውሳኔ ደስተኛ ነን። ደንበኛዬን ይጎዳሉ በምላቸው በሁለቱ ትላልቅ ወንጀሎች ነጻ ስለተባሉ ደስተኛ ነኝ" ያሉት ጠበቃ አበራ "በሦስተኛው ክስ የተሰጠው የጥፋተኛነት ብያኔ ተቀብዬዋለሁ ማለት አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ታዬ ከጠሯቸው አምስት የመከላከያ ምስክሮች መካከል የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይገኙ ሁለቱ ብቻ መሰማታቸውን ጠበቃው ጠቅሰው "ሥርዓቱን ተከትለን ይግባኝ እንላለን" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የጦር መሣሪያ ወንጀሎችን በተመለከተ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ አቶ ታዬ ጉዳዩን እናውቃለን የሚሉ አምስት የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ለምስክርነት ጠርተው እንደነበር ይታወሳል።
ሰኔ 30/2017 ዓ. ም. በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ አቶ ታዬ በምስክርነት ቀርበው ያስረዱልኝ ካሏቸው መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባይገኙም ሌሎች ሁለት የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተው ነበር።
ጠበቃው አቶ አበራ ንጉሥ አክለውም በደንበኛቸው ላይ ተፈጽሟል ስላሉት የሰብአዊ መብት ጥሰት ጉዳይ እና ግንቦት 25/2017 ዓ.ም. ያለአግባብ ከቤታቸው በፖሊስ ሲያዙ ከክርክሩ ጋር ተዛማጅ ያልሆኑ በፖሊስ የተወሰዱ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እንዲመለሱ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።
ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ተደራራቢ ክሶችን የመሠረተው ሚያዚያ 2016 ዓ.ም. ነው።
አቶ ታዬ ደንደአ በቀረቡባቸው ክሶች ምክንያት ለወራት በእስር ከቆዩ በኋላ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ኅዳር 23/2017 ዓ. ም. በ20 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ወስኖ ነበር።
የጦር መሣሪያ ወንጀሎችን በተመለከተ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ በዚያው ችሎት ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ ለወራት የቀረቡባቸውን ቀሪ ክሶችን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ ዐቃቤ ሕግ አቋርጧቸው የነበሩትን ሁለት ክሶችን ዳግም አንቀሳቅሷል።
አቶ ታዬ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነው የአገርን፣ የመንግሥትን እና የሕዝብን ደኅንነት ማረጋገጥ ሲገባቸው በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 257 ንዑስ አንቀጽ (ሠ) ተላልፈዋል በሚል ተከሰው ነበር።
በተጨማሪም ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት እንዲሁም ፍቃድ ሳይኖራቸው በቤታቸው ውስጥ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ60 ጥይቶች ጋር ተገኝቷል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ነገር ግን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት ሐምሌ መጨረሻ አቶ ታዬ ደንደአ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ሁለቱን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ አሰናብቷቸው እንደነበር ይታወሳል።
ከሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ የቀረቡባቸውን ክሶች ደግሞ ከእስር ቤት በዋስ ወጥተው እንዲከላከሉ ተወስኖላቸው የነበረ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ ግን አቶ ታዬ ነጻ የተባሉባቸውን ክሶች በመቃወም ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ የዋስትና መብታቸው ተነስቶ ለእስር ተዳርገዋል።
አቶ ታዬ በአገሪቱ ስላለው የሰላም ሁኔታ እና በመንግሥት ውስጥ ስላሉ ጉዳዮች ለመገናኛ ብዙኃን በመናገር እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሐሳባቸውን በመግለጽ የሚታወቁ ሲሆን፣ ከሥልጣን የተሰናበቱት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጻፈ ሁለት መስመር ደብዳቤ መሆኑ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ ጠንከር ያለ ትችት እና ክስ በሰነዘሩበት ምሽት በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተወስደው አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ ቆይተው ነው በፍርድ ቤት ውሳኔ በዋስ ቢለቀቁም ከግንቦት 2017 ዓ. ም. ጀምሮ በድጋሚ ታስረዋል።















