ታዋቂው ብሪታኒያዊ ተዋናይ ኢድሪስ ኤልባ ለምን ወደ አፍሪካ መመለስ ፈለገ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብሪታኒያዊው ተዋናይ ኢድሪስ ኤልባ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ወደ አፍሪካ ጠቅልሎ በመመለስ የአህጉሪቱን የሲኒማ ኢንዱስትሪ ለማገዝ ዕቅድ እንዳለው ለቢቢሲ ገልጿል።
የ52 ዓመቱ ተዋናይ በታንዛኒያ፣ ዛንዚባር እንዲሁም በጋና ዋና ከተማ አክራ የፊልም ስቱዲዮዎችን ለመገንባት ዕቅድ እንዳለውም አስታውቋል።
በብሪታኒያ ለንደን የተወለደው እና ከአፍሪካ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ኤልባ እናቱ ጋናዊ ሲሆኑ፣ የአባቱ የዘር ሐረግ ደግሞ ከሴራሊዮን የሚመዘዝ ነው።
‘አቬንጀርስ’ን ጨምሮ በበርካታ ማርቭልስ ፊልሞች ላይ የተወነው ኤልባ በማደግ ላይ ባለው የፊልም ሥራ ውስጥ አፍሪካውያን የራሳቸውን ታሪክ ራሳቸው መናገራቸው ወሳኝ ነው ይላል።
በጋና አክራ በነበረ ስብሰባ ላይ በተገኘበት ወቅት በሰጠው በዚህ ቃለ ምልልስ ኢድሪስ ኤልባ “እዚህ መጥቶ ለመኖር ወስኛለሁ፤ ሀሳብ አይደለም በርግጥ የሚሆን ነገር ነው” ብሏል።
“ምናልባት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት፣ አልያም 10 ዓመት ውስጥ መጥቼ መኖር እጀምራለሁ፤ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ። እዚህ ያለሁት የፊልሙን ኢንዱስትሪ ለማጠናከር ነው፤ ያ የአስር ዓመት ሂደት ነው። ከባሕር ማዶ ሆኜ ያንን ማድረግ አልችልም፤ በአፍሪካ፣ በአህጉሪቱ ውስጥ መሆን አለብኝ።”
ኢድሪስ የአፍሪካውያን ወንድማማችነትን (ፓን አፍሪካኒዝምን) ለመደገፍ በሚል አንድ አገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ እንደማይኖር ገልጿል።
“አክራ፣ ፍሪታውን [የሴራሊዮን ዋና ከተማ] እኖራለሁ። ዛንዚባርም እኖራለሁ። ተረኮች የሚናገሩበት ቦታ ሁሉ ሄጄ ለመኖር እሞክራለሁ፤ ያ በጣም አስፈላጊ ነው።”
ኢድሪስ ኤልባ ካሉት ግቦች አንዱ አክራ በሚገኘው የፊልም ስቱዲዮው አንድ ቀን ፊልም መሥራት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“የራስን ታሪክ በራስ መተረክ”
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 በሎንግ ወክ ቱ ፍሪደም ፊልም ላይ የፀረ አፓርታይድ ትግል መሪ ኔልሰን ማንዴላን ሆኖ የተወነው ኢድሪስ ኤልባ አፍሪካውያን በፊልም ሥራ ውስጥ ማዕከላዊ ስፍራውን መያዛቸው ወሳኝ መሆኑን ያምናል።
ያ ማለት ከካሜራ ፊት፣ ከካሜራ ጀርባ፣ በገንዘብ በመደገፍ፣ በማከፋፈል፣ በማርኬቲንግ እና የመጨረሻውን ውጤታ ለዕይታ በማብቃት ውስጥ መሆኑንም ያስረዳል።
ኢድሪስ የፊልም ተመልካቹ ያለምንም ነጋሪ የአሜሪካ ከተሞች የሆኑትን ኒው ዮርክ እና ሎስ አንጀለስ እንደሚያውቀው ሁሉ አህጉሪቱም አንድ ቀን ያን ዓይነት ዕድል ይኖራታል ሲል ይናገራል።
“ይህ እንደቀላል የሚታይ ነገር ግን ከፍተኛ ኃይል (ሶፍት ፓወር) ነው። በአክራ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ” ሲል የሰነቀውን ህልም ይገልጻል።
አክሎም “ማንኛውንም ፊልም ወይንም ስለ አፍሪካ የሚሠራ የትኛውም ነገር ከሆነ የምናየው የሚዘገንን ነው፣ እንዴት ባሪያ እንደ ነበርን፣ እንዴት ቅኝ እንደተገዛን፣ ጦርነት ነው የምናየው።
“ወደ አፍሪካ ስንመጣ ግን ያ እውነት እንዳልሆነ እንረዳለን። ስለዚህ የራሳችንን ልማድ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ አንዱ ቋንቋ ከአንዱ ያለው ልዩነት፣ የራሳችን ታሪክ ራሳችን ባለቤት መሆን አለብን። ዓለም ያንን አያውቅም።”
በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠር ፊልም የሚያመርተው የናይጄሪያው ኖሊዉድ ፊልሞቹ አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ውጤታማ ከሆኑ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው ተብሎ ይገመታል።
ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በሆኑ የአፍሪካ አገራትም እንዲሁ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ፊልሞች የመሥራት ልማድ አለ።
ኤልባ ከዚህ በፊት በአፍሪካ ፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ተሰጥኦው ያላቸው እንዳሉ ተናግሮ ነግር ግን ተቋማት “ያንሳሉ” ብሎ ነበር።
እኤአ በ2022 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተዋናዩን ሀሳብ የሚደግፍ ሪፖርት አውጥቶ ነበር።
የመንግሥታት ድርጅት ተቋም “ከፍተኛ የሆነ የምርት እድገት” መኖሩን ገልጾ፣ ነገር ግን የፊልም ሥራ ዘርፉ ተገቢ ሥልጠና በማጣት፣ የፊልም ተቋማት በበቂ ሁኔታ ባለመኖር እና በፊልም ስርቆት ክፉኛ መጎዳቱን ገልጿል።
ኤልባ የአህጉሪቱ መንግሥታት ተገቢውን ተሳትፎ ካደረጉ እና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ዝግጁ ከሆኑ በጎ ነገር መሥራት እንደሚቻል ያምናል።
“የራሳችን ታሪክ ነገራ ላይ ገንዘብ ማፍሰስ አለብን፤ ምክንያቱም እኔን ስታይኝ በትንሹ ራስህን ታያለህ፤ ያ ደግሞ ያበረታታናል።”












