የአሜሪካ ምርጫ 2024፡ ማን እየመራ ነው? ዶናልድ ትራምፕ ወይስ ካማላ ሀሪስ?

ድምፅ ለመስጠት የተመዘገቡ አሜሪካዊያን ጥቅምት 26/2017 ወደ ምርጫ ጣቢያዎች አምርተው ቀጣይ መሪያቸውን ይመርጣሉ።
የወቅቱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ ወደ ፉክክሩ የመጡት ምክትላቸው ሀሪስ ከቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተፋጠዋል።
አሁኑ ትልቁ ጥያቄ - አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዝደንት ትመርጣለች ወይስ ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ መንበረ-ሥልጣኑን ይቆናጠጣሉ? የሚለው ነው።
የምርጫው ቀን እየቀረበ ነው። ወደ ዋይት ሐውስ ለመግባት የሚደረገውም ፉክክር በዚያው ልክ ተጋግሏል።
ቅድመ ትንበያዎች ከምርጫው በፊት የሚሰበሰቡ ድምፆችን ማዕከል አድርገው ነው የሚሠሩት። በዚህ ሒደት ማን እየመራ ነው?
ማን ይመራል?
ካማላ ሀሪስ በጠቅላላው ድምፅ ከዶናልድ ትራምፕ በጠባብ ነጥብ ከፍ ብለው እየመሩ ይገኛሉ። ካማላ ባለፈው ሐምሌ ዕጩ ሆነው ከመጡ ጀምሮ በጠባብ ድምፅ ተቀናቃኛቸውን በመምራት ላይ ነው የሚገኙት።
ከታች የተመለከተው ሰንጠረዥ እንደሚጠቁመው በቅርቡ የተሰበሰቡ የሕዝብ ድምፆችን ማዕከል በማድረግ ካማላ በመምራት ላይ ይገኛሉ።

ሀሪስ ወደ ምርጫ ፉክክሩ በመጡ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ነው ከትራምፕ ጋር የነበራቸውን ልዩነት ማጥበብ የቻሉት። በተለይ በነሐሤ ወር መጨረሻ አካባቢ ትራምፕን በ4 በመቶ ይመሯቸው ነበር።
ባለፈው መስከረም በነበረው ፕሬዝደንታዊ ክርክር አሊያም ሙግት ምክንያት ሀሪስ በመሪነታቸው ቀጥለውበታል። ምክትል ፕሬዝደንቷ ከትራምፕ ተሽለው ተገኝተውበታል የተባለውን የምርጫ ክርክር 70 ሚሊዮን ገደማ አሜሪካዊያን ተመልክተውታል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት በሁለቱ ዕጩዎች መካከል ያለው ልዩነት የበለጠ እየጠበበ መጥቷል።
ምንም እንኳ እኒህ ከመራጮች የሚሰበሰቡ ድምፆች በአሜሪካዊያን ዘንድ የበለጠ ተቀባይነት ያለው ማነው/ማናት የሚል ፍንጭ ቢሰጡም የምርጫውን ውጤት ለመገመት ያስችላሉ ማለት ከባድ ነው።
አሜሪካ በምትከተለው ኢሌክቶራል ኮሌጅ በተባለ ሥርዓት ምክንያት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ዕጩ ሊረታ ይችላል። በጠቅላላው 538 ኢሌክቶራል ኮሌጆች አሉ። እያንዳንዱ ግዛት እንደ ሕዝብ ብዛቱ ይሰጠዋል። ሀሪስ አሊያም ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ለመግባት ቢያንስ 270 ኢሌክቶራል ኮሌጅ ማግኘት አለባቸው።
በዩናይትድ ስቴትስ 50 ግዛቶች አሉ። አብዛኛዎቹ ግዛቶች ለየትኛው ፓርቲ ዕጩ እንደሚመርጡ ይታወቃል። ነገር ግን የተወሰኑ ወላዋይ የሚባሉ ግዛቶች ለየትኛው ዕጩ ድምፃቸውን እንደሚሰጡ አይታወቅም።
ሁለቱ ዕጩዎች በእነዚህ ግዛት ያሉ መራጮችን ድምፅ ለማግኘት እየተሯሯጡ ይገኛሉ።
በቁልፍ ግዛቶች ማን ይመራል?
ሰባት ግዛቶች ድምፃቸውን ለማን እንደሚሰጡ እስካሁን አልለየም። በእነዚህ ግዛቶች በካማላ እና ትራምፕ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ጠባብ ነው።
በጣም ብዙ ኢሌክቶራል ኮሌጅ ያላት ፔንሲልቬኒያ ግዛት ናት። በዚህችም ግዛት ቢሆን ማን አሸናፊ ይሆናል የሚለውን መለየት አዳጋች ሆኗል።
ሰባቱ ወሳኝ ግዛቶች ፔንሲልቬኒያ፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ ኔቫዳ፣ አሪዞና፣ ጆርጂያ፣ ሚሺጋን እና ዊስኮንሲን ናቸው።
ካማላ ሀሪስ የምርጫ ዘመቻውን ከተቀላቀሉ በኋላ በበርካታ ግዛቶች ጠንከር ብለው መገኘታቸው እየታየ ነው። በለተይ በሚሺጋን፣ ኔቫዳ እና ዊስኮንሲን ሀሪስ እየመሩ መሆኑን የቁጥር መለኪያዎች ያሳያሉ። ቢሆንም ልዩነቱ አሁንም ጠባብ ነው።
ነገር ግን በተለያዩ ወሳኝ በሚባሉ ግዛቶች የመሪዎች መለዋወጥ ይታያል። ማለትም አንድ ሰሞን ሀሪስ ይመራሉ፤ በሌላኛው ደግሞ ትራምፕ።
እኒህ ግዛቶች ለወትሮው ለዲሞክራቲክ ፓርቲው ነበር ድምፃቸውን የሚሰጡት። ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2016 ዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ሲያሸንፉ ሁኔታዎች ተቀየሩ።
ባይደን ደግሞ በ2020 ዶናልድ ትራምፕን ሲረቱ እኒህ ግዛቶች መልሰው ሰማያዊ [የዲሞክራቶች መለያ ቀለም] ሆኑ። ሀሪስ እኒህን ግዛቶች የሚያሸንፉ ከሆነ ቀጣይዋ ፕሬዝደንት የመሆን ዕድላቸው ይሰፋል።
ኤቢሲ የተሰኘው የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ድምፅ መሰብሰቢያ የሆነው 538 የተባለው ድረ-ገፅ ነው ድምፅ የሚሰበስበው።
አሁን በካማላ ሀሪስ እና በዶናልድ ትራምፕ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ጠባብ ስለሆነ አሸናፊውን መገመት ያዳግታል።
በ2016 ምርጫ ከምርጫው በፊት የተሰበሰቡ ድምፆች ዶናልድ ትራምፕ ይሸነፋሉ የሚሉ ነበሩ። በ2020 ምርጫም እንዲሁ በተመሳሳይ ዶናልድ በተቀናቃኛቸው ተቀድመው ነበር።















