አፍጋኒስታናዊው ታዳጊ በአውሮፕላን ጎማ ሥር ተደብቆ ሕንድ ገባ

ካም ኤር አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ታዳጊው ባልታወቀ ሁኔታ በአውሮፕላኑ ጎማ ሥር ተደብቆ ተጉዟል

የ13 ዓመቱ አፍጋኒስታናዊ ታዳጊ በመንገደኞች አውሮፕላን ጎማ ሥር ተደብቆ ከአፍጋኒስታን መዲና ካቡል ተነስቶ ኒው ደልሂ ገባ።

በሰሜናዊ አፍጋኒስታን በምትገኘው ኩንዱዝ ከተማ ነዋሪ የሆነው ታዳጊው ሰኞ ዕለት አውሮፕላኑ በሕንድ በደልሂ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ካረፈ በኋላ በማኮብኮቢያው ሥፍራ ሲዘዋወር መገኘቱን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ታዳጊው በሕንድ የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር ውሎ ለበርካታ ሰዓታት በፖሊስ ከተጠየቀ በኋላ በተመሳሳይ በረራ ወደ ካቡል እንዲመለስ ተደርጓል።

ታዳጊው አደገኛ ጉዞውን ያደረገው በመጓጓት የተነሳ እንደሆነ በተደጋጋሚ ለባለሥልጣናቱ መናገሩ ተገልጿል።

የሕንድ ማዕከላዊ ኢንደስትሪ የጸጥታ ኃይል ቃል አቀባይ እንዳሉት ታዳጊው የበረራ ቁጥሩ አርኪው- 4401 በሆነው የካም አየር መንገድ አውሮፕላን ምንም በማይታወቅ ሁኔታ ተደብቆ ደልሂ ገብቷል።

ከዚያም በአካባቢው ብቻውን ሲዘዋወር በፖሊስ መገኘቱንና ለጥያቄ መወሰዱን ቃል አቀባዩ አክለዋል።

ታዳጊው በተደጋጋሚ የአውሮፕላኑን የኋላ ጎማ በሚይዘው ክፍል ውስጥ ተደብቆ መጓዙን ለባለሥልጣናት ተናግሯል።

በአውሮፕላኑ ላይ ተጨማሪ ፍተሻ የተደረገ ሲሆን የአየር መንገዱ ሰራተኞች ቀይ ቀለም ያለው ትንሽ የድምጽ ማጉያ [ ስፒከር] አግኝተዋል።

የ13 ዓመቱ ታዳጊ ወደ ኢራን መጓዝ ፈልጎ እንደነበርና የገባበት አውሮፕላን ወደ ቴህራን ሳይሆን ወደ ሕንድ መዲና ደልሂ የሚበር መሆኑን እንደማያውቅ ዘ ኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣ ዘግቧል።

እንደ ጋዜጣው ዘገባ ከሆነ ታዳጊው ካቡል አየር ማረፊያ የተወሰኑ ተሳፋሪዎችን ተከትሎ ሾልኮ በመግባት የአውሮፕላኑን የማረፊያ ጎማ በያዘው ክፍል ውስጥ ነበር ገብቶ የተቀመጠው።

በወቅቱ ይዞት የነበረውም ቀይ ቀለም ያለው የድምጽ ማጉያ ብቻ ነበር።

በቅርብ ጊዜያት ብዙውን ጊዜ አገራቸውን ጥለው ለመውጣት እና ወደ አሜሪካ አሊያም አውሮፓ ለመግባት የተደረጉ ተመሳሳይ ክስተቶች አጋጥመዋል። ሆኖም ከዚህ መሰል አደገኛ ጉዞ በሕይወት የሚተርፉት ጥቂቶች ናቸው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በእንደዚህ ዓይነት መልኩ ተደብቀው የሚጓዙ ሰዎች አውሮፕላኑ በሚያርፍበት ወቅት ራሳቸውን የሚስቱ ሲሆን የአውሮፕላኑ ጎማ በሚወርድበት ወቅትም ለሞት ሊዳርግ የሚችል የመውደቅ አደጋ ያጋጥማቸዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ 2022 የ22 ዓመቱ ኬንያዊ በኔዘርላንድስ አምስተርዳም ከእቃ ጫኝ አውሮፕላን ጎማ ውስጥ በሕይወት መገኘቱ ይታወሳል።