የኬንያ ፖሊሶች ከሦስት ሳምንት በኋላ ሄይቲ እንደሚገቡ ተገለጸ

 የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ

የኬንያ ፖሊሶች ከሦስት ሳምንታት በኋላ ሄይቲ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ተናገሩ።

በነውጠኛ ቡድኖች ምክንያት ፀጥታዋ ወደደፈረሰው ሄይቲ የኬንያን ሰላም አስከባሪ ፖሊሶች ለማሠማራት ዕቅድ የሚያወጡ ልዑካን ሄይቲ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

ሩቶ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ ወደ ሄይቲ የተላከው ቡድን ከሄይቲ ፖሊሶች ጋር ውይይት እያደረገ ሲሆን የኬንያ ፖሊሶች ወደ ሄይቲ የሚገቡበትን መንገድ ያመቻቻል።

ሩቶ ይህንን የተናገሩት የሦስት ቀናት የአሜሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ነው።

ባለፉት 15 ዓመታት በአሜሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ናቸው።

ባለፈው አርብ በሄይቲ ከተገደሉ የሃይማኖት አስተማሪዎች መካከል አሜሪካውያን ጥንዶች እንደሚገኙበት መገለጹን ተከትሎ፣ በኬንያ የሚመራው ሰላም አስከባሪ ኃይል በፍጥነት እንዲሠማራ ዋይት ሀውስ ጠይቋል።

“አሁን ሄይቲ ውስጥ ልዑካን ቡድን ተልኳል። መሬት ላይ ያለው ነገር ምን እንደሚመስል፣ ያለውን መሠረተ ልማትና አቅም እየቃኙ ነው” ብለዋል ሩቶ።

“ከሄይቲ ፖሊስና አመራሮች ጋር ባደረግነው ስምምነት መሠረት ቅኝታችንን ስናጠናቅቅ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ኃይላችንን ለማሠማራት ዝግጁ ነን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ሰላም አስከባሪዎች ወደ ሄይቲ ለማሠማራት ሲወስን ኬንያ የመሪነት ሚና ለመወጣት ጠይቃለች።

በ2021 ፕሬዝዳንት ዦቬኔል ሞይስ መገደላቸውን ተከትሎ ነውጠኛ ቡድኖች በፈጠሩት ቀውስ ምክንያት መዲናዋ ፖርት-ኦው-ፕሪንስ ከፍተኛ ውድመት ገጥሟታል።

ሩቶ እንደተናገሩት እየተፈጠረ ያለው ቀውስ ኬንያ ፖሊሶቿን ወደ ሄይቲ ለመላክ እንድትወስን ምክንያት ሆኗል።

“ሰዎች ማጣት የለብንም። የሃይማኖት አስተማሪዎች መገደል የለባቸውም። ነውጠኛ ቡድኖች ተጨማሪ ሰዎች እንዳይገድሉ ነው ኃይላችንን የምናሠማራው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

አሜሪካም ሰላም አስከባሪ ኃይሎቿን ትልካለች።

ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ “በሄይቲ ያለው ቀውስ ጊዜ አይሰጥም” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሩቶ ጋር ባደረጉት ውይይት በፍጥነት ኃይላቸውን ለማሠማራት ቃል ገብተዋል።

በሄይቲ ለሰላም አስከባሪዎች መሣሪያዎች እየተዘጋጁ እንደሆነና “70 በመቶ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ” ሩቶ ገልጸዋል።