ከ240 በላይ ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ለንደን እየበረረ የነበረ የሕንድ አውሮፕላን ተከሰከሰ

የእሳት አደጋ ሠራተኞች በአውሮፕላን አደጋው የተፈጠረን ቃጠሎ ለማጥፋት ሲጥሩ

የፎቶው ባለመብት, AP

በሕንድ ከ240 በላይ መንገደኞችን ይዞ ወደ ለንደን ለመብረር የተነሳ አውሮፕላን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ ተከሰከሰ።

በምዕራብ ሕንድ ከምትገኘው አህመዳባድ ከተማ ተነስቶ በረራ የጀመረው አውሮፕላኑ በለንደን ወደሚገኘው ጋትዊክ አውሮፕላን ማረፊያ የሚበር ነበር ተብሏል።

የአውሮፕላኑ ባለቤት ኤር ኢንዲያ ባወጣው መግለጫ "ዛሬ ከአህመዳባድ ለንደን ጋትዊክን የሚበረው AI 171 አደጋ አጋጥሞታል" ሲል አስታውቋል።

የሕንድ አቪዬሽን ሚኒስትር፣ ኪንጃራፑ ራም ሞሃን ናይዱ በአህመዳባድ በደረሰው አደጋ "በጣም ደንግጫለሁ፤ አዝኛለሁ" ብለዋል።

አክለውም "የአቪዬሽን እና የድንገተኛ አደጋ እርዳታ ሰጪ ተቋማት ፈጣን እና የተቀናጀ እርምጃ እንዲወስዱ መመሪያ ሰጥቻለሁ" ብለዋል።

በሕንድ ከተከሰከሰው አውሮፕላን ቃጠሎ የሚወጣ ጭስ

የፎቶው ባለመብት, AP

"የነፍስ አድን ሠራተኞች የሕክምና እና የእርዳታ ድጋፍ ወደ ቦታው እንዲደርሱ ለማድረግ ሁሉም ጥረት እየተደረገ ነው" ሲሉም አክለዋል።

አውሮፕላኑ በአየር ማረፊያው አቅራቢያ መከስከሱን የፖሊስ እና የአየር መንገዱ ባለሥልጣናት ገልፀዋል።

እስካሁን ድረስ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ስለመኖራቸው ምንም የተባለ ነገር የለም።

አውሮፕላኑ ዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ወደ ሚገኘው ጋትዊክ አየር ማረፊያ በረራ የሚያደርግ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን፣ የተከሰከሰው በአየር መንገዱ አቅራቢያ በሰዎች መኖሪያ አካባቢ ነው ተብሏል።

የሕንድ መገናኛ ብዙኃን በእሳት የተያያዘ የአውሮፕላኑ ስብርባሪ እያሳዩ ሲሆን፣ ከአየር ማረፊያው አቅራቢያ ሰማዩ በጭስ ተሸፍኖ ይታያል።

በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን ከአደጋው ስፍራ በማውጣት በአምቡላንስ ሲጓጓዙ የሚያሳዩ ምሥሎች የመገናኛ ብዙኃን እያወጡነው።

በአውሮፕላኑ ላይ 244 ሰዎች መሳፈራቸውን ኤኤንአይ የተባለ የሕንድ መገናኛ ብዙኃን የጉጅራት ግዛት ፖሊስን ጠቅሶ ዘግቧል።

የአገሪቱ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን አውሮፕላኑ 232 መንገደኞችን እና 12 የበረራ ሠራተኞችን ማሳፈሩን አስታውቋል።