ኒውካስል ከአርሰናል እና የሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

ስድስተኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ ይከናወናሉ።
ቅዳሜ ክሪስታል ፓላስ ሊቨርፑልን፤ እሑድ ደግሞ ኒውካስል አርሰናልን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ ተጠባቂ ናቸው።
"ሊቨርፑል አሳማኝ ባልሆነ መልኩም ቢሆንም አሸንፎ ሲወጣ ስለነበር ይህ ጨዋታ የሚፈተንበት ይሆናል" ብሏል የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን።
ሱተን እነዚህን ጨምሮ የሳምንቱን ጨዋታዎች ግምት እንደሚከተለው አስቀምጧል።
ቅዳሜ

ብሬንትፈርድ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ባለፈው ዓመት ብሬንትፎርድ 4 ለ 3 አሸንፎ ነበር። ዘንድሮ ብሪያን ምቡሞን ለማንቸስተር ሽጦ አስልጣኙ የነበሩትን ቶማስ ፍራንክን ለቶተንሃም አስርክቦ ነው የሚቀርበው።
የኬት አንድሪውስም ሆነ የሩበን አሞሪምን ቡድን መገመት አስቸጋሪ ነው።
ዩናይትድ ግብ ዕድሎችን በመፍጠር በሊጉ ቀዳሚ ቢሆንም እስካሁን አልተጠቀመበትም።
ግምት፡ 1 - 1
ቼልሲ ከ ብራይተን
ቼልሲ ከማንቸስተር ዩናይትድ እና ባየር ሙኒክ ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ከባድ ጨዋታ ይጠብቀዋል።
የኤንዞ ማሬስካ ቡድን አሳማኝ መሆን ካለመቻሉም በላይ የኮል ፓልመር መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።
ብራይተን ጎሎችን ማስቆጠር ቢችልም ወጥ አቋም ማሳየት ግን ተስኖታል።
ብዙዎቹ ቡድኑ የቀድሞ ተጫዋቾችን ወደ ቼልሲ አቅንተዋል።
ግምት፡ 1 - 1
ክሪታል ፓላስ ከ ሊቨርፑል
ሊቨርፑል ወደ ሙሉ አቋሙ በቅርቡ ተመልሶ ቡድኖችን ማሽመድመድ እንደሚጀምር አስባለሁ።
ይህ ግን ከፓላስ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ይሆናል ብዬ አልገምትም።
ፓላስ በኮሚኒቲ ሺልድ በፍጹም ቅጣት ምት አሸንፏቸው እንደነበር ይታወሳል።
ግምት፡ 0 - 0
ሊድስ ከ በርንመዝ
ሊድስ ባለፈው ሳምንት አስደናቂ በሆነ መልኩ ዎልቭስን አሸንፏል። በውድድር ዓመቱ የሚኖራቸውንም ጉዞ የሚያመላክት ነው።
በርንመዝ ባለፈው ሳምንት ከኒውካስል ጋር ጥሩ ባይሆንም ቡድኑ የጎል ዕድሎችን ይፈጥራል።
ግምት፡ 1 - 2

ማንቸስተር ሲቲ ከ በርንሌይ
ፔፕ ጋርሪዲዮላ ባለፈው ሳምንት ከአርሰናል ጋር መከላከልን የመረጠ ሲሆን አሁን ደግሞ ተረኛው በርንሌይ ይሆናል።
በርንሌይ ከሊቨርፑል እና ማንቸስተር ዩናይትደ ጋር ለመፎካከር ቢሞክሩም በዚህ ጨዋታ ግን ሲቲን መቋቋም አይችሉም
ግምት፡ 3 - 0
ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ሰንደርላንድ
የፎረስቱ አለቃ አንጅ ፖስትኮግሉ እስካሁን አንድም ጨዋታ ካለማሸነፋቸውም በላይ አሁንም ከባድ ጨዋታ ይጠብቃቸዋል።
ሰንድርላንድ በ10 ተጫዋች ከአስቶን ቪላ ጋር አቻ መለያየት ችሏል። በደንብ የተደራጀ ቡድን ነው።
ሃቢብ ዲያራ በጉዳት ባይሰለፍም ቡድኑን ጠንካራ መሆኑን አሳይቷል።
ሆኖም በዚህ ጨዋታ አንጅ የመጀመሪያ ድላቸውን የሚያስመዘግቡ ይመስለኛል።
ግምት፡ 2 - 1
ቶተንሃም ከ ዎልቭስ
ዎልቭስ ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፏል።
ቶተንሃም ባለፈው ሳምንት ከብራይተን ጋር አቻ በመውጣት ያለውን አልሸነፍ ባይነት አሳይቷል።
በቻምፒዮንስ ሊግም ጥሩ ሳይሆኑ ማሸነፍ ችለዋል።
ግምት፡ 1 - 0
አስቶን ቪላ ከ ፉልሃም
ቪላ ባለፈው ሳምንት ከሰንደርላንድ ጋር ጥሩ አልነበረም።
ቡድኑ በአንድ ተጫዋች በልጦም ውህደት አይታይበትም ነበር።
ፉልሃም በተከታታይ ሊድስ እና ብሬንትፎርድን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን ቪላ ደግሞ ደካማ አጀማመሩን የሚቀይር አይመስልም።
ቪላ ውጤቱን ለመቀየር እስካሁን ካሳየው በላይ መሥራት ይጠበቅበታል።
ግምት፡ 1 - 1

ኒውካስል ከ አርሰናል
ኒውካስል በ2023 በሜዳው አርሰናልን ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ውጥረት የነገሰበት ሆኗል።
ባለፉት ሦስት የሴንት ጀምስ ፓርክ ጨዋታዎች አርሰናል ተሸንፏል።
መድፈኞቹ ይህንን ጨዋታ ካላሸነፉ ከወዲሁ ከመሪዎቹ መራቅ ይጀምራሉ።
ሚኬል አርቴታ በዚህ አይነት ጨዋታዎች ጥንቃቄን መምረጡ የሚያዋጣ አይመስለም።
ቡካዮ ሳካ እና ኤዜ ጥሩ ከሆኑ ማሸነፍ ይችላሉ። ማርቲኔሊም መረሳት የሌለበት ቢሆንም ዋናው ጉዳይ ግን የአርቴታ አጨዋወት ነው።
ግምት፡ 1 - 2
ኤቨርተን ከ ዌስት ሃም
የዌስት ሃም ደጋፊዎች እንዲለቅ የጠየቁት ዴቪድ ሞዬስ በዚህ ጨዋታ ካሸነፈ ግርሃም ፖተር ከኃላፊነቱ ሊነሳ ይችላል።
ኤቨርተን የጎል አስቆጣሪዎች እጥረት ቢኖርበትም የማሸንፍ ዕድል አለው።
ዌስት ሃሞች ለመፎካከር የሚሆን ወኔ ያላቸው አይመስልም።
ግምት፡ 2 - 0












