ትራምፕ በኢራን ላይ የወሰዱት እርምጃ በአገር ውስጥ እና በውጭ የጋረጠው መዘዝ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"ሰላም ፈጣሪ" ለመሆን ቃል ገብተው በጥር ወር ነጩን ቤተ መንግስት የተረከቡት ዶናልድ ትራምፕ፤ አሜሪካን በኢራን እና እስራኤል ግጭት ውስጥ በመክተት አወዛጋቢ እርምጃ ወስደዋል።

ስልጣን ከያዙ ወዲህ መንገዳቸውን በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ከማምጣት እያራቁ የሄዱት ትራምፕ፤ አሁን ደግሞ ቀጣናውን አሜሪካ ንቁ ተሳታፊ ወደ ሆነችበት ግዙፍ ጦርነት እየመሩት ነው።

ትራምፕ፤ አሜሪካ ኃይሎች በኢራን ሦስት የኢራን ኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ይፋ ካስታወቁ ከሁለት ሰዓታት ገደማ በኋላ በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው፤ ኦፕሬሽኑን "አስደናቂ ስኬት" ሲሉ ጠርተውታል።

ይህ እርምጃ ኢራን የኒውክሌር ኃይል ባለቤት እንዳትሆን በማድረግ ለዘላቂ ሰላም በር እንደሚከፍት ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ኢራን በበኩሏ እጅጉን በሚጠበቀው ፎርዶ ኒውክሌር ተቋም ላይ የደረሰው ጉዳት አነስተኛ እንደሆነ ተናግራለች። እውነታው በየትኛው ወገን እንዳለ የሚፈታው ጊዜ ይመስላል።

ትራምፕ፤ በምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና በመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ታጅበው ባደረጉት ንግግር፤ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን የማትተው ከሆነ፤ ወደፊት "እጅጉን የከፉ እና በጣም ቀላል" ጥቃቶች ሊያጋጥሟት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

"የተውናቸው ብዙ የጥቃት ዒላማዎች" ነበሩ ያሉት ትራምፕ፤ አሜሪካ እነዚህም ስፍራዎች ላይም "ፈጣን፣ የሰላ እና በብቃት የተሞሉ" ጥቃቶችን እንደምትፈጽም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ዛቻ ቢያሰሙም የአሜሪካ ጦር በኢራን እየተሳተፈ እንዲቀጥል ማድረግ ለአሜሪካ፣ ለቀጣናው እና ለዓለም የከፋ ሁኔታን ሊያመጣ የሚችል እርምጃ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ መካከለኛው ምሥራቅ አሁንም ቢሆን "ጫፍ ላይ" ያለ ቀጣና መሆኑን በመጥቀስ፤ አሜሪካ ግጭቱን ለማባባስ መወሰኗ "የቀውስ አዙሪት" ሊያመጣ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

አያቶላህ አሊ ካህሚኒ እንደዛቱት ኢራን ለተፈጸመባት ጥቃት ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ አሜሪካም ለዚሁ ምላሽ ለመስጠት ልትገደድ ትችላለች።

ወደ ሁለት ቀናት የተቀየሩት "ሁለት ሳምንታት"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ በሳምንቱ መጀመሪያ ሲያደርጉ የነበረው ኢራን "ያለቅድመ ሁኔታ እጅ መስጠት አለባት" የሚል ንግግር፤ ፕሬዝዳንቱን ወደ ኋላ መመለስ የማይችሉበት አጣብቂኝ ውስጥ ከትቷቸዋል።

የራሷን ማስጠንቀቂያ ስትሰጥ የነበረችው ኢራንም ራሷን ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ አስገብታለች።

ጦርነቶች የሚጀምሩት እንዲሁም የሚሳተፉት አካላት አካሄድ ከቁጥጥር ውጪ እና ከሚገመተው በላይ እየሰፋ የሚሄደው በእንዲህ አይነት ሁኔታ ነው።

ሐሙስ ዕለት፤ ትራምፕ ለኢራናውያን የሁለት ሳምንት የማስጠንቀቂያ ጊዜ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም የጊዜ ገደቡ እጅጉን አጥሮ ወደ ሁለት ቀን ተቀይሯል።

ቅዳሜ ምሽት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እርምጃ መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።

ለድርድር የተሰጠው ሁለት ሳምንት ማታለያ ነበር? ኢራናውያን በሳምንቱ መጨረሻ ሀሰተኛ ደህንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ ነው? ወይስ ፕራምፕ ሰላም ለመፍጠር በሾሙት ስቲቭ ዊትኮፍ በኩል ከመጋረጃ ጀርባ ሲደረግ የነበረው ድርድር ፈርሶ ነው?

ከጥቃቱ በኋላ ያለው ሁኔታ እምብዛም አልታወቀም። ይሁን እንጂ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በቴሌቪዥን ባስተላለፏቸው መልዕክቶች የሰላምን በር ለመክፈት ሲሞክሩ ታይተዋል።

ይህ ግን ጉዳዩን በአዎንታዊ መንገድ መመልከት ሊሆን ይችላል። እስራኤላውያን ኢራንን ወታደራዊ አቅም ለማውረድ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም፤ አያቶላው አሁንም በእጃቸው ላይ መሳሪዎች አሉ።

ነገሮች በፍጥነት ሊበላሹ ይችላሉ።

አሁን ምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ የሚጠበቅበት ጊዜ የመጣ ይመስላል።

ኢራን፤ የኒውክሌር ፕሮግራሟ ቁንጮ የሆነውን ፎርዶን ጨምሮ በሦስት ተቋማቶቿ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ምን ዓይነት ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች?

ትራምፕ፤አሜሪካ የፈጸመችው ጥቃት ኢራን ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንድትመጣ ያስገድዳታል የሚል ተስፋ የሰነቁ ይመስላል።

ነገር ግን በእስራኤል ጥቃት ስር ሆኖ ለንግግር ፈቃደኛ ያልሆነ አገር፤ በአሜሪካ ቦንቦች ድብደባ ሀሳቡን ይቀይራል ብሎ መናገር ያዳግታል።

ትራምፕ አሜሪካ ጥቃት ነጠላ እና የተሳካ እርምጃ እንደሆነ እያመላከቱ ይገኛል። ነገሩ ይህል ካልሆነ ግን በድጋሚ ጥቃት እንዲፈጸም የሚደረገው ግፊት ሊጨምር ወይም ፕሬዝዳንቱም ለአነስተኛ ወታደራዊ ድል ከፍ ያለ ፖለቲካዊ ጣጣ የሚያመጣ እርምጃ የወሰዱ ሊያስመስላቸው ይችላል።

"ሰላም ፈጣሪው" ፕሬዝዳንት የተጋረጠባቸው ፖለቲካዊ ወድቀት

ትራምፕ የተጋረጠባቸው ጣጣ የሀገር ውስጥ ፖለቲካ ስጋት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ደንንነት ላይ የሚነሳን ጥያቄን ያካትታል።

አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት እንድትፈጸም የማድረግ ሀሳብ ከዲሞክራቶች ብቻ ሳይሆን "ቅድሚያ ለአሜሪካ" የሚለው የትራምፕ እንቅስቃሴ ደጋፍ ከሆኑ ግለሰቦች ጭምር የሰላ ትችት አስከትሏል።

ፕሬዝዳንቱ ባልተለመደ ሁኔታ በሶስት የቅርብ አማካሪዎቻቸው ታጅበው ብሔራዊ ንግግር ማድረጋቸው በፓርቲው ውስጥ አንድነት እንዳለ ለማመላከት የተደረገ ሙከራ ሊሆን ይችላል።

በተለይም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቫንስ አሜሪካ ይበልጥ ተገደበ የውጭ ፖሊሲ እንዲኖራት የማድረግን ሀሳብ ያቀነቅናል። በቅርቡ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ በመምጣት ትራምፕ አሁንም ቢሆን የጣልቃ ገብነት አካሄድ አራማጅ እንዳልሆነ እንደሆነ በመግለጽ ከደጋፊዎቹ ድጋፍ ሊሰጠው እንደሚገባ መከራከሪያውን አቅርቧል።

አሁኑ ጥቃት የአንድ ጊዜ ድርጊት ከሆነ ትራምፕ በደጋፊዎቻቸው መካከል ያለውን መከፋፈል የማጥበብ እድል ይኖራቸዋል። አሜሪካን ወደ ትልቅ ጦርነት የሚያስገቧት ከሆነ ግን ከአጋሮቹ ተቃውሞ ሊያጋጥማቸው ይችላል።

በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ምንም አዲስ ጦርነት አለመጀመራቸውን በኩራት ለሚናገሩት እና በባለፈው ዓመት የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት የቀድሞ ፕሬዝዳንቶችን ሀገሪቱን የውጭ ሀገር ጦርነት ውስጥ በክተት ሲወቅሱ ለነበሩት ትራምፕ፤ የቅዳሜው ጥቃት ጠብ አጫሪ እርምጃ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እርምጃ ወስደዋል። ይህ እርምጃ ወደየት ሊሄድ ይችላል የሚለው ሙሉ በሙሉ እጃቸው ላይ ነው።