በሩሲያ ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ኤርትራ ስትቃወም ኢትዮጵያ ድምጸ ተዓቅቦ አደረገች

የተባበሩት መንግሥታት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሩሲያን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ኤርትራ ስትቃወም ኢትዮጵያ ደግሞ ድምጸ ተዓቅቦ አደረገች።

የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ሐሙስ 17/2015 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ አንድ ዓመት ያስቆጠረውን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ የሚቃወም የውሳኔ ሃሳብ አሳልፏል።

ተመድ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ የሩሲያ ወታደሮች ከዩክሬን እንዲወጡ እና ግጭት እንዲቆም የሚጠይቅ ነው።

የውሳኔ ሃሳቡን 141 አገራት ሲደግፉት፣ ሩሲያን ጨምሮ 7 አገራት ደግሞ ተቃውመውታል። የተቀሩት 32 አገራት ደግሞ በድምጸ ተዓቅቦ አልፈውታል።

የውሳኔ ሃሳቡን የተቃወሙት ሰባት አገራት፤ ሩሲያ፣ ኤርትራ፣ ቤላሩስ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ማሊ፣ ኒካራጉዋ እና ሶሪያ ናቸው።

ኢትዮጵያ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ሳታስመዘግብ ቀርታለች። በተመሳሳይ እንደ ኢትዮጵያ የድምጸ ተዓቅቦ ካደረጉት አገራት መካከል ቻይና፣ ሕንድ፣ ኢራን እና ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ ናቸው።

ኤርትራ፣ ቤላሩስ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ሶሪያ እና ኒካራጉዋ ሩሲያን የተመለከተ የመንግሥታቱ ድርጅት የውሳኔ ሃሳብን ሲቃወሙ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

የተበበሩት መንግሥታት በውሳኔ ሃሳቡ ለዩክሬን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ድጋፉ የጸና መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ሩሲያ የዩክሬንን መሬት ወደ ግዛቷ መጠቅለሏንም ጨምሮ አውግዟል።

ከወራት በፊት የሩሲያ ምክር ቤት አራት የዩክሬን ግዛቶች የአገሪቱ አካል መሆናቸውን በይፋ ማወጁ ይታወሳል።

“የሩሲያ ፌዴሬሽን በአስቸኳይ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሁሉንም ወታደራዊ ኃይሎቿን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ከተሰጠው የዩክሬን ግዛት ማስወጣት አለባት” ብሏል የተመድ የውሳኔ ሃሳብ።

ይህ የመንግሥታቱ ድርጅት የውሳኔ ሃሳብ ሕጋዊ ተፈጻሚነት ባይኖረውም ትልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም ግን ይኖረዋል።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ድምጽ አሰጣጡ ሩሲያ ሕገ-ወጥ የሆነው ወረራዋ መቆም እንዳለበት እና የዩክሬን ሉዓላዊ ግዛት መመለስ እንዳለበት በትክክል ያሳየ ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የአውሮፓ የደኅንነት አካል በኦስትሪያ ቪዬና ባደረገው ስብሰባ ላይ ደግሞ፣ የሩሲያ ተወካይ ንግግር ሲያደርጉ በርካቶች የስብሰባውን አዳራሽ ጥለው ወጥተዋል።

ቀደም ሲል በአውሮፓ የደኅንነት እና ትብብር ድርጅት ስብሰባ ላይ የሞስኮ ተወካዮች እንዲገኙ መፈቀዱ ብዙዎችን ያስቆጣ ሲሆን፤ ዩክሬን እና ሉቱዌኒያ በጠቅላላ በስብሰባው ሳይገኙ ቀርተዋል።

የኦስትሪያ መንግሥት ግን የሩሲያ ተወካዮች በውይይቱ እንዲሳተፉ የጋበዝኩት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አስገዳጅ ስለሆነ ነው ብላለች።

አንድ ዓመት የደፈነው ጦርነት የተጀመረው ቭላድሚር ፑቲን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ነው የተባለውን 200 ሺህ ሠራዊት በዩክሬን ላይ ካዘመቱ በኋላ ነው።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ ይህ ጦርነት ቢያንስ 7ሺህ 199 ሰላማዊ ሰዎችን የገደለ ሲሆን በሺዎቹ የሚቆጠሩትን ደግሞ አቁስሏል።