መንደርደሪያውን ስቶ የወጣው አውሮፕላን አብራሪ አልኮል ጠጥቶ እንደነበር ተረጋገጠ

ኤር ፒስ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Air Peace

የምስሉ መግለጫ, ያጋጠመውን ክስተት በተመለከተ የሚካሄዱ ምርመራዎች እንደቀጠሉ ነው

በናይጄሪያ ለማረፍ ሲሞክር በድንገት አቅጣጫውን የሳተው አውሮፕላን አብራሪ እና ረዳቱ የአልኮል መጠጥ ጠጥተው እንደነበር ተረጋገጠ።

የናይጄሪያ የደኅንነት ምርመራ ቢሮ ሐምሌ ወር ላይ በፖርት ሃርኮርት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ካጋጠመው ክስተት ጋር ተያይዞ በአብራሪዎቹ እና በበረራ ቡድኑ አባላት ላይ ምርመራ አድርጓል።

በዚህም አብራሪዎቹ የአልኮል መጠጥ መጠጣታቸውን እንዲሁም የበረራ ቡድኑ አባላትም ካናቢስ የተባለ እፅ መጠቀማቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

ንብረትነቱ የኤር ፒስ በሆነው ቦይንግ 737 አውሮፕላኑ ውስጥ 103 ሰዎች ተሳፍረው የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ባጋጠመው ክስተት የደረሰ ጉዳት የለም።

ኤር ፒስ እንዳለው የ64 ዓመቱ አብራሪ የደኅንነት መመሪያዎችን ባለማክበሩ ከሥራው የተባረረ ሲሆን፣ ረዳት አብራሪው ግን ወደ ሥራው ተመልሷል።

ኤር ፒስ በሰጠው መግለጫ ላይ ረዳት አብራሪው ብሔራዊ ተቆጣጣሪ በሆነው የናይጄሪያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራዎች እና የጤና ምርመራ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ በመገኘቱ ነጻ መውጣቱን ገልጿል።

ሆኖም በደኅንነት ምርመራ ቢሮው የተደረገው ምርመራ አብራሪው እና ረዳት አብራሪው በቅርብ ሰዓት ውስጥ የአልኮል መጠጥ መውሰዳቸውን የሚያመለክት ንጥረ ነገር ተገኝቶባቸው እንደነበር ገልጿል።

የበረራ ቡድኑ አባላትም በካናቢስ ውስጥ የሚገኘው አእምሮን የሚያነቃቃው ቲኤችሲ የተባለ ንጥረ ነገር ተገኝቶባቸዋል።

ኤር ፒስ ግን በመግለጫው ከደኅንነት ምርመራ ቢሮው ተጠቀሰው እፅ እንደተገኘባቸው የሚያሳዩ የደም እና የሌሎች ምርመራ ውጤት እንዳልደረሰው ገልጿል።

"ክስተቱ ካጋጠመ ከአንድ ወር በላይ በኋላ እና አደጋው ከማጋጠሙ ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የበረራ ቡድኑ አባላት አልኮል መጠጣታቸውን በተመለከተ ከደኅንነት ምርመራ ቢሮው ምንም ዓይነት ይፋዊ መረጃ እስካሁን አልደረሰንም" ብሏል።

የአውሮፕላኑ አብራሪ ከ18 ሺህ ሰዓታት በላይ የረራ ልምድ ያለው ሲሆን፣ የ28 ዓመቱ ረዳት አብራሪው ወደ 1200 ሰዓታት የበረራ ሰዓት አለው።

ምርመራው አሁንም በሒደት ላይ እንደሚገኝ የገለጸው የናይጄሪያ የደኅንነት ምርመራ ቢሮ፣ ሥልጠናዎች እና የውስጣዊ ደንቦች አፈፃፀም እንዲሻሻሉ መክሯል።

ለበርካታ ዓመታት በናይጄሪያ ውስጥ የተከሰተ የአውሮፕላን አደጋ ባይኖርም ከመንደርደሪያ የመውጣት እና በሚያርፉበት ወቅት የጎማ መፈንዳት ክስተቶች አጋጥመዋል።

ከሳምንት በፊት የአቪዬሽን ባለሥልጣናት የአውሮፕላን ደኅንነትን ለማሻሻል ያለመ አዲስ የበረራ መረጃ ማዕከል የከፈቱ ሲሆን፣ አጋር ድርጅቶች ግን ተጨማሪ የደኅንነት መጠበቂያ እርምጃዎች እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች በዘርፉ ውስጥ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል።