ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳይ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ የተመድን ማዕቀብ ጥሶ በሱዳን ጦርነት ላይ ጥቅም ውሏል-አምነስቲ
የፈረንሳይ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ የተባበሩት መንግሥታት የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብን ተላልሮ በሱዳን ጦርነት ጥቅም ላይ መዋሉን አምነስቲ አስታወቀ።
የፈረንሳይ ወታደራዊ ግብዓቶች የተገጠሙባቸው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የጦር መሳሪያዎችን የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በዳርፉር ግዛት አካባቢ እየተጠቀመባቸው መሆኑን አምነስቲ ገልጿል።
“በፈረንሳይ ዲዛይን የተደረጉ እና የተመረቱ ወታደራዊ ግብዓቶች በሱዳን ጦርነት ላይ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ያደረግነው ጥናት አሳይቷል” ሲሉ የአምነስቲ ዋና ጸሐፊ አግነስ ካላማርድ ገልጸዋል።
ቢቢሲ የፈረንሳይን መንግሥት እንዲሁም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን እያስታጠቀች ነው የምትባለውን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን አስተያየት ጠይቋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የተራቡበት የሱዳን ጦርነት በዓለም ላይ አስከፊ የሚባለውን ሰብዓዊ ቀውስ እንዳስከተለ የሰብዓዊ ረድዔት ሰራተኞች ይናገራሉ።
ኬኤንዲኤስ እና ላክሮይክስ በተባሉት የፈረንሳይ ኩባንያዎች የተመረቱት ጋሊክስ የተሰኘው የመከላከያ ስርዓት በምድር ውጊያ ላይ በቅርብ ርቀት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመቋቋም ጥቅም ላይ ይውላል።
የጦር መሳሪያዎቹ በጦርነቱ በተፈጸሙ ከባድ ጥሰቶች ላይ ጥቅም ላይ ውለው ሊሆን እንደሚችል የገለጸው አምነስቲ፣ የፈረንሳይ መንግሥት ኩባንያዎቹ “ይህንን የመከላከያ ስርዓት ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከማቅረብ በፍጥነት እንዲያቆሙ ሊያደርጋቸው ይገባል” ብሏል።
አምነስቲ የጋሊክስ ስርዓት መገጠማቸው በጉልህ የሚታይባቸው ጉዳት የደረሰባቸው የጦር መሳሪያዎች ተሽከርካሪዎችን ማግኘቱን አረጋግጫለሁ ብሏል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ፈረንሳይ በመከላከያ ዘርፍ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ አጋርነት አላቸው። የፈረንሳይ ኩባንያዎች ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2023 ባለው ወቅት 2.74 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ማቅረባቸውን አምነስቲ የፓርላማ ሪፖርትን ዋቢ አድርጎ አስፍሯል።
ኩባንያዎቹ በሚያደርጓቸው የአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ተገቢውን ማጣራት እና ሰብዓዊ መብቶችን ሊያከብሩ እንደሚገባ አምነስቲ አሳስቧል።
አምነስቲ የመከላከያ ስርዓቱ በጦርነቱ ጥቅም ላይ መዋላቸውን በተመለከተ ቴክኖሎጂዎቹን አምርተዋል የተባሉትን ኩባንያዎች እና የፈረንሳይ ባለስልጣናትን አነጋግሬ ምላሽ አላገኘሁም ብሏል።
“ፈረንሳይ በወጪ ንግድ ቁጥጥር የመጨረሻውን ተጠቃሚ የክትትል ማረጋገጫን እንዲሁም ጦር መሳሪያዎቹ ወደ ሱዳን እንደማይላኩ ማረጋገጥ ካልቻለች እነዚህን አቅርቦቶች መፍቀድ የለባትም” ብሏል ተቋሙ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዳርፉር አረብ ባልሆኑ ማህበረሰቦች ላይ የዘር ማጽዳት ወንጀል ተፈጽሟል መባሉን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 2004 የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ጥሏል።
አምነስቲ የጦር መሳሪያ ማዕቀቡ በቀሪው ሱዳን እንዲጣል እና የክትትል ስልቱም እንዲጠናከር ጠይቋል።
አምነስቲ ሁሉም አገራት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጦር መሳሪያዎችን ለሱዳን ተዋጊዎች ከማቅረብ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
በጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳግሎ ወይም ሄምቲ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከአንድ ዓመት በላይ በዘለለው በጄኔራል አብደል ፋታል አልቡርሃን ከሚመራው የሱዳን ጦር ጋር እየተፋለመ ይገኛል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉር የዘር ማጽዳት ወንጀል በመፈጸም የተከሰሰ ቢሆንም ቡድኑ በአካባቢው ታጣቂዎች የተፈጸመ ሲል ያስተባብላል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው እና ሚሊዮኖችን ባፈናቀለው የሱዳኑ ጦርነት ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የጦር ወንጀሎችን በመፈጸም ተከሰዋል።