በካሊፎርኒያ አንድ አውሮፕላን ከህንጻ ጋር ተጋጭቶ የሰዎች ህይወት አለፈ

አደጋው የደረሰበት ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, CBS

በአሜሪካ፣ ካሊፎርኒያ ግዛት አንድ አነስተኛ አውሮፕላን ከንግድ ህንጻ ጋር ተጋጭቶ የሁለት ሰዎች ህይወት መቀጠፉን እና 18 ሰዎች መጎዳታቸውን ባለስልጣናቱ አስታወቁ።

አስሩ የተጎዱ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን እና ስምንቱ እዛው አደጋ የደረሰበት ስፍራ ላይ መታከማቸውን የፉለርተን ፖሊስ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በኤክስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አር ቪ 10 የተሰኘው አነስተኛው አውሮፕላን በአገሬው ሰዓት አቆጣጠት ከቀኑ 8፡15 መጋጨቱን የአሜሪካ አቪዬሽን አስተዳደር አስታውቋል።

ባለስልጣናቱ አደጋው እንዴት እንደተከሰተ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም። ህይወታቸው ያለፉት ሁለት ግለሰቦች የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ይሁኑ ወይም ተሳፋሪዎች በሚለው ላይ የተገለጸ ጉዳይ የለም።

ፖሊስ ከአካባቢው ባሉ ህንጻዎች ነዋሪዎችን እያስወጡ መሆኑን ገልጾ ህዝቡም አደጋው ከተከሰተሰበት ስፍራ እንዲርቅ እየጠየቀ ይገኛል።

የአካበባው ምክር ቤት ተወካይ ሉ ኮሪአ በዚህ አደጋ የተመታው የቤት ዕቃዎች ማምረቻ የንግድ ህንጻ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሪአ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳጋሩት ከተጎጂዎቹ በርካታዎቹ የፋብሪካው ሰራተኞች መሆናቸውን አክለዋል።

ከአየር ላይ የተነሱ ፎቶዎች የአውሮፕላኑ የተወሰነ ክፍል ህንጻው ውስጥ መግባቱን ያሳያሉ።

አደጋውን ተከትሎ እሳት የተነሳ ሲሆን የእሳት አደጋ ሰራተኞች ተረባርበው እሳቱን ማጥፋታቸው ተዘግቧል።

ህንጻውን ተሻግሮ ካለ መንገድ የተቀረጹ የደህንነት ምስሎች የእሳት ፍንዳታ ማሳየታቸው የአገር ውስጥ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።

"ሰዎች በአደጋው በከፍተኛ ሁኔታ ድንጋጤ ላይ ናቸው" ሲሉ ማርክ አንደርሰን የተሰኙ የዓይን እማኝ ኬአርሲኤ ለተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

"ከፍተኛ ፍንዳታ ተሰማ። ከዚያም አንደኛው ነዋሪ ወጥቶ ሲያይ ህንጻው በእሳት ተያይዞ አየ" ብለዋል።

አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ስፍራ ከዲዝኒላንድ በ10 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በፉለርተን ማዘጋጃ ቤት አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ነው።

አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ እየተመለሰ እንደነበር የቴሌቪዥን ጣቢያው አክሎ ዘግቧል።

100 ያህል ሰዎች ሚካኤል ኒኮላስ ዲዛይን ከተሰኘው የቤት ዕቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ እንዲወጡ መደረጋቸው ኦሬንጅ ካውንቲ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።

ሁዋኒታ ራሚሬዝ የተባለች የፋብሪካው ሰራተኛ ከፍተኛ የእሳት ነበልባል እሷ ወዳለችበት ስፍራ እየመጣ ከማየቷ በፊት ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ መስማቷን ለጋዜጣው ተናግራለች። "ህልም ነበር የመሰለኝ" ስትል አክላለች።

ባለፉት ሁለት ወራት የአውሮፕላን የመከስከስ አደጋ ሲያጋጥም ይህ ሁለተኛው እንደሆነ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።

ህዳር ወር ላይ አሁን አደጋ ከደረሰው ህንጻ በቅርብ ርቀት አንድ አውሮፕላን ከአንድ ዛፍ ጋር ተጋጭቶ አደጋ ተከስቷል። በዚያ አደጋ ምንም አይነት ከባድ ጉዳት አልደረሰም።