በናዚ ተባባሪነት ተጠርጣሪ የነበሩ የ425 ሺህ ሰዎች ስም ይፋ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Nationaal Archief
ጀርመን ኔዘርላንድን በወረረችበት ወቅት ከናዚዎች ጋር በመተባበር የተጠረጠሩ 425 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ስም ዝርዝር ለመጀመሪያ ጊዜ በበይነ መረብ በይፋ ታተመ።
ዝርዝሩ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በተቋቋመው ልዩ የሕግ ሥርዓት የተመረመሩ ግለሰቦችን አካቷል። ከእነዚህም ውስጥ ከ150 ሺህ የሚበልጡት ቅጣት የተጣለባቸው ናቸው።
ቀደም ሲል የእነዚህ ምርመራዎች ሙሉ መዝገቦች ማግኘት የሚቻለው በሄግ የሚገኘውን የደች ብሔራዊ ቤተ መዛግብት በመጎብኘት ብቻ ነበር።
ማህደሩን ወደ ዲጂታል ለመቀየር ድጋፍ ያደረገው የሂዩገንስ ኢንስቲትዩት ቀደም ያለው አሠራር እአአ ከ1940 እስከ 1945 የቆየውን የኔዘርላንድስን ወረራ ለማጥናት ሁኔታዎችን ከባድ አድርጎት ቆይቷል።
"አባታቸው በጦርነቱ ውስጥ ስለነበራቸው ተሳትፎ ለማወቅ ከሚፈልጉ ልጆች ጀምሮ የትብብር መስኮችን እስከሚመረምሩ የታሪክ ተመራማሪዎች፤ ይህ ማህደር ለአሁኑም ሆነ ለወደፊት ትውልዶች ጠቃሚ ታሪኮችን ይዟል" ይላል የሂዩገንስ ተቋም።
ማህደሩ የጦር ወንጀለኞችን ማህደር፣ በጀርመን የጦር ሃይል አባልነት ተመዝግበው የነበሩ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ የኔዘርላንድስ ሰዎች እና የብሔራዊ ሶሻሊስት ንቅናቄ (ኤንኤስቢ) ወይም የኔዘርላንድ ናዚ ፓርቲን አባላት ናቸው የተባሉትን አካቶ ይዟል።
በህጋዊ ሂደቱ ንጹህ ሆነው የተገኙ ሰዎችን ስምም መያዙ ተነግሯል።
ይህ የሆነበት ምክንያት ማህደሩ ከ1944 ጀምሮ ተባባሪ የሆኑትን ተጠርጣሪዎችን የመረመረው ከልዩ ፍርድ ቤት የመጡ ፋይሎችን ያካተተ ስለሆነ ነው።
የበይነ መረቡ መረጃ የተጠርጣሪዎችን ስም፣ የተወለዱበትን ቀን እና ቦታ የሚይዝ ሲሆን የሚገኙትም የግላዊ ዝርዝር ጉዳዮችን በመጠቀም ብቻ ፈልጎ ማንነታቸውን ማወቅ የሚያስችል ነው።
አንድ ግለሰብ ጥፋተኛ ሆኖ ስለመገኘቱ ወይም በምን አይነት ትብብር ተሳትፎ ስለመጠርጠሩ አይገልጽም።
ተጠቃሚዎች ብሔራዊ ቤተ መዛግብትን ከጎበኙ ግን ይህን መረጃ ለማየት ምን ማሟላት እንዳለባቸው ያሳውቃል። የወረቀት ፋይሎችን ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች አሳማኝ ምክንያቶችን ሊያቀርቡ ይገባል።
ሚስጥራዊነት ያለውን የታሪክ ጊዜን የሚመለከቱ የግል መረጃዎች በነጻ እንዲገኙ መደረጉ ስጋት በመፍጠሩ በበይነ መረብ የሚታተመው መረጃ መጀመሪያ ላይ እንዲገደብ ተደርጓል
"በጣም አስቀያሚ ምላሾች እንዳይኖሩ እፈራለሁ" ሲል አባቱ የኤንኤስቢ አባል እና ሰዎች ወደ ማጎሪያዎች በሚባረሩበት በካምፕ ቬስተርቦርክ ይሠራ እንደነበር የገለጸው የሪንክ ስሜዲንጋ ዲአይቲ ለተባለ መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።
"ይሄ መገመት አለበት። እንደ ማህበራዊ ሙከራ መፍቀድ የለብህም" ብሏል።
የብሔራዊ ቤተ መዛግብት ዳይሬክተር የሆኑት ቶም ደ ስሜት ለዲአይቲ እንደተናገሩት የተባባሪዎች እና የጥቃት ሰለባ ዘመዶች ግምት ውስጥ መግባት አለባቸው።
"ትብብር አሁንም ትልቅ ጉዳት ነው። በዚህ ዙሪያ ግን አልተወራም። ማህደሮች ሲከፈቱ ነውሩ ይጠፋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።
የባህል ሚኒስትር ኢፖ ብራይንስ ለአገሪቱ ፓርላማ በፃፉት ደብዳቤ "የማህደር መከፈት አስቸጋሪ ያለፈውን (የኔዘርላንድስ) ችግርን ለመጋፈጥ እና እንደ ማህበረሰብ ለማለፍ ወሳኝ ነው" ብለዋል።
ከግል መረጃዎች ስጋት አንጻር በበይነ መረብ ላይ የሚቀርበው መረጃ መጠን የተገደበ እንደሚሆን እና ማህደሩን በአካል የሚጎበኙ ሰዎች ቅጂዎችን እንዲወስዱ አይፈቀድላቸውም ብለዋል ። ብሩይንስ ተጨማሪ መረጃ በይፋ እንዲገለጽ ህጉን የመቀየር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የበይነ መረቡ አሁን በህይወት ሊኖሩ የሚችሉ ሰዎች በዝርዝሩ ውስጥ አልተካተቱም ይላል።












