አቶ ታዬ ደንደአ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው መወሰዳቸውን ባለቤታቸው ተናገሩ

የቀድሞው የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ በሰኞ ከሰዓት በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ባለቤታቸው ተናገሩ።
ከሥልጣናቸው ተነስተው ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ በዋስትና ተለቀው ጉዳያቸውን ከውጪ ሲከታተሉ የነበሩት አቶ ታዬ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት በቀጠሯቸው መሠረት ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር።
አቶ ታዬ በግንቦት 25/2017 ዓ.ም. ጠዋት በነበራቸው የፍርድ ቤት ውሎ ነጻ የተባሉባቸው ሁለት ክሶች በድጋሚ እንዲታዩ የተወሰነ ሲሆን፣ ከችሎት መልስ ከሰዓት በኋላ እንደታሰሩ እና የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ አቶ ታዬ በፖሊሶች ሰኞ ግንቦት 25/2017 ዓ.ም. ከሰዓት 10 ሰዓት በኋላ ለጥያቄ እንደሚፈለጉ በመግለጽ ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መወሰዳቸውን አረጋግጠዋል።
የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ፣ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ ባለፈው ኅዳር ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ሲከታተሉ ቆይተዋል።
ባለቤታቸው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወደ መኖሪያ ቤታቸው የመጡት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በር አንኳኩተው አቶ ታዬ ለጥያቄ በፌደራል ፖሊስ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ወስደዋቸዋል።
ከፀጥታ ኃይሎቹ ውስጥ የታጠቁ እንደነበሩ የጠቀሱት ባለቤታቸው ወደ ቤት በመግባት አቶ ታዬን ይዘው እንደወጡ እና በዚህ ጊዜም የጨፌ (የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት) አባል መሆናቸውን እና የሕዝብ ተወካይ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር ብለዋል።
ከአስር በላይ የሚሆኑ የፖሊስ አባላት አቶ ታዬን ለመያዝ ታዘው መምጣታቸውን እንደተናገሩ እና ተወሰዱ ወደተባለበት መሃል አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ጽሕፈት ቤት እንደሚሄዱ ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።
ነገር ግን የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ታዬ ደንደአ በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተይዘው ከተወሰዱ በኋላ እስከ ሰኞ ምሽት ድረስ የታሰሩበትን ማወቅ እንዳልቻሉ ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ስለአቶ ታዬ መታሰር እና ስላሉበት ሁኔታ ከፌደራል ፖሊስም ሆነ ከሌላ የመንግሥት አካል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
አቶ ታዬ ቀደም ሲል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና በሕገ መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት፣ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል በሁለቱ ማለትም ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት እና ለፀረ ሰላም ኃይሎች ድጋፍ ማድረግ ክሶች በነጻ ተሰናብተው ነበር።
ነገር ግን የአቶ ታዬን ጉዳይ የተመለከተው ችሎት በድጋሚ ከመታሰራቸው ከሰዓታት ቀደም ብሎ ክሶቹ እንዲቀጥሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መወሰኑን ቢቢሲ አቶ ታዬ ከመታሰራቸው በፊት ያነጋገራቸው ጠበቃቸው አቶ አበራ ንጉሥ ገልጸዋል።
አቶ ታዬ ደንደአ በቀረቡባቸው ክሶች ምክንያት ለወራት በእስር ከቆዩ በኋላ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ኅዳር 23/2017 ዓ. ም. በ20 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ወስኖ ነበር።
ባለፈው ዓመት ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ ለእስር የተዳረጉት አቶ ታዬ፣ ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እንዲሁም የጦር መሣሪያ ሕግን በመተላለፍ ወንጀሎች ተከሰው ነበር።
የጦር መሣሪያ ወንጀሎችን በተመለከተ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ አቶ ታዬ ጉዳዩን እናውቃለን የሚሉ አምስት የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለምስክርነት ጠርተው ነበር።
አቶ ታዬ በምስክርነት ቀርበው ያስረዱልኝ ካሏቸው መካከል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይገኙበታል።
ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ተደራራቢ ክሶችን የመሠረተው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2016 ዓ. ም. ነበር።
አቶ ታዬ በአገሪቱ ስላለው የሰላም ሁኔታ እና በመንግሥት ውስጥ ስላሉ ጉዳዮች ለመገናኛ ብዙኃን በመናገር እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሐሳባቸውን በመግለጽ የሚታወቁ ሲሆን፣ ከሥልጣን የተሰናበቱት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጻፈ ሁለት መስመር ደብዳቤ መሆኑ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ ጠንከር ያለ ትችት እና ክስ በሰነዘሩበት ምሽት በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተወስደው አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ ቆይተው ነው በፍርድ ቤት ውሳኔ በዋስ የወጡት።















