የዝውውር ጭምጭምታ፡ ማንቸስተር እና ባየር ሙኒክ የሚሻሙበት አጥቂ እና የሊቨርፑል ጉዳይ

ቪክተር ዮኬሬስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሳምንት በፊት በተከፈተው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በርካታ ክለቦች ተጫዋቾችን ለማዘዋወር እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ለቀጣይ አንድ ወር ገደማ በሚቆየው የዝውውር መስኮት ሊኖሩ የሚችሉ የተጫዋቾችን ዝውውር በተመለከተ እየወጡ ያሉ መረጃዎን እንደሚከተለው አቅርበናል።

ጆን ዱራንን ለማስፈረም ፒኤስጂ ፍላጎት እንዳለው ታውቋል። አስቶን ቪላም አጥቂውን በ60 ሚሊዮን ፓውንድ ሊሸጥ ይችላል ተብሏል።

የባርሴሎናው የስፖርት ዳይሬከተር ዴኮ አጥቂውን ለማስፈረም ፍላጎት እንዳለው ለዱራን ተወካዮች ማስታወቁ ተዘግቧል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ሊያስፈርመው የሚፈልገውን ቪክተር ዮኬሬስ ዝውውር አጨናግፎ ለመውሰድ ባየር ሙኒክ መዘጋጀቱ ታውቋል።

ሪያል ማድሪድ በበኩሉ ሆላንዳዊውን ተከላካይ ቨርጂል ቫን ዳይክን ለማስፈርም የነበረውን ዕቅድ ውድቅ እድርጓል። ተጫዋቹ ከሊቨርፑል ጋር ያለው ስምምነት በመጪው ሰኔ የሚጠናቀቅ በመሆኑ የተከላካዩ ተወካዮች ማድሪድን አነጋግረው እንደነበር 'ሬሌቮ' ዘግቧል።

የሳዑዲ አረቢያ ክለቦች በዝውውር መስኮቱ ብራዚላዊውን የማንቸስተር ዩናይትድ አማካይ ካዜሚሮን ለማስፈረም ይፈልጋሉ።

ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶተንሃም በዝውውር መስኮቱ የፒኤስጂውን አጥቂ ራንዳል ኮሎ ሙዋኒን በውሰት ለማስፈረም ፍላጎት አላቸው ተብሏል። ጁቬንቱስም ፍላጎት አለው ሲል 'አትሌቲክ' ዘግቧል።

የማንቸስተር ዩናይትዱን አጥቂ ማርከስ ራሽፈርድን በውሰት ለማስፈረም ኤሲሚላን ፍላጎት አሳይቷል። በዚህም የተጫዋቹን የተወሰነ ደሞዝ ለመሸፈን ዝግጁ ነው ተብሏል።

ጁቬንቱስ ደግሞ የማንቸስተር ዩናይትዱን ጆሹዋ ዘርክዚን በውሰት ለማስፈረም ቢፈልግም ሆላንዳዊው ግን በኦልድትራፎርድ መቆየት እንደሚመርጥ ታውቋል።

በዘርክዚ ምትክ ጁቬንቱስ ሰርቢያዊውን ዱሳን ቭላሆቪችን አሳልፎ ለመስጠት ተዘጋጅቷል ተብሏል።

ብራዚላዊው አማካይ ዳግላስ ሉዊዝ በሁለት የፕሪሚር ሊግ ክለቦች ይፈለጋል ሲል 'ስካይ ስፖርት ኒውስ' ዘግቧል።

ብራዚላዊውን አንቶኒን ከማንቸስተር ዩናይትድ በውሰት ለማስፈረም ከሚፈልጉ ክለቦች መካከል አንዱ ሪያል ቤቲስ መሆኑ ተዘግቧል።

የግሪኩ ኦሊምፒያኮስም የክንፍ ተጫዋቹን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል።

ክሪስታል ፓላስ ደግሞ 20 ሚሊዮን ፓውንድ የተገመተውን የሰንደርላንዱን ጆብ ቤሊንግሃምን ለማስፈረም ፍላጎት አለው ተብሏል።

የዌስት ሃሙን አጥቂ ኒክላስ ፉልክሩግን በውሰት ለማስፈረም ጁቬንቱስ ፍላጎት እንዳለው ታውቋል።

ብራዚላዊው የዎልቭስ አጥቂ ማቲያስ ኩኛ በክለቡ የሚያቆውን ውል ከመፈረሙ በፊት ያሉትን አማራጮች ለመመልከት ይፈልጋል ሲል 'ስካይ ስፖርትስ' ዘግቧል።

ቼልሲ በውሰት የሰጠውን ተከላካይ ትሬቮህ ቻሎባን ከክሪስታል ፓላስ መመለስ ይሻላል ወይስ አዲስ ተከላካይ እናስፈርም በሚለው ጉዳይ ላይ እየመከረ ይገኛል።

የፌይኖርዱን አኒስ ሃጂ ሙሳን ለማስፈረም ሊቨርፑል ፍልጎት እንዳለው የዘገበው 'ፉትቦል ኢንሳይደር' ነው።

ከናፖሊ ጋር ስሙ የተያያዘውን ፌደሪኮ ኪዬዛን በውሰት ለመስጠት ሊቨርፑል ፍላጎት የለውም ተብሏል።