በሕንድ አውሮፕላን አደጋ የሞቱት እነማን ናቸው?

የአውሮፕላኑ ስብርባሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሕንድ አውሮፕላን አደጋ ተሳፍረው ከነበሩ መንገደኞች መካከል ከአንድ ሰው በስተቀር ሁሉም ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።

አውሮፕላኑ ትናንት ሐሙስ ወደ ለንደን ጋትዊክ አየር ማረፊያ ለማቅናት ከተነሳ በኋላ ነበር በምዕራባዊ ሕንድ የተከሰከሰው።

በአውሮፕላኑ ውስጥ 169 የሕንድ፣ ሰባት የፖርቹጋል እና አንድ የካናዳ ዜጎችን ጨምሮ 242 መንገደኞች እና የበረራ አስተናጋጆች ተሳፍረው ነበር።

ከዚህ አደጋ ቪሽዋሽኩማር ራምሽ የተባለ አንድ እንግሊዛዊ መንገደኛ ብቻ መትረፍ የቻለ ሲሆን በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገለት ይገኛል።

አደጋው በደረሰበት አህመዳባድ አካባቢ የነበሩ ሰዎችም ሳይሞቱ እንዳልቀረ ቀደም ብሎ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ስለ አደጋው ዝርዝር መረጃዎች እየወጡ ቢሆንም እስካሁን በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት መካከል እነዚህ እንደሚገኙበት ቢቢሲ አረጋግጧል።

የናናባዋ ቤተሰብ

አኪል ናናባዋ እና ሃና ቮራጅ ከልጃቸው ሳራ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Family Handout

የምስሉ መግለጫ, አኪል ናናባዋ እና ሃና ቮራጅ ከልጃቸው ሳራ ጋር ወደ ሕንድ የተጓዙት ስለጉዟቸው መረጃ ሳይሰጡ ነበር።

በአደጋው ሕይወታቸውን እንዳጡ ከተነገረው እግሊዛውያን መካከል በግሎውሲስተር ነዋሪ የነበሩ ሦስት የአንድ ቤተሰብ አባላት ይገኙበታል።

አኪል ናናባዋ እና ባለቤቱ ሃና ቮራጅ ከአራት ዓመት ልጃቸው ሳራ ናናባዋ ጋር በአውሮፕላኑ ተሳፍረው ነበር።

የግሎውሲስተር ሙስሊም ማኅበረሰብ በሰጠው መግለጫም በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።

" የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦችን የሚያፅናና ምንም ዓይነት ቃል የለም።ሆኖም በመላው ዓለም ካሉ ማህበረሰቦች በሚመጣ ትብብር ቤተሰቦቻቸው እንዲፅናናኑ እና እንዲበረቱ እንፀልያለን" ብሏል በመግለጫው።

አዳም እና ሃሲና ታጁ እንዲሁም የልጃቸው ባል አልታፍሁሴን

የ72 ዓመት አዛውንቱ አዳም ታጁ እና የ70 ዓመቷ ባለቤታቸው ሃሲና ከ51 ዓመቱ የልጃቸው ባል አልታፍሁሴን ጋር ሆነው ነበር ወደ ለንደን ለመጓዝ ከአህመዳባድ የተነሱት።ሁሉም በለንደን ከተማ ውስጥ ነበር የሚኖሩት።

የጥንዶቹ የልጅ ልጅ የሆነችው አማራህ ታጁ በአደጋው እጅግ መደናገጧንና ቤተሰቦቿን ማጣቷን ማመን እንዳልቻለች ተናግራለች።

እርሷ እንደምትለው ስለ አደጋው መረጃዎች የደረሳቸው አባቷ አልታፍ ታጁ እህታቸውን ለመቀበል ወደ ለንደን እያሽከረከሩ ሳለ ነበር።

ፊዮንጋል እና ጀሚ ግሪንሎው - ሚክ

ፊዮንጋል እና ጀሚ ግሪንሎው- ሚክ ከበረራ በፊት በኢንስታግራም ላይ ያጋሩት ልጥፍ

የፎቶው ባለመብት, Instagram

የምስሉ መግለጫ, ፊዮንጋል እና ጀሚ ግሪንሎው - ሚክ ከበረራ በፊት በኢንስታግራም ላይ ያጋሩት ልጥፍ

ፊዮንጋል እና ጃሚ ግሪንሎው - ሚክ በጋብቻ የተሳሰሩ እንግሊዛዊ ጥንዶች ናቸው።በለንደን መንፈሳዊ የጤና ማዕከል አላቸው።

ጥንዶቹ አደጋው ከመድረሱ ቀደም ብሎ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ከአህመዳባድ አየር ማረፊያ ሊሳፈሩ መሆኑን በቪዲዮ አጋርተው ነበር።

በቪዲዮው ላይ ጥንዶቹ ሲስቁ እና ስለሕንዱ ጉዟቸው እርስ በርስ ሲቀላለዱ ነበር።

የስይድ ቤተሰብ

ጀቭድ ስይድ እና ሜሪየም ስይድ ከሁለት ልጆቻቸው ጋር በአውሮፕላን ውስጥ ተሳፍረው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Facebook

የምስሉ መግለጫ, ጀቭድ ስይድ እና ሜሪየም ስይድ ከሁለት ልጆቻቸው ጋር በአውሮፕላን ውስጥ ተሳፍረው ነበር።

አጃይ ኩማር ራምሽ

አጃይ ኩማር ራምሽ በአውሮፕላኑ ተሳፍሮ የነበረ ሲሆን በሕይወት ከተረፈው እንግሊዛዊው ወንድሙ ቪሽዋሽኩማር ጋር ጎን ለጎን ነበር የተቀመጠው።

የቅርብ ቤተሰባቸው የሆኑት አጃይ ቫልጅ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቪሽዋሽኩማር ራምሽ ከአደጋው በኋላ ወደ ቤተሰቦቹ ደውሎ ደኅና እንደሆነ የተናገረ ሲሆን ወንድሙ ግን የት እንዳለ እንደማያውቅ ገልጿል።

ቪጃይ ሩፓኒ

ቪጃይ ሩፓኒ

የፎቶው ባለመብት, Hindustan Times via Getty Images

ቪጃይ ሩፓኒ በጉጃራት ግዛት የቀድሞ ሚኒስትር ነበሩ።ቪጃይ በአደጋው መሞታቸውን የአገሪቷ ሲቪል አቪየሽን ሚኒስትር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ሩፓኒ የምዕራባዊ ሕንድ ግዛትን ከአውሮፓውያኑ 2016 እስከ 2021 ድረስ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

የገዥው ብሃራቲያ ጃናታፓርቲ (ቢጄፒ) ፓርቲም አባል ነበሩ።

ሲንግሰን

ሲንግሰን የበረራ ቁጥሩ 171 በሆነው ኤርኢንዲያ የበረራ ቡድን አባል እንደነበረች ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።

በአህመዳባድ በሚገኘው የሲቪል ሆስፒታል አካባቢ የነበረው የቅርብ ዘመድ ቲ ታንግሊንጎ ሃኦኪፕ፣ ስለእርሷ መረጃ ለማግኘት እየሞከረ እንደነበርና እንዳልተሳካለት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጨምሮም ሲንግሰን በቤተሰቧ ውስጥ የገቢ ምንጭ ያላት እርሷ ብቻ ስለሆነች ሙሉ በሙሉ በእርሷ ላይ ጥገኛ የሆኑትን እናቷን እና ወንድሟን ታስዳድር እንደነበር ገልጿል።