ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አቶ ግርማ ዋቄ የኡጋንዳ አየር መንገድ አማካሪ እና ጊዜያዊ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ
የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንግድ ሥራ አስፈጻሚን ግርማ ዋቄን በአማካሪነት እና ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ አድርገው መሾማቸውን የአገሪቱ ጋዜጦች ዘገቡ።
አቶ ግርማ ዋቄ በአዲሱ ሹመታቸው በኡጋንዳ አየር መንገድ ውስጥ የታዩ የአስተዳደር ድክመቶችን ይሞላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ ለአገሪቱ ሥራ እና ትራንስፖርት ሚኒስትር በጻፉት ደብዳቤ አቶ ግርማ ዋቄ በአማካሪነት እና በጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚነት መሾማቸውን ገልጸዋል።
''በኡጋንዳ አየር መንገድ ውስጥ አሁን ያለውን የአመራር እና የአስተዳደር ድክመት ይታወቃል። በአየር መንገዱ ውስጥ ያሉ በርካታ የአመራር ድክመቶችን ለማስተካከል እንዲረዳችሁ ግርማ ዋቄን በአማካሪነት እንድትሾሙ አዝዣለሁ'' ብለዋል።
በተጨማሪም "በሐምሌ ወር 2026 ሥራ አስፈጻሚ እስክንሾም ድረስ ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲያገለግሉ ይሁን" ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ማዘዛቸውን ጋዜጦቹ ዘግበዋል።
ግርማ ዋቄ ለአየር መንገዱ ሥራ አስፈጻሚ እስኪሾም ድረስ ከቦርዱ ጋር በቅርበት እንደሚሠሩም ተገልጿል።
ከሳምንታት በፊት የኡጋንዳ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀኒፈር ባሙቱራኪ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ በኡጋንዳውያን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ የአቶ ግርማ ዋቄ ስም በተተኪነት ሲነሳ ሰንብቷል።
ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ ከቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተገናኝተው "ከተለያዩ ጉዳዮች በተጨማሪ ስለ አቪየሽን አስተዳደር" ውይይት ማድረጋቸውን የፕሬዝዳንቱ ፕሬስ ጉዳዮች ኃላፊው መግለጻቸው ይታወሳል።
ነገር ግን በአቶ ግርማ የአገሪቱ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዳልተሾሙ በመግለጽ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ማስተባበያ አውጥቶ ነበር።
የአሁኑ የፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ ደብዳቤ አቶ ግርማ የአየር መንገዱ አማካሪ ሆነው የተሾሙ ሲሆን በተጨማሪም አስከ ሐምሌ ወር ድረስ የዋና ሥራ አስፈጻሚነቱን ኃላፊነት ይይዛሉ።
በአሁኑ ወቅት በሥራ አስፈጻሚነት እያገለገሉ የሚገኙት ባሙቱራኪ ኃላፊነታቸውን ለአቶ ግርማ ዋቄ እንዲያስረክቡ ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ አዝዘዋል።
የኡጋንዳን አየር መንገድ እያስተዳደሩ የነበሩት ጄነፈር ባሙቱራኪ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የኡጋንዳ ጋዜጦች የትራንስፖርት ሚኒስትርን ጠቅሰው ዘግበዋል።
ኒው ቪዥን የተባለው መገናኛ ብዙኃን ከሁለት ሳምነት በፊት ከትራንስፖርት ሚኒስትሩ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ የኡጋንዳ አየር መንገድ ቦርድ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ግምገማ ካደረገ በኋላ በርካታ የአሠራር ጉድለቶችን በማግኘቱ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መወሰኑን ተናግረዋል።
አቶ ግርማ ዋቄ ለሰባት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ አየር መንገድን መርተዋል።
አቶ ግርማ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ባስተዳደሩባቸው ዓመታት በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን ሠርተዋል።