ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ የወደቀችው የ19 ወር ህጻን ከሰዓታት ጥረት በኋላ በሕይወት ተረፈች

በደቡባዊ ታይላንድ አንዲት ጨቅላ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ከወደቀች በኋላ በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አስደናቂ ጥረት በሕይወት መውጣት ቻለች።
የ19 ወራት ዕድሜ ያላት ጨቅላ ታካ በተሰኘ የታይላንድ ግዛት በሚገኝ 13 ሜትር የሚሆን ጥልቀት ባለው የውሃ ጉድጓድ ውስጥ የገባችው ትናንት ሰኞ እየተጫወተች ሳለች ነበር።
ሕጻኗ ከገባችበት የውሃ ጉድጓድ አቅራቢያ በመስክ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ወላጆቿ የድረሱን ጥሪ ማስተጋባታቸውን ተከትሎ፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ምሽቱን በሙሉ በነብስ አድን ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር።
የሚያንማር ዜግነት ያላቸው የስደተኛ ወላጆች ልጅ የሆነችው ሕጻን 30 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ መግባቷ ሲሰማ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር።
የሕጻኗ ወላጆች ሥራ ቦታቸው ወደሆነው የእርሻ ቦታ ልጃቸውን ይዘው ከሄዱ በኋላ ልጃቸውን ከዛፍ ጥላ ስር አስቀምጠው የዕለት ሥራቸው ሲያከናውኑ እንደነበር ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በዕረፍት ጊዜያቸው ልጃቸውን ካስቀመጡበት ሲያጡ ድንጋጤ ውስጥ የገቡት ወላጆች፣ ከውሃ ጉድጓዱ የልጃቸውን ለቅሶ መስማታቸውን ይናገራሉ።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ጊዜ ሳያባክኑ በከባድ ማሽኖችን በመታገዝ ሌሊቱን ሙሉ ሲቆፍሩ መቆየታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ጨቅላዋ መተንፈስ እንድትችል በማሽን በመታገዝ ኦክስጅን ወደ ጉድጓዱ እንዲገባ ሲደረግም ነበር።
ባለሥልጣናት ለአካካባቢ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ፣ በማሽን የታገዘ ቁፋሮ በሚደረግበት ጊዜ ጉድጓዱ ተደርምሶ ህጻኗ ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት በማደሩ የመጨረሻ ደረጃ ቁፋሮ በእጅ መከናወኑን አስረድተዋል።
ህጻኗን ከጉድጓዱ ስትወጣ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ደስታቸውን በጩኸት ገልጸዋል።
“ታዳጊዋን መታደግ በመቻላችን በጣም ደስተኛ ነን” ሲሉ ከአደጋ ጊዜ ሠራተኞቹ መካከል አንዱ የሆኑት ቻናቻርት ዋንቻሬረንሩግ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የህጻኗን ሕይወት ለማዳን “ከሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ስንሰራ ነበር። ያለ እንቅልፍ ቆፍረናል። ሁሉም የተቻለውን ሲያደርግ ነበር” ብለዋል ሠራተኛው።
ባለሥልጣናት ከጉድጓድ የወጣችው ህጻን አነስተኛ ጉዳት ደርሶባት ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዷን ተናግረዋል።
“የድካም ምልክት ይታይባታል ከዚያ ውጪ በመልካም ጤንነት ላይ ትገኛለች” ሲሉ የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ራታሳራን ኬትሶሲንግ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።












