ለ20 ዓመታት በጓንታናሞ ቤይ ያለፍርድ ታስረው የቆዩ ወንድማማቾች ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, REPRIEVE
ጓንታናሞ ቤይ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ እርስ ቤት ውስጥ ለሃያ ዓመታት ያህል ታስረው የቆዩ ሁለት ፓኪስታናውያን ወንድማማቾች ምንም ክስ ሳይቀርብባቸው ተለቀቁ።
አብዱል እና ሞሐመድ አህመድ ራባኒ ፓኪስታን ውስጥ ተይዘው ከአገራቸው የተወሰዱት በአውሮፓውያኑ በ2002 ነበር።
የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት አብዱል ራባኒ የተባለው ግለሰብ የአልቃኢዳን የመደበቂያ ቤት ያስተዳድራል እንዲሁም ወንድሙ የቡድኑ መሪዎችን ጉዞ እና ገንዘብን ይመራል ብሎ ነበር።
ወንድማማቾቹ ወደ ጓንታናሞ ከመሸጋገራቸው በፊት ከአገራቸው ውጪ በሲአይኤ መኮንኖች ማሰቃየት እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል።
ሁለቱ ፓኪስታናውያን ከአስፈሪው ወታደራዊው እስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
ኩባ ውስጥ የሚገኘው ጓንታናሞ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ሰፈር ከመስከረም 11 የሽብር ጥቃት በኋላ ተጠርጣሪዎችን ለማቆያነት የተቋቋመው በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ አማካይነት ነው።
ካምፑ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አሜሪካ ካካሄደችው “ፀረ ሽብር ጦርነት” ጋር በያያዘ ከተፈጸሙ መጥፎ ድርጊቶች ጋር ስሙ ይነሳል።
በተለይ ተጠርጣሪዎች በምርመራ ጊዜ ከባድ ሰቆቃ እንደተፈጸመባቸው እና ያለፍርድ ለረጅም ጊዜ በእስር እንዲቆዩ መደረጋቸው በስፋት ሲነገር ቆይቷል።
ከ20 ዓመት በፊት በጓንታናሞ ውስጥ 680 አስረኞች የነበሩት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን 32 እስረኞች ብቻ ይገኙበታል። የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስር ቤቱ እንዲዘጋ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
አሁን ነጻ የተለቀቁት ወንድማማቾች ከ20 ዓመት በፊት በፓኪስታን የደኅንነት ተቋም አማካይነት ካራቺ በተባለችው ከተማ ውስጥ ነበር የተያዙት። ከዚያም አፍጋኒስታን ውስጥ በሚገኝ የሲአይኤ እስር ቤት ለሁለት ዓመታት ቆይተው ነው ወደ ጓንታናሞ ቤይ ተየሸጋገሩት።
ከ2013 (እአአ) ጀምሮ ባሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ እስሩን በመቃወም አህመድ ራባኒ በተከታታይ የረሃብ አድማ አድርጎ ነበር። የምግብ መድኃኒቶች እየተሰጠው አንዳንድ ጊዜም በኃይል በቱቦ እንዲመገብ እየተደረገ በሕይወት ቆይቷል።
የሁለቱ ወንድማማቾች ጠበቃ የሆኑት ክሊቭ ስታፎርድ ስሚዝ ለኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንደተናገሩት አህመድ ራባኒ በረሃብ አድማው የተነሳ “ከባድ ጉዳት ደርሶበታል” ብለዋል።
ወንድማማቾቹ ከእስር እንዲለቀቁ የተወሰነው ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን፣ ለምን አስካሁን በእስር ላይ እንዲቆዩ እንደተደረገ ግን ግልጽ አልሆነም።
አህመድ ራባኒ በቁጥጥር ስር በዋለበት ጊዜ ሚስቱ እርጉዝ የነበረች ሲሆን፣ ከአምስት ወራት በኋላም ወንድ ልጃ ወልዳለች። ላለፉት 20 ዓመታትም አህመድ ከልጁ ጋር ተገናኝቶ አያውቅም።
የሁለቱ ወንድማማቾች እና ሌሎች ከሽብር ጋር በተገናኘ በጓንታናሞ ቤይ በእስር ላይ የቆዩ ሰዎች አያያዝ ሁኔታ እና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት አለመታየት በአሜሪካ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን አስከትሎ ቆይቷል።
በርካቶቹም ያለፍርድ ለዓመታት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ እንደ ሁለቱ ወንድማማቾች በነጻ መለቀቃቸው ደግሞ በዘፈቀደ የተደረገ እስር ነው በሚል የአሜሪካ መንግሥት የእራሱን ሕግ ጥሷል የሚል ትችትን አስከትሎበታል።












