ጥቁር ወንዶችን ለይቶ ከአውሮፕላን አስወርዷል የተባለው የአሜሪካው አየር መንገድ በዘረኝነት ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, CBS
ከወራት በፊት ከአሪዞና ወደ ኒውዮርክ በነበረ በረራ ጥቁር ወንዶችን ለይቶ ከአውሮፕላን አስወርዷል የተባለው የአሜሪካው አየር መንገድ በዘረኝነት ተከሰሰ።
በአውሮፕላን ውስጥ መጥፎ የአካል ጠረን ቅሬታ መቅረቡን ተከትሎ ጥቁር ወንዶችን ለይቶ አጠር ላለ ጊዜ እንዳስወረዳቸው የቀረበው ክስ ያስረዳል።
ክሱን የመሰረቱት የማይተዋወቁ እና በአውሮፕላኑም ውስጥ አብረው ተቀምጠው ያልነበሩ ሶስት ጥቁር ወንዶች ናቸው።
“የአሜሪካው አየር መንገድ ጥቁር በመሆናችን ለይቶ አውጥቶናል፤ አሳፍሮናል እንዲሁም አዋርዶናል” ሲሉ ግለሰቦቹ ረቡዕ ግንቦት 22/ 2016 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
መቀመጫውን ቴክሳስ ያደረገው አየር መንገድ ክሱ ከእሴቱ ጋር የማይጣጣም መሆኑን በመግለጽ ጉዳዪን እያጣራሁ ነው ብሏል።
ግለሰቦቹን ወክሎ ክሱን ለፌደራሉ ፍርድ ቤት ያቀረበው ‘ኮንሱመር አድቮኬሲ ግሩፕ ፐብሊክ ሲትዝን’ የተሰኘው የሸማቾች ተሟጋች ቡድን በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፋሪ የነበሩት ግለሰቦች ወንበራቸው ላይ ተቀምጠው ለመብረር በተዘጋጁበት ወቅት በበረራ አስተናጋጅ ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ መጠየቃቸውን ገልጿል።
ክሱን የመሰረቱት አልቪን ጃክሰን፣ ኢማኑዌል ዣን ጆሴፍ እና ዛቪየር ቪል ከአውሮፕላኑ እየወጡ በነበረበት ወቅት “በበረራው ላይ የነበሩ ሁሉም ጥቁር ወንዶች እየወረዱ” መሆኑን ተረዱ።
ግለሰቦቹ በዚህ አውሮፕላን ከመሳፈራቸው በፊት ምንም ችግር ሳይገጥማቸው ከሎስ አንጀለስ በረው ነበር የደረሱት።
ክሱን የመሰረቱት ሶስቱ ግለሰቦች እና ተጨማሪ ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ የተደረጉ አምስት ጥቁር ወንዶች “አንድ ነጭ ወንድ የበረራ አስተናጋጅ ከየት እንደመጣ ያላወቀው የተሳፋሪ መጥፎ ጠረን ሸቶኛል በሚል ቅሬታ በማሰማቱ ነው” በሚል በአየር መንገድ ወኪሉ ተነግሯቸዋል።
“ከቆዳችን ቀለም ውጭ ሌላ ምንም አይነት ማብራሪያ የለም” ሲሉ ግለሰቦቹ ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ጠቅሰው “በግልጽ ይህ የዘር መድልዎ ነው” ንለዋል።
የአሜሪካ አየር መንገድ ሰራተኞች ግለሰቦቹን በሌሎች በረራዎች ለመላክ ቢሞክሩም በዚያች ምሽት ወደ ኒውዮርክ የሚደረግ በረራ እንዳልነበር ተገልጿል። በዚህም ምክንያት እንደገና እንዲሳፈሩ ተደርገው በቀደመ ወንበሮቻቸው ላይ ተቀምጠው በረራው መቀጠሉም ተነግሯል።
ክሱ በተጨማሪም ግለሰቦቹ ከአውሮፕላን ከወረዱ በኋላ አብራሪው በሰውነት መጥፎ ጠረን ምክንያት የመዘግየት ችግር ማጋጠሙን ማስታወቁ ተገልጿል። ከሳሾቹ እንደሚሉት ሽታ በሚል የቀረበው ቅሬታ ሃሰት ነው ብለዋል። “
ዳግም ከተሳፈርን እስከ ወረድንበት ድረስ ከነጭ ወንድ የበራረ አስተናጋጅ የነበረን ንግግርም ሆነ ግንኙነት በውርደት፣ በጭንቀት እና በጭንቀት የተሞላ ነበር” ማለታቸውን ክሱ ይዟል።












