ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሱዳን ጦርነት በታጣቂዎች የተደፈሩ ሴቶች ራሳቸውን እያጠፉ ነው
ማሳሰቢያ፦ ይህ ጽሁፍ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ይዘቶችን አካቷል
በጦርነት በምትታመሰው ሱዳን የሰቆቃውን ዋነኛ ገፈት እየቀመሱ ያሉት የሱዳን ሴቶች በታጣቂዎች ከተደፈሩ በኋላ በርካቶች ራሳቸውን ማጥፋታቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ድርጅቶች አስታውቀዋል።
ከሱዳን ጦር ጋር እየተፋለመ ያለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች በመካለኛው ሱዳን ጀዚራ ግዛት የደፈሯቸው በርካታ ሴቶች ራሳቸውን አጥፍተዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የጅምላ ግድያዎችን ጨምሮ በርካታ “አሰቃቂ የመብት ጥሰቶችን” እየፈጸመ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት አስታውቆ ነበር።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጦር ግንባር ላይ ግስጋሴውን በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ታጣቂዎቹ ይደፍሩናል በሚል ፍራቻ ሕይወታቸውን ለማጥፋት እያሰቡ ካሉ ስድስት ሴቶች ጋር ግንኙነት ያለው አንድ የመብት ተሟጋች ድርጅት ለቢቢሲ ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት በተጨማሪም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች እየፈጸሙት ያለው ወሲባዊ ጥቃት መጨመሩን የገለጸ ሲሆን፣ ኃይሉ በበኩሉ ሪፖርቱን ውድቅ አድርጎ “በማስረጃ ላይ የተመሠረተ አይደለም” ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።
ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት በተቀሰቀሰው የሱዳን ደም አፋሳሹ ለሥልጣን በሚደረግ የእርስ በርስ ፍልሚያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ እንዲሁም ከ11 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑን ተፈናቅለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ሲንዲ ማኬይን በዚህ ሳምንት የፖርት ሱዳን የዕርዳታ ማዕከልን ከጎበኙ በኋላ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ካልተደረሰ አገሪቱ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያጋጥማት እንደሚችል አሳስበዋል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን በረሃብ ሊያልቁ ይችላሉ ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጀዚራ ግዛት የፈጸማቸው የጅምላ ግድያዎች እና መደፈሮች ዘገባዎች የተሰሙት በግዛቲቱ ውስጥ የኃይሉ ከፍተኛ አዛዥ የሆነው አቡ አቅላ ካይካ ከድቶ የሱዳንን ጦር መቀላቀሉን ተከትሎ ነው።
“የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ አቡ አቅላ ካይካ ይቆጣጠራቸው በነበሩ አካባቢዎች የበቀል ጥቃት አካሂዷል። መዝረፍ፣ መግደል እንዲሁም ሴቶች እና ትንንሽ ታዳጊዎችን ደፍረዋል” ሲሉ ስትራቴጂክ ኢንሺየቲቭ ፎር ዊሜን ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ (ሲሃ) የተሰኘው ተቋም ኃላፊ ኃላፊ አል ካሪብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በጦርነቱ ወቅት እየደረሱ ያሉ መደፈሮችን እና ፆታዊ ጥቃቶችን እየመዘገበ ያለው ሲሃ ባለፈው ሳምንት ብቻ በጀዚራ ግዛት ሦስት ሴቶች ራሳቸውን ማጥፋታቸውን አረጋግጧል።
ሁለቱ አል ሴሪሃ በተሰኘች መንደር ነዋሪ የነበሩ ሲሆን፣ ሦስተኛዋ ደግሞ በሩፋ ከተማ መሆኗን ሃላ ያስረዳሉ።
ራሳቸውን ካጠፉት መካከል አንደኛዋ በአባቷ እና በወንድሟ ፊት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች ከደፈሯት በኋላ ራሷን መግደሏን እህቷ ለቢቢሲ ተናግራለች። ሁለቱ ታጣቂዎች በኋላ መገደላቸው ተገልጿል።
አልሰሪሃ በተሰኘችው ግዛት በርካታ አስክሬኖች በብርድ ልብስ ተጠቅልለው የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተጋርተዋል።
ቪዲዮዎቹ የተቀረጹበት ስፍራ አልሰሪሃ በሚገኝ አንድ መስጂድ ግቢ ውስጥ መሆኑን ቢቢሲ መረዳት ችሏል።
በቅርቡ በታጣቂዎች ጥቃት ከተፈጸመባቸው ከ50 በላይ መንደሮች ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች እስካሁን የተመዘገቡት በሁለት መንደሮች መሆኑን ሃላ ተናግረዋል።
ሆኖም የስልክ መስመሮች ችግር ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ቁጥሩ ከፍ ሊል እንደሚችል አክለዋል።
ለሕይወቷ በመስጋት ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀች እና በጀዚራ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነች ግለሰብ ባሎቻቸው በታጣቂዎች ከተገደሉ በኋላ ራሳቸውን ያጠፉ ሴቶችም እንዳሉ ለቢቢሲ አረጋግጣለች።
በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አምስት ወንድሞቿ እና አጎቶቿ የተገደሉባት እና በአልሰሪሃ ነዋሪ የሆነችየተደፈረች አንዲት ሴት ራሷን እንዴት እንዳጠፋች የሚገልጹ መልዕክቶችን ከእህቷ ማግኘቷን ለቢቢሲ ተናግራለች።
በርካታ ሴቶች መደፈርን በመፍራት በጅምላ ራሳቸውን እያጠፉ እንደሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ዘገባዎችን በአካባቢው ባለው የኮሚዩኒኬሽን ችግር ምክንያት እሷም ሆነ ሲሃ ማረጋገጥ ፈታኝ ሆኗል ይላሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ማክሰኞ ዕለት ባወጣው ሪፖርት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሐምሌ ወር ባለው ጊዜ ቢያንስ 400 የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎችን መመዝገባቸውን ይፋ አድርጎ ትክክለኛው አኃዝ ከዚህ ይበልጣል ብሏል።
“በሱዳን እየመዘገብነው ያለው ወሲባዊ ጥቃት ከፍተኛነት አስደንጋጭ ነው” ሲሉ ሪፖርቱን ያጠናቀረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ መሐመድ ቻንዴ ኦትማን ተናግረዋል።
በሪፖርቱ የተካተቱ የተደፈሩ ሴቶች ዕድሜያቸው ከስምንት እስከ 75 ዓመታቸው ሲሆን፣ የጤና ተቋማት በጦርነቱ በመውደማቸው በርካቶቹ የሚያስፈልጋቸውን ህክምና ማግኘት እንዳልቻሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቃል አቀባይ ኒዛር ሳይድ አህመድ በበኩላቸው “እነዚህ ክሶች ሐሰተኛ እንዲሁም በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ አይደለም” ሲሉ አስተባብለዋል።
“በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ለመረዳት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣሪ ቡድን ወደ ሱዳን መላክ አለበት” ሲል ቃል አቀባዩ አክሏል።
ሃላ በበኩላቸው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እያደረገ ካለው ግስጋሴ ጋር ተያይዞ እንደፈራለን ብለው በመስጋት ሕይወታቸውን ለማጥፋት እያሰቡ ካሉ ስድስት ሴቶች ጋር ለመገናኘት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።
ድርጅታቸው ሲሃ ለሴቶቹ የሥነ ልቦና ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ ገልጸው፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው ደኅንነታቸው ወደተጠበቁ ስፍራዎች ለማዛወር ሥራዎችን እየሠሩ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በገዚራ ግዛት በእነዚህ ታጣቂዎች በደቦ የተደፈረች እና አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋት የ13 ዓመት ልጅ ለማገዝ እየሞከሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ታዳጊዋ ከትውልድ ቀየዋ ሰሜናዊ ሩፋ ከተማ ወደ ኒው ሃልፋ እየተጓዘች ሲሆን፣ በአስከፊ ሁኔታ ደም እየፈሰሳት እንደሆነ ተናግረዋል።
በሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በጦሩ መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄኔራል መሃመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
በፖለቲካ ዘላቂ ወዳጅ የለም የሚባለው ማሳያ የሆኑት ሁለቱ ጄነራሎች በአንድ ወቅት በአንድ ጎራ ተሰልፈው መፈንቅለ መንግሥት አካሂደዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሚያደርጉት የበላይነት ፍልሚያ ሱዳንን ብጥብጥ ውስጥ ከቷታል።
የአንድ ወቅት አጋር የአሁን ባላንጣ ጄነራሎች ግንኙነት ረጅም ጊዜን አስቆጥሯል።
ሁለቱም በአውሮፓውያኑ 2003 በሱዳን ምዕራባዊ ክፍል በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ተሳትፈዋል። አገሪቷ በዳርፉር አማጽያን ላይ አካሄድኩት ባለችው የጸረ ሽምግ ውጊያም ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ ይነገራል።
በመጨረሻም በአውሮፓውያኑ 2019 ለወራት ከቀጠለው ህዝባዊ ተቃውሞም በኋላ ጄነራሎቹ አል በሽርን ከስልጣን ለመገርሰስ ተባበሩ።
በዚያው ዓመትም በሲቪል የሚመራና ሉዓላዊው ምክር ቤት በበላይነት የሚያየው የሲቪልና ወታደራዊ ጥምር መንግሥት ለመመስረት ከተቃዋሚዎች ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ምክር ቤቱ በጀነራል ቡርሃን የሚመራ ሲሆን ምክትሉ ደግሞ ጄነራል ሄምቲ ሆኑ።
ይህ አመራር እስከ አውሮፓውያኑ 2021 ድረስ ለሁለት ዓመታትም ዘልቋል። ሆኖም ጦሩ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ጄነራል ቡርሃን የሱዳን መሪ ሲሆኑ ሄምቲም ምክትላቸው ሆኑ።
አሁን ለተነሳው ትርምስ ምክንያቱ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከዋናው ጦር ጋር እንዴት መልሶ ማዋቀር ይችላል በሚለውም ጉዳይ ላይ ከማተኮሩ ጋር የተያያዘ ነው።