ራሳቸውን እያጠፉ ያሉት የኬንያ ሰልጣኝ ዶክተሮች

የፎቶው ባለመብት, Kiambu county's Department of Health Services
ባለፈው ሳምንት በኬንያ ሪፍት ቫሊ በምትገኝ አንዲት መንደር ውስጥ በርካታ ሰልጣኝ ዶክተሮች በኃዘን ስሜት ተሰባስበዋል።
መንደሯ የተገኙት ራሱን ያጠፋውን የስራ ባልደረባቸውን ለመቅበር ነው።
ስፍራውን የኃዘን ድባብ ሞልቶታል።
ባልንጀሮቹ እየተነሱ የ29 ዓመቱ ዶክተር ፍራንሲስ ንጁኪን ይህችን አለም አልፈልግም ብሎ ማለፍ ልባቸውን እንደሰበረው አንድ በአንድ ተናገሩ።
ፍራንሲስ በነሐሴ ወር ላይ ነበር በአንድ የህዝብ ሆስፒታል በኢንተርንሺፕ ስራ የጀመረው።
ለወራት የሰራበትን ደመወዝ የኬንያ መንግሥት ስላልከፈለው ከፍተኛ ብስጭት እና ድካም እንደተሰማው ቤተሰቦቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፍራንሲስ ራሱን ያጠፋ ብቸኛው ሰልጣኝ ዶክተር አይደለም።
በስራ ያለው ከፍተኛ ውጥረት እና የኢንሹራንስ ሽፋን አለመኖር ጋር በተያያዘ አምስት የህክምና ባለሙያዎች በባለፉት ሁለት ወራት ራሳቸውን እንዳጠፉ የኬንያ የህክምና ባለሙያዎች ማህበር (ኬኤምፒዲዪ) ጸሐፊ የሆኑት ዶክተር ዳብጂ አቴላ ይናገራሉ። ማህበሩ ራሳቸውን የሚያጠፉ የህክምና ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም አልመዘገብኩም ይላል።
በተጨማሪም በዚሁ በአውሮፓውያኑ ዓመት አምስት ያህል የህክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ ማድረጋቸውን ነው ማህበሩ ያስታወቀው።
ፍራንሲስ በመዲናዋ ናይሮቢ አቅራቢያ በሚገኝ ቲካ በሚባል ስፍራ በሚገኝ አንድ የህዝብ ሆስፒታል ልምምዱን (ኢንተርንሺፕ) እየሰራ ነበር።
በከፍተኛ እንቅልፍ እጦት ምክንያት ያቃዠው እንደነበር እንዲሁም ድባቴ ውስጥ መግባቱን አጎቱ ትሩስ ንጁኪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የአራት ወር ደመወዝ መዘግየቱ የአዕምሮ ህመሙን ካባባሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን እና ራሱን ለማጥፋት እንደዳረገውም" ይህችን አለም ከመሰናበቱ በፊት ማስታወሻ ላይ አስፍሯል ይላሉ አጎቱ።
ለቤቱ የበኩር ልጅ የሆነው ፍራንሲስ ከድባቴ ህመም ጋር ይታገል የነበረ ሲሆን ህክምና እየተደረገለት እንደነበር የፖሊስ ሪፖርት አመልክቷል።
ፍራንሲስ በህክምና ባለሙያነት ብቁ ለመሆን አስገዳጅ የሆነውን የአንድ ዓመት ስልጠና መውሰድ ነበረበት። ከፍራንሲስ ጋር በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልጣኝ ዶክተሮችም በተለያዩ የጤና ተቋማት ተመድበዋል።
እነዚህ ሰልጣኝ ዶክተሮች ለአራት ወራት ያህል ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ሲናገሩ መንግሥት የገንዘብ ችግር አለብኝ የሚለውን ዋቢ አድርገው ነው።
ሰልጣኝ ዶክተሮች በኬንያ የህዝብ ሆስፒታሎች መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎትን የሚሸፍኑ ወሳኝ የጤና ግልጋሎት አካል ናቸው። በተለይም የግል የህክምና መድህን መግዛት ለማይችሉ ኬንያውን ዋነኛ መዳረሻ ናቸው።
ሰልጣኝ ዶክተሮች 30 በመቶ ያህሉን የአገሪቱን የህክምና ባለሙያዎች አኃዝ ይይዛሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሚመደቡት በህዝብ ሆስፒታሎች ሲሆን ዶክተሮችም እንዲቆጣጠሯቸው ይደረጋል። አንዳንዶቹ ለ36 ሰዓታት ያህል በቀን ውስጥ የሚሰሩ ሲሆን ለህመምተኞች የሚያስፈልገውን አብዛኛውን የጤና አገልግሎቶች ይሰጣሉ።
"እንደ በርካታ ባልደረቦቹ፣ ፍራንሲስ የቤት ኪራይ እና መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን ለመሸፈን ከፍተኛ ፈተና ሆነበት" ብሏል ማህበሩ ባወጣው መግለጫ።
መንግሥት በሰልጣኝ ዶክተሮች ክፍያ እና የስራ ሁኔታንን በተመለከተ ከማህበሩ ጋር ለረዥም ጊዜ እየተወዛገበ ይገኛል።
የኬንያ መንግሥት የሰልጣኝ ዶክተሮች ወርሃዊ ደመወዝ ወደ 540 ዶላር (68 ሺህ) ብር ገደማ ለመቀነስ ሃሳብ አቅርቧል።
ማህበሩ በበኩሉ ከዓመታት በፊት ከመንግሥት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት 1 ሺህ 600 ዶላር (200 ሺህ ብር) መሆን አለበት ይላል።
ነገር ግን ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግስታቸው ይህንን ያህል ገንዘብ ለመክፈል አቅም የለንም "በአቅማችን መኖር አለብን" ይላሉ።
የስራ ማቆም አድማ ማስፈራሪያ እና እየጨመረ የመጣውን ጫና ተከትሎ መንግሥት ከነሐሴ ወር ጀምሮ ደመወዛቸው ላልተከፈላቸው ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰልጣኝ ዶክተሮች ክፍያ ለመፈጸም 7.4 ሚሊዮን ዶላር ለቋል።
አንዳንድ ሰልጣኝ ዶክተሮች የሚከፈላቸውን ደመወዝ "ሽርፍራፊ" ነው ይላሉ።
"ከስድስት እስከ ሰባት ዓመታት ያህል ተምረን ከዚያ በሰልጣኝነት ለመመደብ በርካታ ወራት መጠበቅ አለብን። ለረዥም ሰዓታት በስራ እናሳልፋለን እናም መንግሥት ሽርፍራፊ ሊከፍለን ወሰነ። በእውነቱ እየተሰቃየን ነው" ሲል በናይሮቢ ምጋባቲ ሆስፒታል ኢንተርን የሆነው ዶክተር አብዲ አዶ ይናገራል።
ዶክተር አብዲ ለተሻለ ክፍያ ከአገር ለመውጣት ከሚዋልሉት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ወጣት የህክምና ባለሙያዎች መካከል አንዱ ነው።
ሌላ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ኢንተርን በበኩሉ "ህይወት ለማዳን እና የሰዎችን ጤና ወደተሻለ ለማድረግ ቃለ መሃላ አድርጌያለሁ ነገር ግን መንግሥት የአገልግሎት መሐላዬን እንዳፈርስ ሁሉንም እያደረገ ነው" ይላል።
የጤና ባለሙያዎች ያለባቸው የስራ ውጥረት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ማሳያው ባለፈው ወር ህይወታቸው ያለፈው ዶክተር ቲሞቱ ሪዩንጉ እንደሆነ አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ዶክተሩ በናይሮቢ የኬንያታ ብሔራዊ ሆስፒታል የሕጻናት ሐኪም ነበር። ለረጅም ሰዓት የቆየ ፈረቃ ከሸፈነ በኋላ ቤቱ ሄዶ ወደቁ። ህይወቱም አለፈ። በእለቱ ከፍተኛ ድካም እየተሰማው እንደነበር ለተቆጣጣሪው ሲያማርር እንደነበር የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የ35 ዓመቱ ወጣት ዶክተር የስኳር ህመምተኛ ሲሆን ለሁለት ዓመታት ያህል ምንም አይነት እረፍት እንዳልወሰደ ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።
በአስከሬኑ ላይ በተደረገ ምርመራ ዶክተሩ ሂፖግላይኬሚያ ተብሎ በሚጠራው የደም ስኳር መጠን ከመደበኛ በታች መውረድ ምክንያት መሞቱ ተረጋግጧል። ከመሞቱ በፊት ለ48 ሰዓታት ያህል ምንም አይነት ምግብ እንዳልቀመሰም አሳይቷል።
በግንቦት ወር የኬንያ መንግሥት ለ56 ቀናት የቆየውን የስራ ማቆም አድማ ለማስቆም ከአንድ የህክምና ማህበር ጋር ስምምነት ላይ ቢደርስም ፤ የሰልጣኝ ዶክተሮች ቁልፍ የሆነው የደመወዝ ጉዳይ እልባት አላገኘም።
የህክምና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ የህዝብ ሆስፒታሎችን እንቅስቃሴ ቀጥ ያደረገው ሲሆን ይህም ሁኔታ በርካታ ህመምተኞች ህይወታቸውን እንዲያጡ ምክንያት ሆኗል።
በሰልጣኝ ዶክተሮች ክፍያ እና የስራ ሁኔታ ላይ የተደረጉ በርካታ ውይይቶች ፍሬ አልባ ሆነዋል።
ባለፈው ሳምንት ኬኤምፒዲዩ መንግሥት በግንቦት ወር የተደረሰውን ስምምነት ሸሯል በሚል 21 ቀን የስራ አቆም አድማ በማወጅ ሁሉም ሰልጣኝ ዶክተሮች በቤታቸው እንዲቆዩ አዟል።
መስከረም ወር ላይ በኪያምቡ ግዛት ጋቱንዱ በተሰኘ ሆስፒታል ውስጥ ኢንተርን የነበረች የ27 ዓመቷ ዶክተር ራሷን አጥፍታለች።
ዶክተር ዴዝሬ ሞራ ኦብዌጊ አድካሚ የ36 ሰዓታት ፈረቃዋን ስትጨርስ የአዕምሮ ጤና ሁኔታዋ መጎዳቱን የስራ ባልደረቦቿ ይናገራሉ።
እሷም የቤት ኪራይ እና መብራት፣ ውሃ እና ሌሎች አገልግሎቶችን መክፈል ተስኗት ነበር።

የኬኤምፒዲዩ የኢንተርንሺፕ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ሙይንዴ ንቱሲ ለህልፈቷ የገንዘብ ችግር እና መርዛማ የስራ ከባቢ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
በቀብር ስነ ስርዓቷ ላይ የዴዝሬ ቤተሰቦች መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወስድ እና ለጠፋው ህይወት ተጠያቂ እንዲሆን መጠየቃቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ኬኤምፒዲዩ በቅርብ ወቅት ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎችን የመዘገበ ሲሆን እነዚህም ቦሲሪ ኒያምቡንንዴ ኢንተርን በኪሲ ረፈራል ሆስፒታል፣ ኮሊንስ ኪፕሮፕ ኮስጌይ በናይሮቢ ዩኒቨርስቲ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ እንዲሁም የ30 ዓመቱ ኢንተርን ኬይዝ ማኮሪ ናቸው።
ወጣት ዶክተሮች የተሻለ ክፍያ እንዲሁም የስራ ሁኔታቸው እንዲቀየር ጫና ለማድረግ 'ፔይ ሜዲካል ኢንተርንስ' በሚል መሪ ቃል በኤክስ ላይ ዘመቻ ጀምረዋል። ብስጭታቸውንም ለመግለጽ ባለፈው ሳምንት ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቢሮ አምርተው ነበር።
ቢቢሲ የኬንያ ባለስልጣናትን አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አልሰጡም።
ነገር ግን መስከረም ወር ላይ እየጨመረ ለመጣው ራስን ማጥፋት ምላሽ የሰጡት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዲቦራ ባራሳ "የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ በርካቶች አብዛኛውን ጊዜ በዝምታ እያሳለፉ ያሉትን ትግሎች የሚያስታውስ ነው" ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ለጤና ባለሙያዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ቦታ እና የአዕምሮ ጤና ላይ ያተኮረ ዕቅድን አስተዋውቃለሁ ብሏል። ይህ እቅድ የድጋፍ ስርዓቶች እንዲጠናከር እና ችግሮችን እየተጋፈጡ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።












