በሚቀጥለው ሳምንት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የመደረስ ተስፋ እንዳለ ፕሬዚዳንት ባይደን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጋዛ እስከ ሰኞ ድረስ የተኩስ አቁም እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ገለጹ።
አስተያየቱን የሰጡት የእስራኤል እና የሐማስ ባለስልጣናትን አሳትፏል የተባባለ ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ላይ መጠነኛ መሻሻል እንዳለ በተዘገበበት ወቅት ነው።
ይህም እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ እርዳታ እንዲገባ እና መስከረም 26 የተፈጸመውን የሐማስ ጥቃት ተከትሎ የተወሰዱ ታጋቾችን መልቀቅን ያካትታል።
እስራኤል በጉዳዩ ላይ አስተያየት ባትሰጥም የሐማስ ባለስልጣናት ግን ባይደን እንደጠቆሙት ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ጫፍ ላይ እንዳልደረሱ ጠቁመዋል።
ከግብጽ ጋር ድርድሩን በማካሄድ ላይ የምትገኘው ኳታር ይፋ ሊደረግ የሚችል ምንም አይነት ስምምነት እንደሌለ ተናግራለች።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጅድ አል-አንሷሪ እንዳሉት ዶሃ "የረመዳን ጾም ከመጀመሩ በፊት ጦርነቱ እንዲቆም ታበረታታለች። ሂደቱ ተስፋ ቢኖረውም ብሩህ አይደለም" ብለዋል።
በደቡብ እስራኤል የሐማስ ታጣቂዎች ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደሉ በኋላ እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ እና የማያባራ ጥቃት መጀመሯ ይታወሳል።
ጥቃት አድራሾቹ 253 ሰዎችን አግተው የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑት ተለቀዋል።
በጋዛ እስራኤል እያደረገችው ባለው የተቀናጀ የአየር፣ የምድር እና የውሃ ላይ ጥቃት ቢያንስ 97 ሺህ 878 ሰዎች ሲገደሉ፤ 70 ሺህ 215 መቁሰላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። በሐማስ አስተዳደር ስር ባለው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መሰረት ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 96 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ለድርድሩ ቅርብ የሆኑ ስማቸውን ያልገለጸው ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው ሐማስ በፈረንሣይ የተቀረፀውን ረቂቅ የድርድር ማዕቀፍ በማጥናት ላይ ይገኛል።
ማዕቀፉ ሁሉም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለ40 ቀናት እንዲቋረጡ እና በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን 1 ለ 10 ስምምነት ከእስራኤላውያን ታጋቾች መለዋወጥን ያካትታል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ሰኞ ዕለት በኒውዮርክ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ከጫፍ ደርሰናል። እስካሁን ግን አልተጠናቀቀም። ተስፋዬ እስከሚቀጥለው ሰኞ ድረስ የተኩስ አቁም እናደርጋለን የሚል ነው" ብለዋል።
በኋላም በኤንቢሲ ላይ የቀረቡት ፕሬዚዳንቱ ስምምነቱ ከተደረሰ እስራኤል በረመዳን ጥቃቷን ለማቆም ፈቃደኛ ትሆናለች ብለዋል።
የረመዳን ጾም ከአስር ቀን በኋላ ይጀመራል።
“ረመዳን እየደረሰ ነው። ታጋቾቹን በሙሉ ለማውጣት እስራኤል ጊዜ ለመስጠት በረመዳንም እንቅስቃሴ እንደማይያደርጉ ስምምነት ተደርሷል" ብለዋል ባይደን።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር በበኩላቸው “ንግግሮች ይቀጥላሉ። ከእነዚህ መካከል የአንዳንዶቹ የመጨረሻው ለሐማስ የሚተዉ ይሆናል” ብለዋል ።
ሚለር አክለውም ስለ ድርድሩ ወይም ስለሚሳካበት ጊዜ ተጨማሪ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆኑም “በዚህ ሳምንት መጨረሻ ከሆነ እሰየው… ይህንን ስምምነት እንዲደረስ እየሞከርን ነው። የሚሳካም ይመስለናል” ብለዋል።
አንድ የሐማስ ባለስልጣን ቀደም ሲል ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ሐማስ ቅድሚያ የሚሰጠው እስረኞችን መለዋወጥ ሳይሆን ጦርነቱን ማቆም ነው።”
"ከዚህ ሁሉ የህይወት እና የንብረት ውድመት በኋላ ወደ ሙሉ የተኩስ ማቆም፤ የተፈናቀሉትን መመለስ እና የጋዛን መልሶ ግንባታ የማያመጣ ማንኛውንም ሐሳብ መቀበል ምክንያታዊ አይደለም።"
የእስራኤል ዋና አጋር የሆነችው አሜሪካ ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲቆም የሚጠይቀውን ውሳኔ በመቃወሟ ከፍተኛ ትችት አስተናግዳለች።
"በተቻለ ፍጥነት" ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረስም የራሷን የውሳኔ ሃሳብ አቅርባለች። እስራኤል የደቡብ ጋዛዋ ራፋህ ከተማን "አሁን ባለው ሁኔታ" እንዳትወር አስጠንቅቃለች።
እስራኤል 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በተጠለሉባት ራፋህ ላይ ጥቃት እንዳትሰነዝር ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ጫና ገጥሟታል። አብዛኞቹ በግዛቱ ያሉ ሰዎች በስተሰሜን ያለውን ጦርነት ሸሽተው የተጠለሉ ናቸው።
ባይደን በቃለ ምልልሱ ወቅት “በጣም ብዙ ንፁሀን ሰዎች እየተገደሉ ነው። እስራኤል በራፋህ የምታደርሰው ጥቃት ቀንሷል። ራፋህን ከሐማስ ነጻ ከማድረጋቸው በፊት አብዛኛውን ነዋሪ ለማውጣት ለእኔ ቃል ገብተውልኛል” ብለዋል።
እሑድ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ራፋህን ጨምሮ ከሌሎች አካባቢዎች ንፁሀን ዜጎችን ለማስወጣት ያለመውን የአገሪቱን ጦር ዕቅዶች ተቀብያለሁ ብሏል።
ኔታንያሁ እሑድ ዕለት ከሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የእስራኤል ኃይሎች ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም በራፋህ ላይ ወረራ እንደሚጀምሩ በመግለጽ “የመጨረሻውን የሐማስ ምሽግ ሳንሰባብር መልቀቅ አንችልም” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።
"ስምምነት ከደረሰን በተወሰነ መልኩ ይዘገያል እንጂ ይከናወናል። ስምምነት ካልተደረሰ ግን እናደርገዋለን” ሲሉም አክለዋል።
ሰኞ ዕለት ደግሞ የፍልስጤም አስተዳደር ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሽታይህ ዌስት ባንክን በከፊል ከሚመራው መንግሥታቸው ጋር ስልጣናቸውን ለቀዋል።
ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ለአዲስ መንግስት መንገድ ይከፍታል የተባለውን የጠቅላይ ሚንስትሩን ውሳኔ ተቀብለዋል።
የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ካበቃ በኋላ ጋዛን ለማስተዳደር የፍልስጤም አስተዳደር ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ አሜሪካ አባስ ላይ ግፊት እያደረገች ነው።
ኔታንያሁ ባለፈው ሳምንት ለለግዛቲቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሲገልጹ ስለ አስተዳደሩ ሚና ምንም አልጠቀሱም።












