ለሥራ ፈላጊ ስደተኞች በሯ ክፍት የሆነው የአሜሪካዋ ግዛት

ኤድጋር ቬጋ ጋርሲያ (ግራ) የዓሳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሥራ ላይ ሳለ

የፎቶው ባለመብት, Jorge Luis Pérez Valery

የምስሉ መግለጫ, ኤድጋር ቬጋ ጋርሲያ (ግራ) ከፋብሪካ ሥራው ጠርቀም ያለ ገንዘብ ያገኛል

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እየተቃረበ ነው። ተፎካካሪዎቹ ካማላ ሃሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ ንዑስ ሐሳብ አድርገው ከያዟቸው ጉዳዮች መካከል የስደተኞች ጉዳይ አንዱ ነው።

ሁለቱም ዕጩዎች በሜክሲኮ ድንበር በኩል በሕገ-ወጥ መንገድ አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞችን ለመግታት ቃል ገብተዋል።

አንድ ሪፐብሊካን ግዛት ግን በተቃራኒው ስደተኞችን ለመሳብ ብዙ እየጣረች ትገኛለች።

በአላስካ ባሕረ-ሰላጤ ኮፐር ሪቨር አቅራቢያ በምትገኘው ትንሿ የኮርዶቫ ከተማ የምሳ ሰዓት ደርሷል። ከተማዋ ዓሳ ዓሳ ትሸታለች።

ከአንዱ የዓሳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በርካቶች ምሳ ለመብላት እየወጡ ነው። ነገር ግን የሚቀርብላቸው የአሜሪካ ምግብ አይደለም። ታኮ እና ቶርቲያ የተባሉ የሜክሲኮ ማዕዶች እንጂ።

በርካቶች ብዙ ሺህ ማይሎች አቋርጠው ወደዚህች በዓሳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዋ የምትታወቀው ከተማ ለመሥራት የመጡት ገንዘብ ብለው ነው።

“ባለፈው ዓመት በአራት ወራት ብቻ 27 ሺህ ዶላር ሠርቻለሁ” ይላል ኤድጋር ቬጋ ጋርሺያ። በሜክሲኮ የአንድ ቤተሰብ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 16,269 ዶላር ነው።

የኮርዶቫ ከተማ ዓሳ አስጋሪ

የፎቶው ባለመብት, Jorge Luis Pérez Valery

በኮርዶቫ አብዛኛው ጊዜ ብርድ ነው። የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች ይሆናል። ከባድ ዝናብ እና የበረዶ ብናኝ የተለመደ ነው። ፖላር ናይት በሚባለው ወቅት ደግሞ ለሁለት ወራት ፀሐይ አትወጣም።

ነገር ግን በሞቃታማው ጊዜ ቀኑ ብርሃናማ ይሆናል። የአካባቢው ነዋሪዎች ታዋቂውን የአላስካ ሳልመን (የዓሳ ዓይነት) ለማጥመድ ወደ ወንዝ ይወርዳሉ።

ከከተማዋ ነዋሪዎች ከግማሽ በላዩ በዓሳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሚሠሩ ናቸው። ዓሳ አዘጋጅቶ፣ አሽጎ ለገበያ ማቅረብ ብዙ የሰው ኃይል ይጠይቃል።

የአላስካ ግዛት የሰው ኃይል ክፍል እንደሚለው በግዛቲቱ የባሕር ዓሳ ማምረቻ ፋብሪካዎች ከሚሠሩ ሠራተኞች 80 በመቶ ያህሉ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ናቸው።

ምንም እንኳ ከሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች የመጡ ሠራተኞች ይኑሩ እንጂ አብዛኞቹ ከዩክሬን፣ ከፔሩ፣ ከቱርክ፣ ከፊሊፒንስ ሲሆኑ በርከት ያሉት ደግሞ ከሜክሲኮ ናቸው።

በዓሳ ማምረቻዎቹ የሚከፈላቸው ገንዘብ እና የሥራ ሁኔታ ከእናት አገራቸው የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት ይናገራሉ።

አንድ የዓሳ ማምረቻ ፋብሪካ ሠራተኛ በሰዓት 18.06 ዶላር ያገኛል። ይህም በሰዓት 2100 ብር አካባቢ ማለት ነው። በሰዓት እስከ 27 ዶላር የሚከፈላቸውም አሉ።

ከሥራ ሰዓታቸው ውጪ ቆይተው የሚሠሩ ከሆነ ደግሞ በአላስካ ሕግ መሠረት ተጨማሪ 50 በመቶ ክፍያ ያገኛሉ።

አብዛኛኞቹ ፋብሪካዎች የመኖሪያ ቤት ያዘጋጃሉ። በቀን ሦስት ጊዜ ለሠራተኞቻቸው ምግብ ያቀርባሉ። ይህ ደግሞ ሠራተኞች ገቢያቸውን እንዲቆጥቡ ትልቅ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።

የዓሳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ

የፎቶው ባለመብት, Jorge Luis Pérez Valery

የምስሉ መግለጫ, ሥራ የሚጀምረው ንጋት ሲሆን ለ18 ሰዓታት ይቀጥላል

አልፎም ከተማዋ ትንሽ በመሆኗ ወጪ ለማውጣትም አትጋብዝም። ሲኒማ እና የገበያ ማዕከል የላትም። ከተማዋ አንድ መጠጥ ቤት [ባር] ነው ያላት። ነዋሪዎች በአየር ሁኔታው ምክንያት ዓሳ ማጥመድ ሲሳናቸው እዚህ ተሰባስበው ፑል እየተጨዋቱ ይጎነጫሉ።

ፋብሪካዎች የሠራተኞቻቸውን የጉዞ ወጪም ይሸፍናሉ። ኮርዶቫ እጅግ ራቅ ያለ ሥፍራ ስላለች ወደ ከተማዋ መጓዝ የሚቻለው በአውሮፕላን አሊያም በጀልባ ነው።

የኑሮ ሁኔታው ይህን ያህል የተመቻቸ ነው የሚባል አይደለም። ሠራተኞች ፋብሪካ ውስጥ ካለ ተደራራቢ የተማሪዎች አልጋ ላይ ነው የሚተኙት። በአንድ ክፍል አራት ሰዎች ያድራሉ። የሚፈልጓቸውን ዕቃዎች አጣበው ያስቀምጣሉ።

ሥራውም ቀላል የሚባል አይደለም። ሥራ የሚጀምረው ንጋት ላይ ሲሆን፣ ለ18 ሰዓታት ይቀጥላል። ፋብሪካዎቹ በየቀኑ በርካታ ሺህ ኪሎ ግራም ዓሳ አሽገው ይጭናሉ።

ኮርዶቫ ከተማ በጣም ራቅ ብላ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት

የፎቶው ባለመብት, Jorge Luis Pérez Valery

የምስሉ መግለጫ, ኮርዶቫ ከተማ በጣም ራቅ ብላ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት

ኤድጋር ሥራውን ተክኖበታል። በአንድ እጁ ዓሳውን በሌላ እጁ ስለት ይዞ ሲገፍ ይታያል። ፍጥነቱ የሚያስገርም ነው። የዓሳ ሽታ ልብስ እና ቆዳው ላይ ቢቀርም ሥራውን ይወደዋል።

ከአላስካ በሚያገኘው ገቢ ወደ ሜክሲኮ ተመልሶ የተደላደለ ኑሮ መኖር ይችላል። ቤተሰቦቹ ሜክሲካሊ በተባለቸው የድንበር ከተማ ነው የሚኖሩት። አራት ልጆቹ ሥራውን ጨርሶ እስኪመጣ እየጠበቁት ነው።

ላስካ የገቢ ምንጯ ዓሳ እርባታ እና ምርቱን አቀናብሮ ለገበያ ማቅረብ ነው።

በየዓመቱ 2268 ቶን (2.2 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ገደማ) የዓሳ እና የሌሎች የባሕር እንስሳት ምግቦች ታሽገው ይወጣሉ። ይህ ቁጥር ከጠቅላላው የአሜሪካ ምርት ግማሽ ያክሉን ይሆናል።

እንደ ኦሺን ቢውቲ ትራይደንት ያሉ ግዙፍ የዓሳ ማምረቻ ኩባንያዎች በአላስካ በርካታ ፋብሪካዎች አሏቸው።

ኮርዶቫ የሚገኙ የዓሳ ማጥመጃ ጀልባዎች

የፎቶው ባለመብት, Jorge Luis Pérez Valery

የምስሉ መግለጫ, ኮርዶቫ የሚገኙ የዓሳ ማጥመጃ ጀልባዎች

ለዚህ ነው ኢንዱስትሪው ተጨማሪ የሰው ኃይል የሚፈልገው። የአሜሪካ መንግሥት ወደ አላስካ ሄደው መሥራት ለሚፈልጉ ሰዎች ተጨማሪ ጊዜያዊ የሥራ ፈቃድ ለመስጠት አቅዷል።

ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ሊሰጥ የታቀደው የሥራ ፈቃድ 66 ሺህ ነበር። በያዝነው ዓመት ይህ ቁጥር ወደ 130 ሺህ አድጓል።

በኮርዶቫ ከተማ አነስተኛ የዓሳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ያለው ሪች ዌለር ከአሜሪካውያን ሠራተኞች ጋር ብዙ ችግር ውስጥ ይገባ ነበር። ዕፅ ይጠቀማሉ፣ ሳይስፈቅዱ ይቀራሉ፣ ይጣላሉ ሲል ያማራል።

ነገር ግን ሜክሲኮዎችን ከቀጠረ በኋላ ግን ፋብሪካው የበለጠ ምርታማ እንደሆለት ይመሰክራል።

ቀናት በቀሩት የአሜሪካ ምርጫ እየተፎካከሩ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ የሕገ-ወጥ ስደተኞች “ወረራ” ያሳሰባቸው ይመስላል።

ስደተኞች የአሜሪካውያንን ሥራ እየነጠቁ ነው ሲሉ ያማራሉ። ካማላ ሃሪስ ደግሞ “የተሰበረውን” የስደተኞች ሥርዓት ለመጠገን ቃል ገብተዋል።

በኮርዶቫ በርካታ ሰዎች ሥራ ፍለጋ መምጣታቸው የከተማዋን 3 ሺህ ሕዝብ ሦስት እጥፍ አሳድጎታል። ነገር ግን የከተማዋ ከንቲባ ስደተኞች የኮርዶቫ የጀርባ አጥንት ናቸው ይላሉ።