ባርቢ የተሰኘው ፊልም የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ያበረታታል በሚል በአረቡ ዓለም ተቃውሞ ገጠመው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባርቢ የተሰኘው በቅርቡ የተለቀቀው የሆሊውድ ፊልም ኩዌት ውስጥ እንዳይታይ ሲታገድ በሌባኖስ ደግሞ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው።
ፊልሙ ማሕበረሰባዊ እሴቶችን ይጥሳል በሚል በአረቡ ዓለም ተቃውሞ እየገጠመው ነው።
ኩዌት “የማሕብረሰቡን ሥነ-ምግባትት” ለመጠበቅ በሚል ፊልሙን ስታግድ ሌባኖስ ደግሞ ባርቢ ፊልም “የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ያበረታታል” ሰለማለቷ የአገሪቱን የባሕል ሚንስትር ዋቢ አድርጎ የአገሪቱ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ሁለቱ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት በተቀረው ዓለም እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘውን ፊልም ያግዱት እንጂ ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ በሌሎች ወግ አጥባቂ በሚባሉ አገራት እየታየ ነው።
ፊልሙ በተለቀቀ በጥቂት ሳምንታት በመላው ዓለም ከ1 ቢሊዮን በላይ ዶላር ማስገባት ችሏል።
የኩዌት የፊልም ቁጥጥር ኃላፊ የሆኑት ላፊ አል-ሱባኤል እንደሚሉት በተለምዶ ፊልሞች የሚታገዱት የኩዌትን ስም የሚያጎድፉ ሲሆኑ ነው ብለዋል።
ኃላፊው ከዚህ ቀደም አግባብ አይደሉም የሚባሉ የፊልሙ ክፍሎች ተቆርጠው እንዲወጡ ይጠይቅ እንደነበረ አስታውሰው አገሪቱ የማትቀበለውን ባሕሪ የሚያበረታታ ፊልም ግን ሙሉ በሙሉ ይታገዳል ብለዋል።
ፊልሙ “ለኩዌት ማሕበረሰብ ባዕድ የሆኑ ሐሳቦችና እምነቶችን ያስተዋውቃል፤ ሕዝባዊ መረጋጋትን ያምሳል” ይላሉ የኩዌት መረጃ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ።
ረቡዕ ዕለት የሌባኖስ ባሕል ሚኒስትር ሞሐመድ ሞርታዳ፤ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ባርቢ የተሰኘውን ፊልም “ለማገድ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ” ጠይቀዋል።
ሚኒስትሩ ይህ ፊልም “ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት እና ሲወለዱ ባገኙት ፆታ አለማመንን [ትራንስሴክሹዋሊቲ] ያበረታታል፤ አባትነትን ያናንቃል፤ የእናትን ኃላፊነት ያጣጥላል፤ አልፎም ቤተሰብ መመሥረትን እና ጋብቻ መፈፀምን ጥያቄ ውስጥ ይከታል” ይላሉ።
የሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ የሌባኖስ ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሃገሪቱ ዳኛ ባሳም ማውላዊ ፊልም ሳንሱር የሚያደርገው ኮሚቴ ባርቢን ድጋሚ እንዲመለከተው ጠይቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሌባኖስ ባሕል ሚኒስትር ሐሳብ ከሺያ እስላማዊ እንቅስቃሴው ቡድን ሔዝቦላ ድጋፍ አግኝቷል።
ባለፈው ወር የሔዝቦላህ መሪ፤ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት ለሌባኖስ ማሕበረሰብ “አደጋ ስለሚደቅን” የአገሪቱ ባለሥልጣን ይህን ድርጊት የሚያበረታቱ ዝግጅቶችን እንዲያግድ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ሳሚር ካሲር የተሰኘው የሌባኖስ መብት ተሟጋች ቡድን ኃላፊ የሆነችው አይማን ማና “ይህ ምክንያታዊነት የጎደለው አጉል እምነት ነው” ስትል ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናገራለች።
ፊልሙ በሌሎች አገራትም ተቃውሞ ገጥሞታል። ለምሳሌ በቪዬትናም ፊልሙ የተዛባ ካርታ በማሳየቱ ተቃውሞ አላጣውም።
ማርጎ ሮቢ እንደ ባርቢ፤ ራያን ጎስሊንግ እንደ ኬን የሚጫወቱበት ይህ ፊልም የሕፃናት መጫወቻ ከሆነችው አሻንጉሊት የተቀዳ፤ ራስን መግለጥን የሚያበረታታ ነው።












