"ከፍራስራሽ ውስጥ ነው የወጣሁት" ከሕንድ የአውሮፕላን አደጋ የተረፈው ብቸኛው መንገደኛ

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ከአውሮፕላን አደጋ የተረፈው ራምሽን ሆስፒታል ሄደው ሲጠይቁ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ከአውሮፕላን አደጋ የተረፈው ራምሽን ሆስፒታል ሄደው ሲጠይቁ

ሐሙስ ዕለት ካጋጠመው አሰቃቂው የሕንድ የመንገደኞች አውሮፕላን አደጋ አንድ ብሪታኒያዊ መንገደኛ ብቻ በሕይወት ተርፏል።

ከ242 ተሳፋሪዎች ውስጥ እርሱ ብቻ የመትረፉ ዜና የዓለም መገናኛ ብዙኃን አርዕስት ሆኗል፤ በርካቶችን አስደንቋል።

ግለሰቡ በአውሮፕላኑ ዋና አካል ክፍል ላይ ባገኘው ክፍተት እንዴት መውጣት እንደቻለም በሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ ለሕንድ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

ዕድለኛው ቪሽዋሽኩማር ራምሽ "የመቀመጫ ቀበቶዬን መፍታት ቻልኩ። ያገኘሁትን የአውሮፕላኑን ክፍተት በእግሬ ገፋሁት። ከዚያም መውጣት ቻልኩ" ብሏል።

የ40 ዓመቱ ራምሽ ወደ ለንደን ለመጓዝ ተነስቶ በነበረው ቦይንግ 787 አውሮፕላን ውስጥ ተቀምጦ የነበረው በ11ኤ የወንበር ቁጥር ላይ ነበር።

ሆኖም አውሮፕላኑ ለበረራ ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ነበር ሐሙስ ዕለት በምዕራባዊ ሕንድ በሚገኘው አህመዳባድ ከተማ የተከሰከሰው።

የአውሮፕላኑ ባለቤት የሆነው 'ኤይር ኢንዲያ' እንዳለው ከራምሽ በስተቀር 169 የሕንድ እና 52 የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎችን ጨምሮ ሁሉም መንገደኞች እና የበረራ ቡድን አባላት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

እስካሁን ከ200 በላይ አስክሬኖች ተገኝተዋል። ሆኖም ከእነዚህ መካከል ምን ያህሎቹ የአውሮፕላኑ መንገደኞች፣ ምን ያህሎቹ ደግሞ አደጋው በደረሰበት ሥፍራ የነበሩ ሰዎች እንደሆኑ ግልጽ አይደለም።

በሕክምና ላይ የሚገኘው ራምሽ አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ "ውስጡ የነበሩ መብራቶች ያለማቋረጥ ሲበሩ ነበር" ብሏል።

ከአምስት እስከ 10 ሰኮንድ ለሚሆን ጊዜም አውሮፕላኑ አየር ላይ የቆመ ይመስል እንደነበር ራምሽ ገልጿል።

"አውሮፕላኑ ውስጥ አረንጓዴ እና ነጭ መብራቶች መብራት ጀመሩ። ከዚያም በድንገት ከሕንፃ ጋር ተጋጭቶ ፈነዳ" ብሏል ምስክርነቱን ሲሰጥ።

የቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር አውሮፕላን የወደቀበት ሕንፃ የብይራምጅ ጅጅብሆይ ሜዲካል ኮሌጅ እና ሲቪል ሆስፒታል ዶክተሮች ማደሪያ ነው።

ባለትዳር እና የአራት ዓመት ልጅ አባት የሆነው ራምሽ እንደሚለው እርሱ የተቀመጠበት የአውሮፕላኑ ክፍል ከሕንፃው ጋር ሳይጋጭ ለወለሉ ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ ነበር ያረፈው።

"በሩ ሲሰበር የሆነ ክፍተት ተመለከትኩ፣ በዚያ ለመውጣት ሞከርኩ፤ ተሳካልኝ" ብሏል።

እርሱ ከነበረበት በተቃራኒ አቅጣጫ ያለው የአውሮፕላኑ ክፍል ወደ ግድግዳው የተጠጋ በመሆኑና በመጋጨቱ ማንም መውጣት እንዳልቻለም ራምሽ ተናግሯል።

አውሮፕላኑ የወደቀበት የሕንጻው ክፍል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አውሮፕላኑ የወደቀበት የሕንጻው ክፍል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአደጋው ምክንያት እስካሁን አልታወቀም። ባለሥልጣናት ከአደጋው ሥፍራ የበረራ መረጃዎችን የያዘ አንድ ጥቁር ሳጥን (ብላክ ቦክስ) መገኘቱን ገልጸዋል። ይህም ለመርማሪዎች ስለክስተቱ ተጨማሪ መረጃዎችን ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ምሥሎች ራምሽ በጭስ ከታፈነው የአደጋው ሥፍራ እየተራመደ ወደ አምቡላንስ ሲሄድ አሳይተዋል።

ከፍርስራሽ ውስጥ በሕይወት መውጣቱን ማመን እንዳልቻለም ለሕንድ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

"የበረራ አስተናጆች እና አጠገቤ የነበሩ ሁለት ሰዎች ፊት ለፊቴ ሲሞቱ በዓይኔ በብረቱ ተመልክቻለሁ። እኔም የምሞት መስሎኝ ነበር። ግን ዓይኖቼን ከፍቼ አካባቢዬን ስመለከት በሕይወት መኖሬን ተረዳሁ" ብሏል።

"ግን አሁንም ቢሆን እንዴት እንደተረፍኩ አላወቅኩም። ከፍርስራሽ ውስጥ ነው የወጣሁት።"

ለራማሽ የሕክምና ክትትል እያደረጉት ያሉት ዶክተር ዲሃቫል ጋምቲ እንዳሉት ራምሽ በመላ አካሉ ላይ በርካታ ጉዳቶች እንዳጋጠሙት አያውቅም ነበር። ለዚያም ነው አደጋ ያጋጠመው የማይመስለው ብለዋል።

አርብ ጠዋት ላይ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ አደጋው የደረሰበትን ሥፍራ የጎበኙ ሲሆን፣ ራማሽን ጨምሮ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች እንዲሁም የተጎጂ ቤተሰቦችን ለመጠየቅ ወደ ሆስፒታል አቅንተው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ እንዳሉትም የውጭ ጉዳይ ቢሮ ድጋፍ ለመስጠት ከራምሽ ጋር መገናኘቱን ገልጿል።

ራምሽ የተወለደው በሕንድ ሲሆን፣ ከ22 ዓመታት በፊት ጀምሮ ኑሮውን በዩናይትድ ኪንግደም አድርጎ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።ወንድሙ አጃይም በአውሮፕላኑ ውስጥ አብሮት ነበር።

የቅርብ ዘመዳቸው ሂረን ካንቲላል እንዳለው ወንድማማቾቹ ለተወሰኑ ወራት እረፍት ሕንድ ነበሩ።

ራምሽ አርብ ጠዋት ላይ መራመድ እና ቤተሰቦቹን በትክክል ማነጋገር እንደቻለ ካንቲላል ተናግሯል።

ራምሽ በሚቻለው ፍጥነት ከሆስፒታል ወጥቶ ማግኘት እንደሚፈልጉም ገልጿል።

ጨምሮም ቤተሰቦቹ ወደ ሕንድ እንዲመጡ እና እንዲጎበኙት ከብሪታኒያ መንግሥት ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚፈልጉ ተናግሯል።

ቢቢሲ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ቢሮን ከራምሽ ጋር ተገናኝቶ እንደሆነ ጠይቆ ነበር።

የቢሮው ቃል አቀባይ ከራምሽ ጋር መገናኘታቸውን ገልጸው "የቆንስላ ሠራተኞቻችን የበረራ ቁጥር ኤአይ171 በሆነው ኤይር ኢንዲያ አውሮፕላን አደጋ ሰለባ የሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ቤተሰቦችን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው" ብለዋል።

አደጋውን ተከትሎም የውጭ ጉዳይ ቢሮው የኤምባሲ እርዳታ ለሚፈልጉ እንዲሁም ስለጓደኞቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ሁኔታ ማወቅ ለሚፈልጉ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሕንድ ለሚኖሩ ዜጎች የእርዳታ መስጫ መስመሮችን ዘርግቷል።