የሶማሌ ክልል ፈቃዳቸው አልታደሰም የተባሉ 15 የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞችን አገደ

ማይክሮፎን

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ ባለሥልጣናት ለውጭ የመገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ አስራ አምስት ጋዜጠኞች አስፈላጊው የሥራ ፈቃድ የላቸውም በማለት ዕገዳ እንደተጣሉባቸው ተነገረ።

በሶማሌ ክልል ውስጥ ሲሰሩ ከነበሩት የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች መካከል ቢቢሲ እና የአሜሪካ ድምጽ የሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎቶች ይገኙባቸዋል።

የሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት እርምጃውን የወሰዱት የፌደራል መንግሥቱ የመገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣጣሪ አካል የሆነው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ደብዳቤ መጻፉን ተከትሎ ነው።

ባለሥልጣኑ በደብዳቤ አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ወኪሎች አስፈላጊውን ፈቃድ ሳያገኙ በክልሉ ውስጥ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሷል።

ነገር ግን የክልሉ የጋዜጠኞች ማኅበር ባለሥልጣናቱ ጋዜጠኞችን በክልሉ እንዳይሰሩ ለማገድ ያቀረበውን ምክንያት ውድቅ አድርጎታል።

ለዕገዳው ዋነኛ ምክንያት የመገናኛ ብዙኃኑ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሚገኘው ክልል ውስጥ ስላለው ሙስና እና ከባድ ድርቅ ያስከተለውን ተጽእኖ በማጋለጣቸው ነው ሲል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

የጋዜጠኞቹ ማኅበር ሊቀመንበር አብዱልራዛክ ሐሰን ጨምሮም በየስድስት ወሩ የሚታደሰው የጋዜጠኞቹ ፈቃድ እንዲታደስ ሲጠየቅ ቆይቷል ብሏል።

ቢቢሲ ከሶማሊ ክልል የኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በተደረሰው የሰላም ስምምነት የቆመው የእርስ በርስ ጦርነት በተካሄደባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ያለው የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ በፍጥነት ሲያሽቆለቁል ቆይቷል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥቂት የማይባሉ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን መድረኮች፣ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ለእስር መዳረጋቸው ይታወቃል።

መቀመጫውን አሜሪካ ኒው ዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች የሆነው ሲፒጄ፣በሁለት ዓመት ውስጥ ቢያንስ 63 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች መታሰራቸውን ሪፖርት አድርጓል።