ከተገደለ ከአስርታት በኋላ መነጋጋሪያ ሆኖ የቀጠለው ቶማስ ሳንካራ ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, William Campbell
ቶማስ ሳንካራን ምን ገደለው? ይህ ጥያቄ ከ34 ዓመታት በኋላም ትክክለኛ ፍርድ አግኝቶ ምላሽ አልተሰጠበትም።
ደጋፊዎቹ ሕዝቡን ይወዳል፤ አገሩን ይወዳል፤ አፍሪካን ይወዳል፤ ሲሉ ስሙን እያነሱ ያዜሙለታል።
ይህ የእሱ ትክክለኛው መገለጫው አይደለም የሚሉ ተቺዎች ደግሞ ለተቃዋሚዎቹ ዕድል የማይሰጥ ሲሉ ይወቅሱታል።
ሳንካራ ከተገደለ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ቢሆንም በቡርኪናፋሶ ዜጎች ዘንድ አልተዘነጋም። በተለይ ወታደሮች በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ስሙ በስፋት እየተነሳ እና እየታወሰ ነው።
ቼ ጉቬራን ከልቡ እንደሚያደንቅ የሚነግረለት ቶማስ ሳንካራ ለምን አሁንም ስሙ ይነሳል?
ታኅሣሥ 21 ቀን 1949 ለምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቡርኪናፋሶ ታሪካዊ ዕለት ነበረች። ዝነኛውን ቶማስ ኢሲዶር ኖኤል ሳንካራን አስገኝታለችና።
ከነፃነት በኋላ ከልጅነት እስከ ወጣትነት ዘመኑ አራት መፈንቅለ መንግሥቶች የተፈራረቁባት፣ መረጋጋት የራቃት፣ ድህነቷ የቀጠለ፣ ከድጡ ወደ ማጡ የምታዘግም አሳዛኝ አገሩን ሁኔታ እያየ ነበር ያደገው።
የቡርኪና ፋሶ የቀድሞ ስም ኧፐር ቮልታ ነበር። በአውሮፓውያኑ በ1960 ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ተላቅቃ ነፃነቷን ስትቀዳጅ ሳንካራ ገና የአስራ ሁለት ዓመት ብላቴና ነበር።
ይህን ታሪካዊ ሀቅ በዓይኑ አይቷል። አይቶም በደስታ አብሮ ከታላላቆቹ ጋር ጨፍሯል። ደግሞም በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ በተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥቶች ተፈራርቀው አምባገነን መሪዎች አገሩን እንደ ግል ርስታቸው ሲመዘብሩ እና በሕዝቧ ላይ ግፍ ሲፈጽሙ ተመልክቶ አዝኗል።
በ1972 አገሩ ኧፐር ቮልታ ከማሊ ጋር በገጠመችው ጦርነት ቆራጥ ወታደር፤ ጀግና የጦር መሪ መሆኑን አስመስክሯል።
ከሁሉም በላይ የለየለት አብዮተኛ ነበር። በጀግንነት የተዋጋበትን ጦርነት ኋላ ላይ እያስታወሰ ጭቁኖችን ያጋደለ "ትርጉም የለሽ" ግጭት በማለት አውግዞታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነሐሴ 1983 ሳንካራ የቅርብ ጓደኛዬ በሚለው ብሌስ ካምፓዎሬ የተመራው መፈንቅለ መንግሥት ቡድን የኧፐር ቮልታን የመሪነት ሥልጣን ተቆጣጠረ። ሥልጣኑንም ያኔ ገና የሰላሳ ዓመት ወጣት ለነበረው ሳናካራ አስረከበ።
አገሪቱ በእሱ የሥልጣን ዘመን ነበር ከኧፐር ቮልታ ወደ ቡርኪና ፋሶ ስያሜዋን የቀየረችው። ትርጉሙ "የቅን ሰዎች ምድር" እንደማለት ነው።
"ለመብቱ የማይታገል ሰው ሊታዘንለት አይገባም" ዓይነት ብሒል ነበረው ቶማስ ሳንካራ።
የቶማስ ሳንካራ የመታሰቢያ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ ሉክ ዳሚባ "ለእኛ ሳንካራ ጀግናችን ነበር። ሕዝቡን ይወዳል። አገሩን ይወዳል። አፍሪካን ይወዳል። ሕይወቱን ለእኛ ሰጥቷል" ሲሉ ይገልጹታል።
ሳንካራ ቅንጡ የሚባል የአኗኗር ዘይቤ አልነበረውም። የራሱን እና የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ ቀንሷል። የመንግሥት ባለሥልጣናት በአውሮፕላን ሲጓዙ የቢዝነስ ክፍል እንዳይጠቀሙም አግዷል።
ለትምህርት ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በአገሪቱ ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉ ሰዎች በ1983 ከነበረበት 13 በመቶ በ1987 ወደ 73 በመቶ አድጓል። እንዲሁም ግዙፍ ብሔራዊ የክትባት ዘመቻን በበላይነት መርቷል።
ከፊውዳል ባለንብረቶች መሬት ነጥቆ በቀጥታ ለድሃ ገበሬዎች አከፋፍሏል። ይህም የስንዴ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።
የተባበረችው አፍሪካ "የአዲስ ቅኝ አገዛዝ" ተቋማት ብሎ ከሚጠራቸው ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና ከዓለም ባንክ ተቃራኒ እንድትቆም ጥሪ አቅርቧል።
አንድ ጊዜ "የሚያበላህ ይቆጣጠርሃል" ሲል መናገሩ ይጠቀሳል።
አፍሪካ ውስጥ እንደ ቡርኪና ፋሶ ባሉ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበራትን የፈረንሳይን የበላይነት የሚገዳደር የፀረ-ኢምፔሪያሊስት የውጭ ፖሊሲን ይፋ አደረገ። ፈረንሳይ ሳንካራን ለመግደል ፊታውራሪ ነበረች ስትል ባለቤቱ ማሪያም ትከሳለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሁንም ድረስ የአገሪቱ ወጣቶች "እሱ ፕሬዝዳንታችን ሆኖ በልባችን ይኖራል። ለሕዝቡ ያደረገው ነገር እኛ ወጣቶችም እሱ ያደረገውን እንድናደርግ ያበረታታናል" ይላሉ።
በዋና ከተማዋ ዋጋዱጉ በሚገኘው የቶማስ ሳንካራ የመታሰቢያ ፓርክ ውስጥ ስድስት ሜትር ርዝማኔ ያለው የነሐስ ሐውልት በ2019 ቆሞሎታል። የመጀመሪያው ሐውልት ላይ ቅሬታዎች በመነሳታቸው ባለፈው ዓመት በድጋሚ ተሠርቷል።
ሳንካራ የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር እንደ አዲስ ጽፏል። ከ10 ሚሊዮን በላይ ዛፎችን በመትከል የሳህልን በረሃማነት ለመከላከል ሠርቷል። የአገሪቱ ዜጎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በመደገፍም ይታወቃል።
ሴቶችን ለከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ከመሾም ባለፈ ሴቶች እንዲሠሩ ያበረታታ ነበር።
ሳንካራ የሴት ልጅ ግርዛትን ይቃወማል። የእርግዝና መከላከያን ያበረታታል። የአገሪቱን ጦር እንዲቀላቀሉ በመመልመል እና በትምህርት ጊዜ የእርግዝና ፈቃድ በመስጠትም ይታወቃል።
ቶማስ ሳንካራ ተቺዎችም አላጣም።
የሳንካራ አክራሪ የግራ ክንፍ ፖሊሲ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ክፉኛ ይተቻል።
በአውሮፓውያኑ 1986 አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ዘገባ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ናቸው የተባሉ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታስረው ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸዋል ብሏል።
በሳንካራ መንግሥት ውስጥ የመረጃ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ሰርጌ ቴኦፊል ባሊማ "የብዝሃነት ዴሞክራሲ ሃሳብን ለመቀበል በጣም የዘገየ ይመስለኛል። ተቃዋሚዎቹን ለማናገር እና ሊያዳምጣቸው አልቻለም" ሲሉ ሳናካራን ተችተዋል።
ፕሮፌሰር ባሊማ አክለውም "ለሕዝብ ሥልጣን መስጠት ስለፈለገ የሕዝቡን ግላዊ እና ሕዝባዊ የሕይወት ዘይቤ በተገቢው መንገድ ለመምራት ለተመለመሉት የአብዮቱ መከላከያ ኮሚቴዎችን (ሲዲአር) ለሚመሩት ሠርቶ አደሮች ሥልጣን ሰጠ። በእውነቱ እነሱም የእሱን ሥልጣን ያጠለሹ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ተገኝተዋል።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ 2020 ከአፍሪካ ሪፖርት ድረ-ገጽ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት እና በሳንካራ ከሥልጣን የተባረሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዣን-ባፕቲስት ኦውድራጎ "የግል ፍላጎት እና የፖለቲካ ማኪያቬሊዝም" በባህሪው ውስጥ ቦታ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሳንካራ በአገሩ ከተቺዎቹ ይልቅ ደጋፊዎቹ ይበዙ ነበር። ቢሆንም ስጋት የደቀኑበት ተቺዎቹ ሆኑ።
ወጣቱ መሪ ከዘመኑ የቀደመ ነበር። በድሆች መወደዱ፤ በተለይም ማርክሲዝምን ማቀንቀኑ እንደ ወዳጆቹ ሁሉ ፓሪስ እና ዋሽግተንን የመሳሰሉ ጠላቶችንም እንዳፈራለት ጠንቅቆ ያውቅው ነበር።
ሳንካራ በተለይ ያኔ የአፍሪካ እና የአረብን ሕዝቦችን አብዮት ያቀነቅኑ ከነበሩት ከሊቢያው መሪ ከኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ ጋር መወዳጀታቸው ደግሞ በጠላቶቻቸው "ይቺ ባቄላ…" እንዲባልላቸው ምክንያት ሆነ።
አዲስ አበባ ደርሶ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባኤ ላይ የዓለም ባንክ እና የዓለም ገንዘብ ድርጅትን አወገዘ። ተቋማቱ ብድር እያሉ አፍሪካን እየበዘበዙ ነው ሲል አወገዘ።
የሳንካራ ውግዘት እና ማሳጣት ምዕራባውያንን ብቻ ሳይሆን በምዕራባውያን ድጋፍ ሥልጣን በተቆናጠጡ የአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ጥርስ አስነከሰበት።
የአገር ወዳዱ ቶማስ ሳንካራ የሥልጣን ዘመን ከአራት ዓመት እንኳን ሳይበልጥ በሴራ በአውሮፓውያኑ 1987 የካቢኔ ስብሰባ ሊያደርግ ሲሄድ በታማኝ ጠባቂዎቹ ተገደለ።
ሳንካራን የገደሉት ሰዎች በጊልበርት ዲንዴሬ የሚታዘዙ ናቸዉ። ዲንድሬ ደግሞ የደኅንነት ኃላፊ እና የብሌስ ኮምፓወሬ ቀኝ እጅ የነበሩ ሰው ነበሩ።
ብዙዎች እንደሚጠረጥሩት ካስገዳዮቹ የሳንካራ የቅርብ ጓድ እና ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ትልቅ ሚና የነበረው ብሌስ ኮምፓዎሬ አንዱ ነው።
ኮምፓዎሬ፤ ከሳንካራ መገደል በኋላ የቀድሞ ጓዱን ሥልጣን ይዞ ቡርኪናፋሶን ለ27 ዓመት ገዝቷል።
እነሆ አሁን ከ30 ዓመታት በኋላ በሳናካራ ግድያ ተባባሪ በመሆን 14 ሰዎች ክስ ተመሥርቶባቸው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ተከሳሾቹ ውሳኔ አልተሰጠባቸውም።
በፈላጭ ቆራጭነት ወደ 30 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የመራው ኮምፓዎሬ ሕዝብ ዐይንህ ላፈር ብሎት፣ ክብር ነስቶት፣ ሥልጣኑን ጥሎ ከፈረጠጠ በኋላ በስደት ሲኖር ዓመታት ተቆጥረዋል።
የአፍሪካው ቼ ጉቬራ ለመባል አራት ዓመት እንኳን ያልፈጀበት ሳንካራ ከተገደለ አስርታት ቢቆጠሩም ክብር ዝናው በመላዉ አፍሪቃ እየናኘ ይገኛል።















