አወዛጋቢው ካንዬ ዌስት ከስምንት ወር ቅጣት በኋላ ወደ ትዊተር ተመለሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትዊተር የካንዬ ዌስት 'ትዊቶች' ክብረ ነክ መልዕክት አላቸው በሚል ገጹን ከዘጋ ከስምንት ወር በኋላ መልሶ እንዲጠቀም ፍቃድ ሰጠ።
ዬ በሚል ስሙ የሚታወቀው አሜሪካዊው ራፐር አመፅ ማነሳሳት አይቻልም የሚለውን የትዊተር ሕግ ጥሷል በሚል ነው የትዊተር ገፁ እንዲዘጋ የተደረገው።
ኢላን መስክ የትዊተርን አርማ ወደ ኤክስ ከቀየረ በኋላ ወደ ገፁ የተመለሰው ካንዬ እስካሁን ምንም አላለም።
ካንዬ ዌስት ለመጨረሻ ጊዜ የለጠፈው ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ነው።
አሜሪካዊው የጥበብ ሰው የትዊተር ገጹ በተዘጋ ወቅት የትዊተር ባለቤት ኢላን መስክ፤ ዬ “አመፅ ማነሳሳት አይፈቀድም የሚለውን ሕግ በመጣሱ” ገፁ ላልተወሰነ ጊዜ ይዘጋል ማለቱ ይታወሳል።
ካንዬ በወቅቱ የተለያዩ ሰዎችና ማሕበረሰቦችን የሚነኩ ፅሑፎችን በትዊተር ገፁ ሲለጥፍ ነበር።
ከእነዚህ መካከል አንደኛው የናዚ ምልክት የሆነው ስዋስቲካ እና የዳዊት ኮከብን ደባልቆ የሚያሳይ ምልክት ነው።
ከዚህ ክስተት ሁለት ወር አስቀድሞ አሜሪካዊው ራፐር በተመሳሳይ ከኢንስታግራም ታግዶ ነበር።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ፀረ-ሴሜቲክ መልዕክቶችን በመለጠፉ ከሁለቱም ማሕበራዊ ትሥሥር መድረኮች ታግዶ ነበር።
አልፎም ኢንስታግራምና ትዊተር መልዕክቱን ከቋታቸው አጥፍተዋል።
በተመሳሳይ ወር ግዙፉ የልብስና ጫማ አምራች ኩባንያ አዲዳስ ከራፐሩ ጋር ያለውን ውል አቋርጧል።
አዲዳስ “ፀረ-ሴሜቲክም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ጥላች አንታገስም” ብሎ ነበር።
ካንዬ ዌስት ባለፈው ዓመት መጋቢት ደቡብ አፍሪካዊ ኮመዲያን ትሬቨር ኖዋን በተመለከተ ዘር ተኮር አፀያፊ ቃል በመጠቀሙ ለ24 ሰዓታት ከኢንስታግራም ታግዶ እንደነበርም ይታወሳል።
ቅዳሜ ዕለት የአወዛጋቢው ሙዚቀኛ ገፅ ድጋሚ ስለመከፈቱ ኢላን መስክም ሆነ ድርጅቱ ኤክስ ያሉት ነገር የለም።
ባለፈው ኅዳር ኢላን መስክ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ገፅ መክፈቱ ይታወሳል።
ቢሊየነሩ የትዊተር ባለቤት ይህን ያደረገው በገዛ ገፁ በሰበሰበው ድምፅ 51.8 በመቶ ተጠቃሚዎች ትራምፕ ወደ ትዊተር እንዲመለሱ እንሻለን ካሉ በኋላ ነው።
ነገር ግን ትራምፕ ወደ ትዊተር የመመለስ ፍላጎት የለኝም ብለዋል።
ካንዬ ዌስት በሰጣቸው ፀረ-ሴሜቲክ አስተያቶች ሳቢያ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮች ያጣ ሲሆን ከበርካታ ኩባንያዎች ጋር ያለውም ውል ተቋርጧል።












