በጃፓን የተከሰተውን ከፍተኛ ርዕደ መሬት ተከትሎ ሱናሚ እንደሚነሳ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

የደረሰው ጉዳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የጃፓን ማዕከል በከፍተኛ ርዕደ መሬት መመታቱን ተከትሎ ነዋሪዎች “በአስቸኳይ እንዲወጡ” ማስጠንቀቂያ ተሰጠ።

በ7.6 የተለካውን ይህንን ከፍተኛ ርዕደ መሬት ተከትሎ ሱናሚ (የውቅያኖስ ውሃን የያዘ አደገኛ አውሎ ነፋስ) እንደሚከሰትም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

ሱናሚው እስከ 5 ጫማ ከፍታ ያለው ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

ማስጠንቀቂያው የተሰጠው የባሕር ዳርቻ በሆነው የላሽኪዋ ኖቶ አካባቢ ነው።

አጎራባቾቹ የኒጋታ እና ቶያማ ግዛቶች ውስጥም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው ከፍታ ወዳለባቸው ቦታዎች እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተላልፏል።

የቴሌቭዥን መሰናዶ አቅራቢ “ቤታችሁ፣ ንብረታችሁ ዋጋ እንዳለው ይገባናል። ነገር ግን ሕይወታችሁ የበለጠ ዋጋ አለው። ከፍታ ወዳለበት ስፍራ በአፋጣኝ ሂዱ” ሲሉ ነው ያስጠነቀቁት።

ርዕደ መሬቱ ሲከሰት ቤታቸውና አውራ ጎዳናዎችም ሲነቃነቁ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን ነዋሪዎች እያጋሩ ነው።

ዛሬ በ90 ደቂቃ ውስጥ በማዕከላዊ ጃፓን እስከ 4.0 እና ከዚያም በላይ የሆኑ 21 ተከታታይ ርዕደ መሬቶች ተከስተዋል።

የጃፓን ብሔራዊ ሜትሮሎጂ እንዳለው ከፍተኛው ልኬት 7.6 ነው።

እአአ ከ2011 ወዲህ ከፍተኛ የሱናሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የመጀመሪያው እንደሆነ መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።

ጃፓን በተደጋጋሚ ሱናሚ ከሚከሰትባቸው አገራት አንዷ ናት። በተከታታይ የርዕደ መሬት ስጋት ስለሚከሰትም በዓለም ግንባር ቀደም የሆነ የሱናሚ ማስጠንቀቂያ ያላት አገር ናት።

ርዕደ መሬቱ በተከሰተበት ስፍራ የሕዝብ አገልግሎት መስጫዎች ተዘግተዋል።

ከ36,000 በላይ የሆኑ ቤቶች መብራት ተቋርጦባቸዋለረ።

የጃፓን ኒውክሌር ባለሥልጣን “በኒውክሌር ማብላያ ምንም ስጋት የለም” ብሏል።

የደረሰው ጉዳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የጃፓን መንግሥት ቃል አቀባይ ዮሺማሳ ሀያሺ፣ ነዋሪዎች ተጨማሪ ርዕደ መሬት ሊከሰት እንደሚችል አውቀው እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።

የደቡብ ኮርያ የሜትሮሎጂ ባለሥልጣን በምሥራቃዊ ክፍል ሱናሚ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ሩሲያም ሱናሚ ሊነሳ ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።

በ2011 ጃፓን 9.0 የደረሰ ርዕደ መሬት ገጥሟት ነበር። ይህንን ተከትሎም በሰሜን ምሥራቅ አካባቢ ከፍተኛ ሱናሚ ተከስቷል። በወቅቱ 18,000 ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ሱናሚው በፉኩሺማ የኒውክሌር ማብላያ ባስከተለው ጉዳት ከቼርኖቤል ቀጥሎ ከባድ ነው የተባለ የኒውክሌር አደጋ ተከስቶም ነበር።