ኩዌት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ምናባዊ ዜና አንባቢ ይፋ አደረገች

በኩዌት ይፋ የተደረገችው ምናባዊ ዜና አንባቢ

የፎቶው ባለመብት, KUWAITNEWS

የምስሉ መግለጫ, በኩዌት ይፋ የተደረገችው ምናባዊ ዜና አንባቢ

የኩዌት መገናኛ ብዙኃን ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) በመጠቀም ምናባዊ ዜና አንባቢን አስተዋወቀ።

“ፊዳ” የተባለችው ዜና አንባቢ በኩዌት ኒውስ የትዊተር ገጽ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርባለች።

ነጭ ሴት ተደርጋ የተስላችው ይህች ምናባዊ ዜና አንባቢ፣ ጥቁር ኮት እና ነጭ ካናቴራ ለብሳ ለመገናኛ ብዙኃኑ ተከታታዮች እራሷን አስተዋውቃለች።

“ፊዳ እባላለሁ። በኩዌት በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካይነት የኩዌት ኒውስ የመጀመሪያዋ ዜና አንባቢ ነኝ። ምን አይነት ዜና ይፈልጋሉ? አስታየትዎን ይንገሩን” በማለት ምናባዊ ዜና አንባቢዋ በአረብኛ ቋንቋ ስትናገር ትታያለች።

የኩዌት ኒውስ ምክትል አርታዒ የሆኑት አብዱላ ቦፍታኢን የጣቢያው ውሳኔ የሰው ሰራሸ አስተውሎት “አዲስ እና ፈጠራ የታከለበት ይዘት” ማቅረብ እንደሚያስችል የመረመረ ነው ሲሉ ለፈረንሳዩ ዜና ወኪል፣ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

አብዱላ ቦፍታኢን ምናባዊ ዜና አንባቢዋ የምትናገረው የአረብኛ ቋንቋ በኩዌት ዘዬ የተገራ መሆኑን እና ለታዳሚዎቻቸው ዜና እንደምታነብ ገልጸዋል።

“ፊዳ ዝነኛ ስም ነው። የጥንት የኩዌት ስም ሲሆን፣ የከበረው ብረት፤ ብር ማለት ነው። ሮቦቶች ቀለማቸው የብር እና ብረት እንደሆነ እናልማለም፤ ስለዚህ ሁለቱን በአንድ ላይ በማድረግ ስያሜዋን ሰጥተናታል” ሲሉ ተናግረዋል።

የዜና አንባቢዋ የፀጉር እና የዓይን ቀለም በኩዌት የሚኖሩ የአገሬው ሕዝብን እና የውጭ አገር ዜጎችን እንደሚወክል ጨምረው ቦፍታኢን ተናግረዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ምናባዊ ዜና አንባቢ በማስተዋወቅ ኩዌት የመጀመሪያዋ አገር አይደለችም። እአአ 2018 ላይ የቻይና መንግሥት ዜና አገልግሎት የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነ ዜና አንባቢ አስተዋውቆ ነበር።

ዢኑዋ በወቅቱ ይፋ ያደረገው በሰው ሰራሽ አስተውሎት የበለጸገው ምናባዊ ዜና አንባቢ፣ የጽሑፍ ዜናዎችን እንደማንኛውም ባለሙያ ጋዜጠኛ በአግባቡ ማቅረብ ይችላል ብሎ ነበር።

ከአንድ ወር በፊት ጎልድማን ሳክስ የተሰኘ ባንክ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ በዓለም ዙሪያ በሰዎች የሚሰሩ 300 ሚሊዮን የሚደርሱ ሥራዎችን ሊተካ ይችላል ሲል አንድ ሪፖርት ይፋ አድርጎ ነበር።

የኢንቨስትመንት ባንኩ ጎልድማን ሳክስ እንደሚለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአሜሪካ እና በአውሮፓ በሰው ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል ሩቡን ሊተኩ ይችላሉ ያለ ሲሆን፤ ከሰው ልጅ በላይ ውጤታማ ስለሚሆኑ ምርታማነት እና እድገትንም ይጨምራሉ ብሏል።