ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አቶ ግርማ ዋቄ ለኡጋንዳ አየር መንገድ መሪነት ተሾሙ መባሉን የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ጽሕፈት ቤት አስተባበለ
ጉምቱው የአቪየሽን አመራር አቶ ግርማ ዋቄ የኡጋንዳ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል መባሉን የኡጋንዳ ፕሬዝዳንታዊ ጽሕፈት ቤት አስተባበለ።
ባለፈው ሳምንት የኡጋንዳ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀኒፈር ባሙቱራቺ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ በኡጋንዳውያን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ የአቶ ግርማ ዋቄ ስም በተተኪነት ሲነሳ ሰንብቷል።
ዛሬም የኡጋንዳ የወጣቶች እና ሕጻናት ጉዳዮች ሚኒስትር ባላም ባሩጋሃራ ባላም፤ ኤክስ ላይ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አቶ ግርማን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርገው እንደሾሙ ጽፈው ነበር።
ነገር ግን ካምፓላ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ከኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ባገኘው መረጃ ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አቶ ግርማ ዋቄን በጽሕፈት ቤታቸው አግኝተው እንዳናገሯቸው አረጋግጦ፤ ሹመቱን ግን ጽሕፈት ቤቱ አስተባብሏል።
በተጨማሪም የፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ የፕሬስ ጉዳዮች ኃላፊ ሳንዶር ሊል፤ በኤክስ ገጻቸው ላይ "ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ለኡጋንዳ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመዋል መባሉ እውነት አይደለም" ሲሉ አስተባብለዋል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ከቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄ ጋር ረቡዕ ዕለት ተገናኝተው "ከተለያዩ ጉዳዮች በተጨማሪ ስለ አቪየሽን አስተዳደር" ውይይት ማድረጋቸውን የፕሬስ ጉዳዮች ኃላፊው አመልክተዋል።
ጨምረውም ኡጋንዳውያን ለአገሪቱ አየር መንገዱ አዲስ ሥራ አስፈጻሚ እንደተሾመለት ተደርጎ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚነገረውን ችላ እንዲሉት ጠይቀዋል።
በአፍሪካ ቀዳሚ እና ትልቁን የኢትዮጵያ አየር መንገድን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እና በቦርድ ሰብሳቢነት የመሩት አቶ ግርማ ዋቄ በአፍሪካ ውስጥ ስኬታማ የአቪየሽን ልምድ ካላቸው መሪዎች መካከል ጎልተው የሚታዩ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሻገር በሌሎችም ሠርተዋል።
የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ለአሁን አቶ ግርማ ዋቄ ለኡጋንዳ አየር መንገድ ሥራ አስፈጻሚነት እንዳልተሾሙ ቢገልጽም፤ ጉዳዩ ምናልባት በሒደት ላይ ሊሆን እንደሚችል እና እውነታው በቅርብ ቀን ሊታወቅ እንደሚችል በካምፓላ የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።
የአቶ ግርማ ሹመት በኡጋንዳውያን ዘንድ የተከፋፈለ አስተያየትን ያስከተለ ሲሆን፤ በርካቶች እንደ ኢትዮጵያ ስኬታማ አየር መገንድ እንዲኖራቸው ከመፈለግ የተነሳ በተግባር የተፈተኑት አቶ ግርማ መሪነቱን እንዲይዙ ፍላጎታቸውን እየገለጹ ነው።
ሌሎች ደግሞ የአቶ ግርማን ብቃት ጥያቄ ውስጥ ሳያስገቡ አገሪቱ ውስጥ የዋና ሥራ አስፈጻሚነቱን ቦታ ሊይዙ የሚችሉ ዜጎች ስለሚኖሩ እነሱ ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ይከራከራሉ።